በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ሁኔታ ነው?

የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ሁኔታ ነው?

የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ሁኔታ ነው?

የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት ቤነዲክት 16ኛ የናዝሬቱ ኢየሱስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “የአምላክ መንግሥት የሚመጣው ተቀባይ በሆነ ልብ በኩል ነው” በማለት ገልጸዋል። ለአንዳንድ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ከዚህ ያለፈ ትርጉም የለውም፤ እነዚህ ሰዎች አንድ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን ሲቀበልና በእሱ ላይ እምነት ሲያሳድር በውስጡ የሚካሄድ ለውጥ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይሁንና የአምላክ መንግሥት ሲባል አንድ ሰው በግለሰብ ደረጃ የሚያደርገው የባሕርይ ለውጥ ወይም ‘በልብህ ውስጥ ብቻ ያለ’ ነገር ነው?

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ለአምላክ መንግሥት ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትም “የኢየሱስ ስብከት የሚያጠነጥነው” በአምላክ መንግሥት ዙሪያ እንደሆነ አምነው ተቀብለዋል። ኢየሱስ፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አጭር በነበረው የአገልግሎት ዘመኑ “የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ” በመላው አገሪቱ ዞሯል። (ማቴዎስ 4:23) ኢየሱስ ባስተማረው ትምህርትና በፈጸማቸው ተአምራት አማካኝነት የአምላክ መንግሥት ሲባል አንድ ሰው አምላክን ተቀብሎ መታዘዙ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ አድርጓል። መንግሥቱ አገዛዝን፣ ፍርድንና ዘላለማዊ በረከቶችን የሚያጠቃልል ነገር ነው።

አገዛዝና ፍርድ

በኢየሱስ አገልግሎት መገባደጃ አካባቢ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የነበሩት የያዕቆብና የዮሐንስ እናት ወደ ኢየሱስ ቀርባ “በመንግሥትህ እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ፣ አንዱ በቀኝህ አንዱ ደግሞ በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ” አለችው። (ማቴዎስ 20:21) እናታቸው እየተናገረች የነበረው በልጆቿ ልብ ውስጥ ስላለ ነገር እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ በዚህ መንግሥት ውስጥ ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙ ሰዎች እንዳሉ ተረድታ ስለነበር ልጆቿ በመንግሥቱ ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው ፈልጋ ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ ለ11ዱ ታማኝ ሐዋርያት በመንግሥቱ ውስጥ ቦታ እንደሚኖራቸውና ‘በዙፋኖች ተቀምጠው’ ከእሱ ጋር ‘እንደሚፈርዱ’ ቃል ገብቶላቸዋል። (ሉቃስ 22:30) ተከታዮቹ የኢየሱስን መንግሥት የተረዱት እውነተኛ አገዛዝ ማለትም አስተዳደር ወይም መስተዳድር እንደሆነ አድርገው ነበር።

በኢየሱስ ዘመን ለነበሩት ለአብዛኞቹ ሰዎችስ የአምላክ መንግሥት ምን ትርጉም ነበረው? ሰዎች በግለሰብ ደረጃ የሚያደርጉት የባሕርይ ለውጥ እንደሆነ አድርገው ተረድተውት ነበር? ወይስ ከዚያ ያለፈ ነገር ይጠብቁ ነበር? በ33 ዓ.ም. የዋለው ፋሲካ በዓል ከመከበሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አቀባበል ያደረገለት ሕዝብ “የዳዊትን ልጅ እባክህ አድነው!” በማለት ጮዃል። (ማቴዎስ 21:9) ሕዝቡ እንዲህ ብሎ የጮኸው ለምን ነበር? ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ እንደሆነና አምላክ ዘላለማዊ መንግሥት የሆነውን “የአባቱን የዳዊትን ዙፋን” እንደሚሰጠው ተገንዝበው ስለነበረ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። መንግሥቱ የሚያመጣውን መዳን፣ ሰላምና ፍትሕ ናፍቀው ነበር።—ሉቃስ 1:32፤ ዘካርያስ 9:9

ዘላለማዊ በረከቶች

ኢየሱስ ለሚያከናውነው አገልግሎት ግድ የሌላቸው የሚመስሉ ሰዎችም እንኳ እሱ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል ስለ አንዱ ያውቁ ነበር። ኢየሱስ በተገደለበት ጊዜ ከጎኑ የተሰቀለ አንድ ወንጀለኛ “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” በማለት ለምኖት ነበር። ታዲያ የኢየሱስ መልስ ምን ነበር? በሞት አፋፍ ላይ ለነበረው ለዚያ ሰው “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት አጽናንቶታል።—ሉቃስ 23:42, 43

ያ ዘራፊ ካቀረበው ጥያቄ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ከሙታን ከተነሳ በኋላ መንግሥቱን እንደሚቀበል ወይም ወደዚያ እንደሚገባ እምነት ነበረው። ኢየሱስም ያንን ሰው በብዙ ሚሊዮን ከሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ጋር ከሞት ለማስነሳትና ባሕርይው እንዲለውጥ ለማድረግ የሚያስችል ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ፍላጎቱም ጭምር አለው። አዎን፣ በመንፈሳዊው ዓለም ሥልጣን የተቀዳጀው ኢየሱስ በመንግሥቱ አማካኝነት በመላው ምድር ለሚኖሩ የሰው ዘሮች ዘላለማዊ በረከቶችን ያመጣል።—ዮሐንስ 5:28, 29

በመካከላቸው የነበረ መንግሥት

ነገር ግን ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት በመካከላችሁ ነው” ብሎ ተናግሮ አልነበረም? አዎን፣ ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ በ⁠ሉቃስ 17:21 ላይ ይገኛል። እንዲያውም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “የእግዚአብሔር መንግሥት በውሥጣችሁ ናት” በማለት ተርጉመውታል። (ለምሳሌ፣ የ1879 ትርጉምን እና ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብልን ተመልከት።) ታዲያ ኢየሱስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር?

በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው እሱን ለሚቃወሙና ፈሪሳውያን ተብለው ለሚጠሩ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ነበር። እነዚህ ሰዎች ከመሲሑና ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ ይሆናል ብለው የሚጠብቁት ነገር ነበራቸው። መሲሑ አይሁዳውያንን ከሮማውያን ነፃ ለማውጣትና ለእስራኤል ንጉሣዊ መንግሥትን ለመመለስ እንደ ድል አድራጊ ንጉሥ ሆኖ “ከሰማይ ደመና ጋር” እንደሚመጣ ይጠብቁ ነበር። (ዳንኤል 7:13, 14) ይሁን እንጂ ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት በግልጽ በሚታይ ሁኔታ አይመጣም” ብሎ በመናገር አመለካከታቸው የተሳሳተ መሆኑን አመልክቷል። ከዚያም “የአምላክ መንግሥት በመካከላችሁ ነው” ብሏቸዋል።—ሉቃስ 17:20, 21

ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት የዚህ መንግሥት ንጉሥ መሆኑን በግልጽ ለይቶ የሚያሳውቅ ትምህርት ሲያስተምርና ተአምራትን ሲፈጽም ንጹሕ ልብም ሆነ እውነተኛ እምነት ያልነበራቸው ፈሪሳውያን ይበልጡን ተቃወሙት። የኢየሱስን መሲሕነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ተጠራጠሩ። ስለዚህ ሐቁን ይኸውም በተሾመው ንጉሥ የተወከለው መንግሥት ‘በመካከላቸው መሆኑን’ ፍርጥርጥ አድርጎ ነገራቸው። ኢየሱስ ይህን ሲል መንግሥቱን በውስጣቸው እንዲፈልጓት መናገሩ አልነበረም። * ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እዚያው ፊታቸው ቆመውላቸው ነበር። ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት እዚሁ ከእናንተ ጋር ነው” ያላቸው በዚህ ምክንያት ነው።—ሉቃስ 17:21 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን

ትልቅ ቦታ ልትሰጠው የሚገባ መንግሥት

የአምላክ መንግሥት ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች ልብ ውስጥ የማይኖር ቢሆንም በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባ ነገር መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ ባስተማረው ትምህርትም ሆነ ባከናወናቸው ተአምራት አማካኝነት አድማጮቹ እውነተኛ ሰላምና መረጋጋትን በሚያመጣው ጽድቅ በሰፈነበት አገዛዙ ላይ ከልብ የመነጨ እምነት እንዲያሳድሩ ጥረት አድርጓል። በሕይወታቸው ላይ ለውጥ የሚያመጣ እምነት እንዲኖራቸው ይፈልግ ነበር። እንዲያውም “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ከኢየሱስ አድማጮች ውስጥ ብዙዎቹ በተናገራቸው ቃላት ልባቸው ተነክቶ የአምላክን መንግሥት በረከቶች ለማግኘት ሲሉ ኢየሱስን ለመከተል እንዲነሳሱ የሚያደርግ እምነት ሊኖራቸው ችሏል።

አንተስ እንዲህ ዓይነት እምነት እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን እምነት ለመገንባት ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ መክፈቻ ላይ የተናገራቸውን “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና” የሚሉትን ቃላት አስታውስ። (ማቴዎስ 5:3) እንግዲያውስ ይህን መጽሔት ያመጡልህ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን አብረሃቸው እንድታጠና ያቀረቡልህን ግብዣ ለምን አትቀበልም? እንዲህ ካደረግህ በግለሰብ ደረጃ የባሕርይ ለውጥ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛና ጻድቅ በሆነው አገዛዝ ላይ ማለትም ለሁሉም ሰው ሰላምና ደኅንነት በሚያመጣው መንግሥት ላይ ተስፋ መጣል ትጀምራለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ኢየሱስ እየተነጋገረ የነበረው ከፈሪሳውያን ጋር ነው፤ ፈሪሳውያን ደግሞ ተቃዋሚዎች ስለነበሩ ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ የባሕርይ ለውጥ እንዳደረጉ ወይም ተቀባይ ልብ እንዳላቸው አድርጎ ሊናገር እንደማይችል የተረጋገጠ ነው።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የአምላክ መንግሥት ኢየሱስን በግትርነት በሚቃወሙና ሊገድሉት በሚፈልጉ ተቃዋሚዎች ልብ ውስጥ ነበር?