በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእርግጥ ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ ነው?

በእርግጥ ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ ነው?

በእርግጥ ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ ነው?

አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ “መስቀል በጣም የታወቀ የክርስትና መለያ ምልክት ነው” በማለት ይናገራል። በርካታ ሃይማኖታዊ ሥዕሎችና የሥነ ጥበብ ሥራዎች ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንደተቸነከረ ያሳያሉ። መስቀል በመላው ሕዝበ ክርስትና ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው ለምንድን ነው? በእርግጥ ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ ነው?

ብዙዎች የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት እንደምንችል ይናገራሉ። ለምሳሌ የ1954 የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኢየሱስ በተገደለበት ጊዜ በቦታው የነበሩ ሰዎች “ከመስቀል ውረድ” ብለው እንደተዘባበቱበት ይናገራል። (ማቴዎስ 27:40, 42) ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም በተመሳሳይ ሁኔታ ተርጉመውታል። አዲሱ መደበኛ ትርጉም የቀሬና ሰው ስለሆነው ስለ ስምዖን ሲናገር ወታደሮቹም “መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት” ይላል። (ማርቆስ 15:21) በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “መስቀል” ተብሎ የተተረጎመው ስታውሮስ የሚለው የግሪክኛ ቃል ነው። ይሁንና ይህን ቃል መስቀል ብሎ ለመተርጎም የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ? የዚህ ግሪክኛ ቃል ትርጉም ምንድን ነው?

መስቀል ነበር?

ዊልያም ቫይን የተባሉ ግሪካዊ ምሑር እንዳሉት ስታውሮስ የሚለው ቃል “በዋነኝነት የሚያመለክተው ቀጥ ያለ ምሰሶን ወይም እንጨትን ነው። ወንጀለኞች ተቸንክረው የሚገደሉት እንዲህ ባለ እንጨት ላይ ነበር። ስታውሮስ የሚለው ስምም ሆነ በእንጨት ወይም በምሰሶ ላይ መቸንከር የሚል ትርጉም ያለው ስታውሮ የሚለው ግስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ከሚታወቀው አንዱን እንጨት በሌላው ላይ በማጋደም ከሚሠራው መስቀል ተለይቶ መታየት ይኖርበታል።”

ዚ ኢምፔሪያል ባይብል ዲክሽነሪ እንደሚናገረው ስታውሮስ የተባለው ቃል “ማንኛውንም ነገር በላዩ ላይ ለመስቀል የሚያገለግልን ወይም መሬት ላይ ሊቸከል የሚችልን ቀጥ ያለ እንጨት፣ ምሰሶ ወይም ችካል ያመለክታል።” መዝገበ ቃላቱ በመቀጠል “በሮማውያን ዘንድ እንኳ ክሩክስ (ክሮስ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘበት የላቲን ቃል) መጀመሪያ ላይ ቀጥ ያለ ምሰሶን የሚያመለክት ይመስላል” ብሏል። በመሆኑም ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “መስቀል መጀመሪያ ላይ ሹል ጫፍ ያለውን አንድ ወጥ ምሰሶ ያመለክት እንደነበረ የታወቀ ነው” ማለቱ አያስደንቅም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ኢየሱስ የተገደለበትን እንጨት ለማመልከት ዛይሎን የተባለ ሌላ የግሪክኛ ቃል ተጠቅመዋል። ኤ ክሪቲካል ሌክሲከን ኤንድ ኮንኮርዳንስ ቱ ዚ ኢንግሊሽ ኤንድ ግሪክ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ ዛይሎን ለሚለው ቃል “አጠና፣ ቀጥ ያለ እንጨት” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። በመቀጠልም እንደ ስታውሮስ ሁሉ ዛይሎን “ሮማውያን ስቅላት የተፈረደባቸውን ሰዎች የሚቸነክሩበት ቀጥ ያለ እንጨት ወይም ግንድ ነበር” ይላል።

ኪንግ ጀምስ ቨርሽን ከዚህ ጋር በመስማማት በሐዋርያት ሥራ 5:30 ላይ “እናንተ በዛፍ [ዛይሎን] ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሳው” ይላል። ሌሎች ትርጉሞችም ስታውሮስን “መስቀል” እያሉ ሲተረጉሙ ዛይሎንን “ዛፍ” በማለት ተርጉመውታል። ዘ ጀሩሳሌም ባይብል በሐዋርያት ሥራ 13:29 ላይ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከዛፍ [ዛይሎን] ላይ አውርደው በመቃብር አኖሩት” ይላል።

ስታውሮስ እና ዛይሎን የተባሉት የግሪክኛ ቃላት ያላቸውን መሠረታዊ ትርጉም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከላይ የተጠቀሰው ክሪቲካል ሌክሲከን ኤንድ ኮንኮርዳንስ “ሁለቱም ቃላት በአሁኑ ጊዜ መስቀልን የሚያሳዩ ሥዕሎች ከሚያስተላልፉት ሐሳብ ጋር አይስማሙም” ብሏል። በሌላ አባባል የወንጌል ጸሐፊዎች ስታውሮስ የሚለውን ቃል በመጠቀም ሊያስተላልፉ የፈለጉት ሐሳብ ዛሬ ሰዎች መስቀል ብለው ከሚጠሩት ጋር ምንም ዓይነት ተመሳሳይነት የለውም። በመሆኑም የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በ⁠ማቴዎስ 27:40-42 ላይም ሆነ ስታውሮስ የሚለው ቃል በተጠቀሰባቸው ሌሎች ቦታዎች “እንጨት” ወይም “የመከራ እንጨት” የሚለውን ሐረግ መጠቀሙ የተገባ ነው። ኮምፕሊት ጂዊሽ ባይብል ደግሞ “ወንጀለኞች የሚሰቀሉበት እንጨት” የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል።

የመስቀል አመጣጥ

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ መስቀል ላይ እንደተሰቀለ የማይናገር ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያስተምሩና እንደሚከተሉ የሚናገሩት የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንትና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሕንጻዎቻቸውን በመስቀል የሚያስጌጡትና የእምነታቸው ምልክት አድርገው የሚጠቀሙበት ለምንድን ነው? መስቀል ይህን ያህል የታወቀ ምልክት ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

መልሱ መጽሐፍ ቅዱስን እንከተላለን የሚሉ የአብያተ ክርስቲያናት አባላት ብቻ ሳይሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን የማይከተሉና “የክርስትና” አብያተ ክርስቲያናት ከመመሥረታቸው ከብዙ ዘመናት በፊት የኖሩ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ሰዎች ጭምር መስቀልን እንደ ቅዱስ ነገር አድርገው የሚመለከቱት መሆኑ ነው የሚል ነው። የተለያየ ቅርጽና መልክ ያላቸው መስቀሎች አገልግሎት ላይ የዋሉት የሰው ልጅ ሥልጣኔ ከመጀመሩ ከረጅም ጊዜ በፊት አንስቶ እንደሆነ በርካታ ሃይማኖታዊ የማመሳከሪያ ጽሑፎች ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ በጥንታዊው የግብፃውያን ሥዕላዊ የአጻጻፍ ስልት በተጻፉ ጽሑፎችና የሴትና የወንድ አማልክቶቻቸውን በሚያሳዩ ምስሎች ላይ ከላይ በኩል ክብ ቅርጽ ያለው T የሚመስል መስቀል ይታያል። ይህ ዓይነቱ መስቀል አንሳቴ ወይም ባለእጀታ መስቀል ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሕይወትን የሚወክል ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይታመናል። ከጊዜ በኋላ ይህ ዓይነቱ የመስቀል ቅርጽ በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት አግኝቶ በስፋት የሚሠራበት ሆኗል።

ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚናገረው “እጅግ ጥንታዊ የሆነው የመስቀል ዓይነት በሩቅ ምሥራቅና በቅድመ ታሪክ አርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች ዘንድ በሳንስክሪት ቋንቋ ስዋስቲካ በሚል ስያሜ ይበልጥ የሚታወቀው ‘ጋማ’ ክሮስ (ክሩክስ ጋማታ) የሚባለው መስቀል ሳይሆን አይቀርም።” ይህን ምልክት በሰፊው የሚጠቀሙበት በሕንድ የሚገኙ የሂንዱ እምነት ተከታዮች እንዲሁም በመላው እስያ የሚኖሩ ቡድሂስቶች ሲሆኑ በዛሬው ጊዜም በእነዚህ አካባቢዎች በጌጣጌጦችና በሕንጻዎች ላይ በብዛት ይታያል።

መስቀል “የክርስትና” ምልክት እንዲሆን የተደረገው መቼ እንደሆነ በውል አይታወቅም። በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ እንደሚከተለው ይላል፦ “በ3ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አጋማሽ ላይ አብያተ ክርስቲያናት ከአንዳንዶቹ የክርስትና እምነት መሠረተ ትምህርቶች ርቀዋል ወይም ትምህርቶቹን አዛብተዋቸዋል። በክህደት ላይ የተመሠረቱትን አብያተ ክርስቲያናት ክብር ከፍ ለማድረግ ሲባል አረማውያን ምንም የእምነት ለውጥ ሳያደርጉ በአብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት አገኙ።” እንዲሁም መስቀልን ጨምሮ “የነበሯቸውን አረማዊ ምልክቶችና አርማዎች ይዘው እንዲቀጥሉ ተፈቀደላቸው።”

አንዳንድ ጸሐፊዎች የፀሐይ አምልኮ ተከታይ የሆነው ቆስጠንጢኖስ በ312 ዓ.ም. ዘመቻ ላይ እንዳለ በሕልሙ ፀሐይ ላይ “ኢን ሆክ ዊንካስ” (በዚህ ድል ትነሳለህ) የሚል የላቲን ጽሑፍ የተጻፈበት መስቀል ማየቱን እንደተናገረ ይጠቅሳሉ። ከጊዜ በኋላ ይህ “የክርስቲያኖች” ምልክት መላው ሠራዊቱ በሚይዛቸው አርማዎች፣ ጋሻዎችና የጦር ትጥቆች ሁሉ ላይ እንዲቀረጽ ተደረገ። (በስተግራ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስትና እንደተለወጠ ይነገር እንጂ የተጠመቀው ይህ ከሆነ ከ25 ዓመታት በኋላ በሞት አፋፍ ላይ እንዳለ ነበር። አንዳንዶች ይህን ያደረገበትን ምክንያት በጥርጣሬ ይመለከታሉ። ዘ ነን ክርስቺያን ክሮስ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “ቆስጠንጢኖስ ይህን ያደረገው የናዝሬቱን ኢየሱስ ትምህርቶች ተቀብሎ ስለተለወጠ ሳይሆን ክርስትናን ተገዥዎቹ በሙሉ የሚቀበሉት ካቶሊካዊ [ሁሉን አቀፍ] ሃይማኖት እንዲሆን ለማመቻቸት ሲል ነበር።”

ከዚያ ጊዜ ወዲህ ብዙ ዓይነት ቅርጽና መልክ ያላቸው መስቀሎች አገልግሎት ላይ ውለዋል። ለምሳሌ ዚ ኢለስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ የቅዱስ አንቶኒ መስቀል ተብሎ የሚጠራው የመስቀል ዓይነት “T የሚመስል ቅርጽ ያለው ሲሆን አንዳንዶች ይህ የመስቀል ዓይነት ታሙዝ የተባለው የባቢሎናውያን አምላክ ምልክት ከሆነው ታው ከሚባል ፊደል የመጣ እንደሆነ ያስባሉ።” በተጨማሪም የቅዱስ እንድርያስ መስቀል የሚባል የመስቀል ዓይነት ያለ ሲሆን ይህ መስቀል በX ቅርጽ የተሠራና በአብዛኛው ወረድ ያለ አግዳሚ ያለበት ባለ ሁለት ቅስት መስቀል ነው። ይህ የX ቅርጽ ያለው መስቀል የላቲን መስቀል ተብሎ የሚጠራም ሲሆን በተለምዶ “ጌታችን የተገደለው በዚህ ዓይነት መስቀል ነው” የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ።

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የነበራቸው አመለካከት

በአንደኛው መቶ ዘመን ኢየሱስ ሲያስተምር ያዳመጡ ብዙ ሰዎች አማኞች ከመሆናቸውም በላይ የእሱ መሥዋዕታዊ ሞት የማዳን ኃይል ያለው መሆኑን እንደተቀበሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ አይሁዶች ከሰበከና ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ እንደሆነ በሚገባ ካስረዳ በኋላ የሆነውን ነገር ሲገልጽ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የምኩራብ አለቃው ቀርስጶስ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ። መልእክቱን የሰሙ በርካታ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ይጠመቁ ጀመር።” (የሐዋርያት ሥራ 18:5-8) በዚህ ወቅት ጳውሎስ ምንም ዓይነት የአምልኮ ምልክት ወይም ምስል አላስተዋወቀም፤ ከዚህ ይልቅ የእምነት ባልንጀሮቹ ‘ከጣዖት አምልኮ እንዲሸሹ’ መክሯቸዋል።—⁠1 ቆሮንቶስ 10:14

ታሪክ ጸሐፊዎችም ሆኑ ተመራማሪዎች የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በመስቀል ይጠቀሙ እንደነበረ የሚያሳይ አንድም ማስረጃ ሊያገኙ አልቻሉም። በ17ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የነበረ አንድ ጸሐፊ “የተባረከው ኢየሱስ ውርደትን ከምንም ሳይቆጥር መከራን ታግሦ የተገደለበትን መሣሪያ ደቀ መዛሙርቱ ሲያከብሩ ማየት ሊያስደስተው ይችላል?” የሚል ጥያቄ አንስቶ እንደነበር ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክሮስ የተባለው መጽሐፍ መግለጹ ልብ ሊባል ይገባል። አንተስ ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ?

አንድ ሰው የሚያቀርበው አምልኮ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ የምስሎች ወይም የሚታዩ ነገሮች እርዳታ አያስፈልገውም። ጳውሎስ “የአምላክ ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋር ምን ስምምነት አለው?” ሲል ጠይቋል። (2 ቆሮንቶስ 6:14-16) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የተሰቀለበትን መሣሪያ የሚመስል ነገር ሠርተው እንዲያመልኩ የሚያዝ ቃል አንድም ቦታ አናገኝም።—ከማቴዎስ 15:3 እና ከ⁠ማርቆስ 7:13 ጋር አወዳድር።

ታዲያ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት ምንድን ነው? መስቀል ወይም ማንኛውም ዓይነት ሌላ ምልክት ሳይሆን ፍቅር ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እየሰጠኋችሁ ነው፤ ልክ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐንስ 13:34, 35

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የወንጌል ጸሐፊዎች ሊያስተላልፉ የፈለጉት ሐሳብ ዛሬ ሰዎች መስቀል ብለው ከሚጠሩት ጋር ምንም ዓይነት ተመሳሳይነት የለውም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስታውሮስ ላይ የተፈጸመን ስቅላት የሚያሳይ የ17ኛው መቶ ዘመን ሥዕል፣ ከሊፕስየስ “ዴ ክሩሴ” የተወሰደ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕይወትን የሚወክለውን የአንሳቴ መስቀል የሚያሳይ ግርግዳ ላይ የተሳለ የግብፃውያን ሥዕል (14ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ገደማ)

[የሥዕሉ ምንጭ]

© DeA Picture Library / Art Resource, NY

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በላክስሚ ናራያን የሂንዱ ቤተ መቅደስ ላይ የሚገኝ ጋማ ክሮስ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

From the book The Cross in Tradition, History, and Art (1897)