አረጋውያን እንደገና ወጣት የሚሆኑበት ጊዜ
ወደ አምላክ ቅረብ
አረጋውያን እንደገና ወጣት የሚሆኑበት ጊዜ
እርጅና ብቻህን ና የሚባለው ያለምክንያት አይደለም። የቆዳ መሸብሸብን፣ የዓይን መፍዘዝን፣ የመስማት ችግርንና የጉልበት መድከምን የመሰሉ የእርጅና ውጤቶችን ደስ ብሎት የሚቀበል ሰው የለም። ‘ሕይወታችን በእርጅና የሚያከትም ከሆነ አምላክ በወጣትነት ብርታት እንድንደሰት አድርጎ የፈጠረን ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ደስ የሚለው ነገር አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ ይህ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አምላክ እርጅና ከሚያስከትለው ጣጣ እኛን ለመገላገል ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጓል! በኢዮብ 33:24, 25 (NW) ላይ የሚገኙትን ኤሊሁ ለኢዮብ የተናገራቸውን ቃላት ልብ በል።
ታማኝና በይሖዋ ዘንድ ተወዳጅ የነበረውን የኢዮብን ሁኔታ እስቲ እንመርምር። ኢዮብ ምንም የሚያውቀው ነገር ባይኖርም ሰይጣን ‘ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ ነው’ በማለት ንጹሕ አቋሙ ጥያቄ ላይ እንዲወድቅ አደረገ። ይሖዋ ነገሮችን መልሶ ማስተካከል እንደሚችል ስለሚያውቅና በኢዮብ ላይ ሙሉ እምነት ስለነበረው ሰይጣን ኢዮብን እንዲፈትነው ፈቀደ። ከዚያም ሰይጣን “[ኢዮብን] ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጠጕሩ በክፉ ቍስል መታው።” (ኢዮብ 2:7) የኢዮብን ሰውነት ትል የወረሰው ሲሆን ቆዳው ያፈከፍክ፣ ይጠቁርና እየተቀረፈ ይወድቅ ነበር። (ኢዮብ 7:5፤ 30:17, 30) ኢዮብ ምን ያህል እንደተሠቃየ መገመት ትችላለህ? ያም ቢሆን “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 27:5 NW
ይሁን እንጂ ኢዮብ ከባድ ስህተት ሠርቶም ነበር። በሞት አፋፍ ላይ እንዳለ በተሰማው ጊዜ የራሱን ንጽሕና በማረጋገጥ ላይ ብቻ በማተኮር “ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ [አደረገ]።” (ኢዮብ 32:2) የአምላክ ቃል አቀባይ የሆነው ኤሊሁ ለኢዮብ ተግሣጽ ሰጥቶታል። ይሁንና ኤሊሁ ከአምላክ ዘንድ የመጣ የሚከተለውን አጽናኝ መልእክትም ለኢዮብ ነግሮታል፦ “ቤዛ ስላገኘሁ ወደ ጉድጓድ [መቃብር] ከመውረድ [ኢዮብን] አድነው! ሥጋው ከልጅ ሥጋ የበለጠ ይለምልም ብርቱ ወደነበረበት የወጣትነት ዘመኑም ይመለስ።” (ኢዮብ 33:24, 25 NW) እነዚህ ቃላት ለኢዮብ ተስፋ ፈንጥቀውለት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም እስኪሞት ድረስ መሠቃየት አያስፈልገውም። ኢዮብ ንስሐ እስከገባ ድረስ አምላክ ለኢዮብ የቀረበውን ቤዛ ሊቀበልና ከደረሰበት መከራ ነፃ ሊያወጣው ፈቃደኛ ነው። *
ኢዮብ የተሰጠውን እርማት በትሕትና ተቀብሎ ንስሐ ገብቷል። (ኢዮብ 42:6) ይሖዋ ለኢዮብ የቀረበውን ቤዛ እንደተቀበለ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይህ ደግሞ የኢዮብን ኃጢአት እንዲሸፍንለት ብሎም ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዲመልሰውና እንዲባርከው መንገድ ከፍቶለታል። ይሖዋ “ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን የኢዮብን ሕይወት ባረከ።” (ኢዮብ 42:12-17) ኢዮብ ያገኛቸው ሌሎች በረከቶች እንዳሉ ሆነው ከአስከፊ በሽታው ሲፈወስና “ሥጋው ከልጅ ሥጋ የበለጠ” ሲለመልም ምን ያህል እንደተደሰተ መገመት ትችላለህ!
ለኢዮብ የቀረበውን ቤዛ አምላክ የተቀበለው ቢሆንም ያስገኘው ጥቅም ውስን ነበር። ምክንያቱም ቤዛው ኢዮብን ፍጹም እንዲሆን ማድረግ አልቻለም፤ ደግሞም ከጊዜ በኋላ ሞቷል። አሁን ግን እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው ቤዛ ተከፍሎልናል። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ልጁን ኢየሱስን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) በቤዛው ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች በሙሉ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል። በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ አምላክ ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆችን እርጅና ከሚያስከትለው ጣጣ ይገላግላቸዋል። ያረጁ ሰዎች ‘ሥጋቸው ከልጅነት ሥጋ የበለጠ ሲለመልም’ በሚያዩበት በዚያን ጊዜ ለመገኘት አልጓጓህም? ታዲያ ለዚያ ጊዜ ብቁ እንድትሆን የሚያስችልህን እውቀት ለምን አትቀስምም?
በሚያዝያ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦
▪ ከኢዮብ 16 እስከ 37
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 እዚህ ላይ የገባው “ቤዛ” የሚለው ቃል የኃጢአት መሸፈኛ የሚል ትርጉም አለው። (ኢዮብ 33:24) ከኢዮብ ጋር በተያያዘ የሚቀርበው ቤዛ፣ አምላክ የኢዮብን ኃጢአት ለመሸፈን ወይም ለማስተሰረይ የሚቀበለው የእንስሳ መሥዋዕት ሊሆን ይችላል።—ኢዮብ 1:5