ከአምላክ ቃል ተማር
ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?
ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎች በማንሳት መልሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች በመልሶቹ ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።
1. ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?
ከሰው ልጆች በተለየ መልኩ ኢየሱስ በምድር ላይ ከመወለዱ በፊት በሰማይ መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይኖር ነበር። (ዮሐንስ 8:23) የአምላክ የመጀመሪያ ፍጥረት ሲሆን ሌሎች ፍጥረታት በሙሉ በተፈጠሩበት ጊዜ በሥራው ተባብሯል። በይሖዋ በቀጥታ የተፈጠረው እሱ ብቻ በመሆኑ የአምላክ “አንድያ ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። ኢየሱስ የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለግል ስለነበር “ቃል” ተብሎም ተጠርቷል።—ዮሐንስ 1:1-3, 14፤ ምሳሌ 8:22, 23, 30ን እና ቆላስይስ 1:15, 16ን አንብብ።
2. ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለምንድን ነው?
አምላክ በሰማይ የሚኖረውን የልጁን ሕይወት ማርያም ወደተባለች አንዲት ድንግል አይሁዳዊት ማህፀን በማዛወር ወደ ምድር ላከው። በመሆኑም ኢየሱስ ሰብዓዊ አባት አልነበረውም። (ሉቃስ 1:30-35) ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው (1) ስለ አምላክ እውነቱን ለማስተማር (2) የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ ምሳሌ ለመተው እና (3) ፍጹም ሕይወቱን “ቤዛ” አድርጎ ለመስጠት ነው።—ማቴዎስ 20:28ን እና ዮሐንስ 18:37ን አንብብ።
3. ቤዛ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
ቤዛ አንድን በባርነት የተያዘን ሰው ለማስለቀቅ የሚከፈል ዋጋ ነው። አምላክ የሰው ልጆች እንዲሞቱና እንዲያረጁ ዓላማው አልነበረም። ይህን እንዴት እናውቃለን? አምላክ ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአት ብሎ የሚጠራውን ነገር ቢሠራ እንደሚሞት ነግሮት ነበር። አዳም ኃጢአት ባይሠራ ኖሮ ፈጽሞ አይሞትም ነበር። አዳም ከመሞቱ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ካመፀበት ቀን አንስቶ ወደ ሞት ማዝገም ጀምሯል። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 5:5) አዳም ኃጢአትንና የኃጢአት ደሞዝ የሆነውን ሞት ለዘሮቹ በሙሉ አስተላልፏል። በመሆኑም ሞት በእሱ አማካኝነት ወደ ሰው ዘር ዓለም “ገባ።” ቤዛ ያስፈለገን በዚህ ምክንያት ነው።—ሮም 5:12ን እና 6:23ን አንብብ።
4. ኢየሱስ መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው?
እኛን ከሞት ባርነት ለማላቀቅ ማን ቤዛ ሊከፍልልን ይችላል? በምንሞትበት ጊዜ የቅጣት ዋጋ የምንከፍለው ራሳችን ለሠራነው ኃጢአት ብቻ ነው። በመሆኑም ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ለሌሎች ኃጢአት ዋጋ መክፈል አይችሉም።—መዝሙር 49:7-9ን አንብብ።
ኢየሱስ ከሰብዓዊ አባት አለፍጽምናን ባለመውረሱ የሞተው በራሱ ኃጢአት ሳይሆን ለሌሎች ኃጢአት ሲል ነው። አምላክ ለሰው ዘር ያለውን ከፍተኛ ፍቅር ለመግለጽ ሲል ልጁ እንዲሞትልን ወደ ምድር ልኮታል። ኢየሱስም ቢሆን አባቱን በመታዘዝ ለእኛ ኃጢአት ሲል ሕይወቱን በመስጠት ፍቅሩን አሳይቷል።—ዮሐንስ 3:16ን እና ሮም 5:18, 19ን አንብብ።
5. ኢየሱስ በአሁኑ ወቅት ምን እያደረገ ነው?
ኢየሱስ በምድር ሳለ የታመሙትን በመፈወስ፣ የሞቱትን በማስነሳት እንዲሁም ሰዎችን ከአደገኛ ሁኔታ በመታደግ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች ወደፊት የሚያደርገውን ነገር በናሙና መልክ አሳይቷል። (ሉቃስ 18:35-42፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ አምላክ ከሞት በማስነሳት መንፈሳዊ ሕይወት ሰጥቶታል። (1 ጴጥሮስ 3:18) በመሆኑም ኢየሱስ በምድር ሁሉ ላይ ለመግዛት የሚያስችለውን ኃይል ይሖዋ እስኪሰጠው ድረስ በአምላክ ቀኝ ሆኖ ሲጠባበቅ ነበር። (ዕብራውያን 10:12, 13) በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ በሰማይ ላይ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ሲሆን በምድር ላይ የሚገኙት የእሱ ተከታዮች ደግሞ በዓለም ዙሪያ ይህን ምሥራች እያወጁ ነው።—ዳንኤል 7:13, 14ን እና ማቴዎስ 24:14ን አንብብ።
በቅርቡ ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን በመጠቀም መከራንም ሆነ ለመከራ መንስኤ የሆኑትን ነገሮችን በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል። በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር የሚያሳዩና እሱን የሚታዘዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ በደስታ ይኖራሉ።—መዝሙር 37:9-11ን አንብብ።