በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አምናለሁ”

“አምናለሁ”

በእምነታቸው ምሰሏቸው

“አምናለሁ”

ማርታ ወንድሟ የተቀበረበት ዋሻ በአንድ ትልቅ ድንጋይ ተከርችሞ በዓይነ ሕሊናዋ እየታያት ሳይሆን አይቀርም። ሐዘኗ የድንጋዩን ያህል ከባድ ሆኖባታል። የምትወደው ወንድሟ አልዓዛር በሞት እንደተለያት መቀበል በጣም ከብዷታል። ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ባሉት አራት ቀናት ውስጥ ስለነበረው ለቅሶና ሊያስተዛዝኑ ስለመጡት እንግዶች ስታስብ ሕልም ውስጥ እንዳለች ሆኖ ይሰማታል።

የአልዓዛር የቅርብ ወዳጅ የሆነው ኢየሱስ አጠገቧ ቆሟል። ማርታ ኢየሱስን ስታየው ሐዘኗ እንደ አዲስ ተቀስቅሶባታል፤ ምክንያቱም በዓለም ላይ ወንድሟን ከሞት መታደግ ይችል የነበረው ብቸኛ ሰው እሱ እንደሆነ ታውቃለች። ያም ሆኖ የቢታንያ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ማርታ ኢየሱስ በመምጣቱ በተወሰነ መጠንም ቢሆን መጽናናት ችላለች፤ አሁን የሚገኙት በኮረብታ ላይ ከተቆረቆረችው ቢታንያ ከምትባለው ትንሽ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ስፍራ ነው። ከእሱ ጋር በቆየችባቸው ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ፊቱ ላይ የሚነበበውን የደግነት ስሜት ስትመለከት እፎይታ ተሰምቷታል፤ ሁሌም የምታደንቅለት ለሌሎች የማዘን ባሕርይው እንደወትሮው ሁሉ የብርታት ምንጭ ሆኖላታል። ኢየሱስ በእምነቷና በትንሣኤ ተስፋ ላይ እንድታተኩር የሚረዷትን ጥያቄዎች ጠየቃት። ያደረጉት ጭውውት ማርታ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውን የሚከተለውን ሐሳብ እንድትናገር አነሳስቷታል፦ “አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆንህን አምናለሁ።”​—ዮሐንስ 11:27

ማርታ አስደናቂ እምነት ያላት ሴት ነበረች። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሷ የሚናገረው ጥቂት ነገር ቢሆንም እምነታችንን እንድናጠናክር ሊረዳን የሚችል ትልቅ ትምህርት ይዟል። እንዲህ ያልንበትን ምክንያት ለመረዳት ማርታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰችበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንመልከት።

“ትጨነቂያለሽ፣ ትጠበቢያለሽ”

ጊዜው አልዓዛር ከመሞቱ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ነው። በወቅቱ አልዓዛር ጤነኛ ነበር። አልዓዛር በቢታኒያ በሚገኘው ቤቱ አንድ ትልቅ እንግዳ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስን ሊያስተናግድ ነው። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው አልዓዛር፣ ማርታና ማርያም አንድ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበረ ይመስላል። ማርታ እንግዳ የምታስተናግድበት መንገድ ጋባዧ እሷ እንደሆነች የሚያስመስል በመሆኑና ስሟ ከሌሎቹ ቀድሞ የተጠቀሰባቸው ጊዜያት በመኖራቸው አንዳንድ ተመራማሪዎች የሁሉም ታላቅ እሷ ሳትሆን እንደማትቀር ይናገራሉ። (ዮሐንስ 11:5) ከሦስቱ መካከል አግብቶ የነበረ ሰው ይኑር አይኑር ማወቅ የሚቻልበት መንገድ የለም። ያም ሆነ ይህ ሦስቱም የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች ሆነው ነበር። ኢየሱስ በይሁዳ በሚያገለግልበት ወቅት ሕዝቡ ከሚያደርስበት ተቃውሞና ከሚያሳየው ጥላቻ አንጻር ሲታይ የእነማርታ ቤት ጥሩ ማረፊያ ሆኖለት ነበር። ኢየሱስ በዚያ ቤት ሲቆይ የሚያገኘውን ሰላምና የሚደረግለትን ድጋፍ አድንቆ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

ማርታ ቤቱ ለእንግዳ የሚመች እንዲሆን ለማድረግ ብዙ ሥራ ይጠብቃታል። ጉድጉድ ማለት የምትወደው ይህች ታታሪ ሴት ብዙ ጊዜ ወከባ የሚበዛባት ትመስላለች። ማርታ ተፍተፍ ያበዛችው ኢየሱስ ስለሚመጣ ብቻ ሳይሆን ወትሮውንም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ሰው ስለሆነች ነው። ማርታ ጊዜ ሳታጠፋ ለዚህ የተከበረ እንግዳዋና ምናልባትም ለተወሰኑት የጉዞ ጓደኞቹ የተለያዩ ምግቦችን በመሥራት ለየት ያለ ግብዣ ማዘጋጀት ጀመረች። በዚያ ዘመን እንግዳ መቀበል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። አንድ እንግዳ ቤታቸው ሲመጣ ስመው ይቀበሉታል፤ ከዚያም ጫማውን አውልቀው እግሩን የሚያጥቡት ሲሆን ጥሩ መዓዛ ባለው ፈሳሽ ቅባትም ራሱን ይቀቡታል። (ሉቃስ 7:44-47) እንዲሁም ጥሩ ማረፊያና ጣፋጭ ምግብ ይዘጋጅለታል።

ከዚህ አንጻር ማርታና ማርያም የሚመጣባቸውን ትልቅ እንግዳ ለመቀበል ብዙ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር። አንዳንዶች ከማርታ ይልቅ አስተዋይና ቁምነገረኛ እንደሆነች አድርገው የሚያስቧት ማርያም መጀመሪያ ላይ እህቷን ስታግዛት እንደቆየች ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ሲመጣ ግን ሁኔታው ተለወጠ። ኢየሱስ ይህ አጋጣሚ ሌሎችን ለማስተማር አመቺ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር፤ ደግሞም ያደረገው ይህንኑ ነው! በዘመኑ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በተለየ መልኩ ኢየሱስ ሴቶችን ያከብር የነበረ ከመሆኑም ሌላ የስብከቱ ጭብጥ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት በደስታ ያስተምራቸው ነበር። ማርያም ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም በጣም ስለጓጓች በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ እያንዳንዱን ቃል በጥሞና ታዳምጥ ጀመር።

በዚህ ጊዜ ማርታ ምን ያህል ውጥረት እንደሚበዛባት መገመት አያዳግትም። ማርታ ያን ሁሉ ምግብ አዘጋጅታ ለማቅረብና እንግዶቿን ለማስተናገድ ወዲያ ወዲህ ማለቷ የፈጠረባት ጫና ቀስ በቀስ እንድትጨነቅና እንድትጠበብ አድርጓታል። አንዳንድ ነገሮችን ለማሰናዳት ስታልፍ ስታገድም እህቷ እሷን ከማገዝ ይልቅ ቁጭ ብላ ስታያት በሁኔታው በመበሳጨት በረጅሙ ተንፍሳ ወይም ፊቷ ተለዋውጦ አሊያም ግንባሯ ተቋጥሮ ይሆን? ከሆነም አይፈረድባትም። ያንን ሁሉ ሥራ ብቻዋን ልትሠራው አትችልም ነበር!

አሁን ግን ማርታ ብስጭቷን አምቃ መያዝ አልቻለችም። እናም የኢየሱስን ንግግር በማቋረጥ “ጌታ ሆይ፣ እህቴ ሥራውን ሁሉ ለእኔ ጥላ ስትቀመጥ ምንም ግድ አይሰጥህም? እንድታግዘኝ ንገራት እንጂ” በማለት የታፈነውን ስሜቷን አወጣችው። (ሉቃስ 10:40) ይህ ኃይለኛ ንግግር ነው። ኢየሱስ ማርያምን ተቆጥቶ ወደ ሥራዋ እንድትመለስ እንዲያዛት ፈልጋ ነበር።

ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ብዙ ሰዎች እንደሚሰማቸው ሁሉ ማርታም የኢየሱስ ምላሽ አስገርሟት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ረጋ ባለ መንፈስ እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ማርታ፣ ማርታ፣ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፣ ትጠበቢያለሽ። ይሁንና የሚያስፈልገው ጥቂት ወይም አንድ ነገር ብቻ ነው። ማርያም በበኩሏ የተሻለውን ነገር መርጣለች፤ ይህም ከእሷ አይወሰድባትም።” (ሉቃስ 10:41, 42) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ማርታ ሥጋዊ ለሆኑ ነገሮች ከልክ በላይ እንደምትጨነቅ መናገሩ ነበር? ጥሩ ምግብ ለማዘጋጀት ስትል መልፋቷን ከምንም አልቆጠረውም ማለት ነው?

በፍጹም አይደለም። ኢየሱስ ማርታ ይህን ያደረገችው በፍቅርና በንጹሕ ልብ ተነሳስታ መሆኑን ተገንዝቦ እንደነበር ግልጽ ነው። ሌላው ቀርቶ አንድን እንግዳ ለመቀበል ድል ያለ ግብዣ ማዘጋጀት ስህተት እንደሆነ አልተሰማውም። ማርታ ቤት ከመጋበዙ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ማቴዎስ ለእሱ ባዘጋጀው “ትልቅ ግብዣ” ላይ በደስታ ተገኝቶ ነበር። (ሉቃስ 5:29) እዚህ ላይ አነጋጋሪው ጉዳይ ማርታ ያዘጋጀችው ግብዣ ሳይሆን ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር ነው። ትኩረቷ ሁሉ ያረፈው ሰፊ ግብዣ ማዘጋጀት ላይ ስለነበር ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ሳይታያት ቀረ። ይህ ነገር ምንድን ነው?

የይሖዋ አምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ስለ እውነት ለማስተማር በቤቷ ተገኝቷል። ጣት የሚያስቆረጥመው ምግቧንና እሱን ለመቀበል ያደረገቻቸውን ሌሎች ዝግጅቶች ጨምሮ ማንኛውም ነገር ከዚህ ሊበልጥባት አይገባም ነበር። ኢየሱስ ማርታ እምነቷን ለማጠናከር የሚያስችላት ልዩ አጋጣሚ እያመለጣት በመሆኑ እንዳዘነ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ያም ሆኖ የራሷን ምርጫ እንድታደርግ ትቷታል። ማርታ የራሷን ምርጫ ማድረግ መብቷ ቢሆንም ማርያም ትምህርቱን ማዳመጥ ትታ ሥራ እንድታግዛት ለማስገደድ ኢየሱስን መጠየቋ ግን ሌላ ጉዳይ ነው።

ስለዚህ ኢየሱስ የማርታን ስሜት ለማረጋጋት ስሟን ሁለት ጊዜ ደጋግሞ ከጠራ በኋላ ቀስ አድርጎ እርማት የሰጣት ሲሆን ‘ስለ ብዙ ነገሮች መጨነቅና መጠበብ’ አስፈላጊ እንዳልሆነ ገለጸላት። በተለይ መንፈሳዊ ድግስ ሲኖር አንድ ወይም ሁለት ዓይነት ቀለል ያሉ ምግቦችን ማዘጋጀት ይበቃ ነበር። እንግዲያው ኢየሱስ ማርያም ያደረገችውን ‘የተሻለ ምርጫ’ ማለትም ከእሱ የመማር መብቷን በምንም ዓይነት አይወስድባትም!

በማርታ ቤት ውስጥ ስለተከናወነው ሁኔታ የሚገልጸው ይህ ዘገባ በዛሬው ጊዜ ላሉ የክርስቶስ ተከታዮች ብዙ ትምህርት ይዟል። እኛም “መንፈሳዊ” ፍላጎታችንን እንዳናሟላ ምንም ነገር እንቅፋት እንዲሆንብን መፍቀድ አይኖርብንም። (ማቴዎስ 5:3) ማርታ የተወችውን የልግስናና የታታሪነት ምሳሌ መከተል የምንፈልግ ቢሆንም ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እስኪያመልጡን ድረስ እንግዳ ከመቀበል ጋር በተያያዘ ያን ያህል ቦታ ለማይሰጣቸው ነገሮች ‘መጨነቅና መጠበብ’ አንፈልግም። ከእምነት አጋሮቻችን ጋር የምንገናኝበት ዋነኛው ምክንያት ምርጥ ምርጥ ምግቦችን ለማቅረብ ወይም ለመመገብ ሳይሆን እርስ በርስ ለመበረታታትና መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለማካፈል ነው። (ሮም 1:11, 12) እንዲህ የመሰለ የሚያንጽ ጊዜ ለማሳለፍ በጣም ቀለል ያለ ግብዣ ማድረጉ ብቻ እንኳ ሊበቃ ይችላል።

በጣም የምትወደው ወንድሟ ሞቶ ተነሳ

ታዲያ ማርታ ኢየሱስ ለስለስ ባለ መንገድ የሰጣትን ተግሣጽ ተቀብላ በተግባር አውላው ይሆን? መልሱን ለማግኘት ብዙም መጨነቅ አያስፈልገንም። ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ማርታ ወንድም የሚገልጸውን አስደናቂ ዘገባ ሲጀምር “ኢየሱስ ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር” በማለት ይነግረናል። (ዮሐንስ 11:5) ኢየሱስ ቢታንያ በሚገኘው የእነማርታ ቤት ከተጋበዘ ወራት አልፎታል። ዮሐንስ ከላይ ከተናገረው ሐሳብ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ማርታ ኢየሱስ ፍቅራዊ ምክር ስለሰጣት አላኮረፈችውም እንዲሁም አልተቀየመችውም፤ ከዚህ ይልቅ ምክሩን ከልቧ ተቀብላለች። በዚህም ረገድ ቢሆን ለእኛ ግሩም የእምነት ምሳሌ ትሆነናለች፤ ደግሞስ ከመካከላችን አልፎ አልፎ መጠነኛ እርማት የማያስፈልገው ማን አለ?

ማርታ ወንድሟ በታመመ ጊዜ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል አስታምማዋለች። ሥቃዩን ለማስታገስና ከሕመሙ እንዲሻለው ለማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርጋለች። አልዓዛር ግን እያደር ሕመሙ እየጠናበት ሄደ። እህቶቹ ቀን ከሌት ከጎኑ ሳይለዩ ተንከባከቡት። ማርታ የተዳከመውን የወንድሟን ፊት ባየች ቁጥር ለበርካታ ዓመታት በደስታም ሆነ በሐዘን ወቅት አብረው ያሳለፏቸው ጊዜያት ፊቷ ላይ ድቅን ይሉባት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።

ማርታና ማርያም ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ሲረዱ ወደ ኢየሱስ መልእክት ላኩ። በወቅቱ ኢየሱስ እነሱ ካሉበት የሁለት ቀን መንገድ ገደማ ርቆ በሚገኝ ቦታ እየሰበከ ነበር። “ጌታ ሆይ፣ የምትወደው ሰው ታሟል” የሚል አጭር መልእክት ላኩበት። (ዮሐንስ 11:1, 3) ኢየሱስ ወንድማቸውን እንደሚወደው ያውቁ ነበር፤ በመሆኑም ወዳጁን ለመርዳት የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ እምነት ነበራቸው። ኢየሱስ አልዓዛር ሳይሞት ይደርሳል ብለው ተስፋ አድርገው ይሆን? ከሆነ ተስፋቸው መና ሊቀር ነው። አልዓዛር ሞተ።

ማርታና ማርያም ወንድማቸውን አልቅሰው ቀበሩት፤ በቢታንያና በዙሪያዋ የሚኖሩ በርካታ ሰዎችም እነሱን ለማስተዛዘን መጡ። ኢየሱስ ግን ወሬው የለም። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሁኔታው ማርታን ግራ ሳያጋባት አልቀረም። አልዓዛር በሞተ በአራተኛው ቀን ኢየሱስ ወደ ከተማይቱ አቅራቢያ እንደደረሰ ሰማች። ምንጊዜም ቀልጣፋ የሆነችው ማርታ ሐዘን ላይ ብትሆንም እንኳ ወሬውን ስትሰማ ለማርያም ምንም ሳትላት ኢየሱስን ለማግኘት በፍጥነት ተነስታ ወጣች።​—ዮሐንስ 11:20

ማርታ ጌታዋን ገና ስታየው “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” በማለት ባለፉት ቀናት በእሷም ሆነ በማርያም አእምሮ ውስጥ ሲጉላላ የነበረውን ሐሳብ ተናገረች። እርግጥ ነው፣ ማርታ የነበራት ተስፋና እምነት አሁንም ቢሆን አልጠፋም። “ያም ሆኖ አሁንም አምላክ የጠየቅከውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጥህ አውቃለሁ” በማለት አክላ መናገሯ ይህን ያሳያል። ወዲያውኑም ኢየሱስ ተስፋዋን ለማጠናከር “ወንድምሽ ይነሳል” አላት።​—ዮሐንስ 11:21-23

ማርታ ኢየሱስ የተናገረው ወደፊት ስለሚፈጸመው ትንሣኤ ስለመሰላት “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” አለችው። (ዮሐንስ 11:24) በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላት እምነት አስደናቂ ነው። ምንም እንኳ ትንሣኤ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሰፈረ ግልጽ ትምህርት ቢሆንም ሰዱቃውያን የሚባሉ አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ትንሣኤ መኖሩን ይክዱ ነበር። (ዳንኤል 12:13፤ ማርቆስ 12:18) ይሁን እንጂ ማርታ ኢየሱስ ስለ ትንሣኤ ተስፋ እንዳስተማረ አልፎ ተርፎም የአልዓዛርን ያህል ሞተው የቆዩ ባይሆኑም እንኳ ሙታንን እንዳስነሳ ታውቃለች። ቀጥሎ ምን ሊከናወን እንደሆነ ግን የምታውቀው ነገር የለም።

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” በማለት የማይረሳ ነገር ተናገረ። በእርግጥም ይሖዋ አምላክ፣ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙታንን እንዲያስነሳ ለልጁ ሥልጣን ሰጥቶታል። ኢየሱስ ማርታን “ይህን ታምኛለሽ?” ሲል ጠየቃት። እሷም በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የሰፈረውን መልስ ሰጠችው። ኢየሱስ መሲሕ ወይም ክርስቶስ እንደሆነ እንዲሁም የይሖዋ አምላክ ልጅና ነቢያት ወደ ዓለም እንደሚመጣ ትንቢት የተናገሩለት እሱ እንደሆነ እምነት ነበራት።​—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:25-27

ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ዓይነት እምነት ሲመለከቱ ምን ይሰማቸዋል? ቀጥሎ በማርታ ፊት የተከናወኑት ነገሮች ለዚህ ጥያቄ የማያሻማ መልስ ይሰጣሉ። ማርታ እህቷን ለመጥራት በፍጥነት ሄደች። ከዚያም በኋላ ኢየሱስ ከማርያምና አብረዋት ካሉት ሐዘንተኞች ጋር ሲነጋገር ስሜቱ ምን ያህል በጥልቅ እንደተነካ አስተዋለች። ሞት የሚያስከትለው መሪር ሐዘን በጥልቅ እንደተሰማው ያለ ምንም ይሉኝታ እንባውን በማፍሰስ ሲገልጽ ተመለከተች። ከዚያም ኢየሱስ ከወንድሟ መቃብር ላይ ድንጋዩን አንከባለው እንዲያነሱ ትእዛዝ ሲሰጥ ሰማችው።​—ዮሐንስ 11:28-39

ምንጊዜም ምክንያታዊ የሆነችው ማርታ ከሞተ አራት ቀን ስለሆነው አሁን እንደሚሸት በመግለጽ ተቃውሞዋን አሰማች። ኢየሱስም “ካመንሽ የአምላክን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርኩሽም?” አላት። እሷም በማመኗ የይሖዋ አምላክን ክብር ማየት ቻለች። እዚያው እንደቆሙ ይሖዋ አልዓዛርን ከሞት እንዲያስነሳው ለልጁ ኃይል ሰጠው! ቀጥሎ የተከናወኑት ነገሮች በማርታ ላይ ምን ስሜት ፈጥረው ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” በማለት ሲጣራ፤ ከዋሻው ውስጥ የሚንኮሻኮሽ ድምፅ ሲሰማ፤ አልዓዛር ከሞት ተነስቶ ከነመግነዙ ቀስ ብሎ እየተራመደ ከዋሻው ሲወጣ፤ ኢየሱስ “ፍቱትና ይሂድ” ብሎ ትእዛዝ ሲሰጥ፤ በተጨማሪም በእርግጠኝነት መናገር እንደሚቻለው እሷና ማርያም በታላቅ ደስታ ተውጠው ወንድማቸው አንገት ላይ ጥምጥም ሲሉበት የነበረውን ሁኔታ መቼም ቢሆን አትረሳውም። (ዮሐንስ 11:40-44) አሁን ማርታ የድንጋይ ያህል ከብዷት ከነበረው ሐዘኗ ተገላግላለች!

ይህ ዘገባ እንደሚያሳየው የሙታን ትንሣኤ የሕልም እንጀራ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ልብን በደስታ የሚሞላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ከዚህ በፊት የተፈጸመ ታሪካዊ ሐቅ ነው። ይሖዋና ልጁ ለማርታ፣ ለማርያምና ለአልዓዛር እንዳደረጉት ሰዎች ለሚያሳዩት እምነት ወሮታ መክፈል ያስደስታቸዋል። አንተም እንደ ማርታ ጠንካራ እምነት ከገነባህ ወደፊት እንዲህ ያለ ወሮታ ይጠብቅሃል። *

“ማርታ ታገለግላቸው” ነበር

የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ከዚህ በኋላ ማርታን ጠቅሶ የሚናገረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ወቅቱ ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው የመጨረሻው ሳምንት መባቻ ነው። ኢየሱስ ከፊቱ ምን መከራ እንደሚጠብቀው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በቢታንያ ለማረፊያነት የመረጠው አሁንም የእነማርታን ቤት ነው። ከዚያ በመነሳት 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም በእግሩ መጓዝ ይችላል። ኢየሱስና አልዓዛር በሥጋ ደዌ በተያዘው በስምዖን ቤት ራት እየበሉ ነው፤ ማርታ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰችው በዚህ ጊዜ ሲሆን ዘገባው ‘ታገለግላቸው ነበር’ በማለት ስለ እሷ በጨረፍታ ይጠቅሳል።​—ዮሐንስ 12:2

በእርግጥም ይህች ሴት እንዴት ያለች ታታሪ ነበረች! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከእሷ ጋር መጀመሪያ ስንገናኝ በሥራ ተጠምዳ ነበር፤ ስንሰናበታትም አብረዋት ያሉትን ለማስተናገድ የተቻላትን ያህል ተፍ ተፍ እያለች ነበር። ዛሬ ያሉ የክርስቶስ ተከታዮች በጉባኤዎቻቸው ውስጥ እንደ ማርታ ያሉ ማለትም ራሳቸውን በማቅረብ ምንጊዜም እምነታቸውን በተግባር የሚያሳዩ መንፈሰ ጠንካራና ለጋስ ሴቶች በመኖራቸው ተባርከዋል። ማርታ በዚህ ባሕርይዋ እስከ መጨረሻው ቀጥላ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። ከሆነ ብልህ መሆኗን አሳይታለች ማለት ነው፤ ምክንያቱም በሕይወቷ ውስጥ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ይጠብቋታል።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ማርታ የምትወደው ጌታዋ ኢየሱስ በአሰቃቂ መንገድ ሲገደል የሚሰማትን ሐዘን በጽናት መቋቋም ነበረባት። ከዚህም በላይ ኢየሱስን ያስገደሉት ግብዝ የሆኑት ነፍሰ ገዳዮች አልዓዛርንም ለመግደል ቆርጠው ተነስተው ነበር፤ ምክንያቱም የእሱ ከሞት መነሳት ብዙዎች በኢየሱስ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። (ዮሐንስ 12:9-11) ደግሞም ይዋል ይደር እንጂ በጣም የሚዋደደው የማርታ ቤተሰብ በሞት መለያየቱ አይቀርም። ሞት የእነማርታን ቤት ያንኳኳው እንዴትና መቼ እንደሆነ ባናውቅም ማርታ የነበራት ትልቅ እምነት እስከ መጨረሻው እንድትጸና ረድቷታል ብለን በእርግጠኝነት መናገራችን ምክንያታዊ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ማርታን በእምነቷ መምሰላቸው የተገባ የሆነው ለዚህ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.27 የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ስለሆነው ስለ ትንሣኤ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 7⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርታ ሐዘን ላይ ብትሆንም እንኳ ኢየሱስ እምነትን በሚያጠናክሩ ነገሮች ላይ እንድታተኩር የሰጣትን ምክር ተቀብላለች

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርታ ‘ተጨንቃና ተጠብባ’ የነበረ ቢሆንም የተሰጣትን እርማት በትሕትና ተቀብላለች

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአልዓዛር ከሞት መነሳት ማርታ በኢየሱስ ላይ እምነት ማሳደሯ ከንቱ እንዳልቀረ አስገንዝቧታል