በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው?

“የሰው ልጅ እንኳ የመጣው . . . በብዙዎች ምትክ ነፍሱን [ወይም፣ ሕይወቱን] ቤዛ አድርጎ ለመስጠት [ነው]።”​—ማርቆስ 10:45

ኢየሱስ ምን እንደሚጠበቅበት ያውቅ ነበር። በሕይወቱ ውስጥ ሰላሙን የሚያደፈርስ ነገር እንደሚያጋጥመው ተረድቶ ነበር። እንዲያውም ገና በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ በሚያሳዝን ሁኔታ ሕይወቱ እንደሚቀጭ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ሞትን ለመጋፈጥ ዝግጁ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ሞት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው የኢየሱስ ሞት በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ በሚጠራው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ወደ 175 ጊዜ በቀጥታ ተጠቅሷል። ለመሆኑ ኢየሱስ መሠቃየትና መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው? የኢየሱስ ሞት በእኛ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ስለሚችል የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን አስፈላጊ ነው።

ኢየሱስ እንደሚደርስበት ይጠብቀው የነበረው ነገር፦

ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው በመጨረሻው ዓመት ውስጥ ወደፊት ስለሚጠብቀው ሥቃይና ሞት በተደጋጋሚ ጊዜ በመናገር ደቀ መዛሙርቱን አዘጋጅቷቸው ነበር። ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ፋሲካን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም በሚሄድበት ጊዜ ለ12ቱ ሐዋርያት እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል፤ እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፣ ይተፉበታል፣ ይገርፉታል፣ ከዚያም ይገድሉታል፤ ሆኖም ከሦስት ቀን በኋላ ይነሳል።” * (ማርቆስ 10:33, 34) ኢየሱስ በእሱ ላይ ስለሚደርሰው ነገር ይህን ያህል እርግጠኛ የነበረው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ አሟሟቱን በሚመለከት በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተነገሩትን በርካታ ትንቢቶች ያውቃል። (ሉቃስ 18:31-33) ስለ አሟሟቱ የተነገሩ አንዳንድ ትንቢቶችንና እነዚህ ትንቢቶች እንዴት እንደተፈጸሙ የሚያሳዩ ጥቅሶች እንመልከት፦

መሲሑ . . .

ኢየሱስ እነዚህንም ሆነ ሌሎች ትንቢቶችን ፈጽሟል። ኢየሱስ እነዚህ ትንቢቶች በራሱ ላይ እንዲፈጸሙ ማድረግ የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ሁሉ ትንቢቶች በእሱ ላይ ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው በእርግጥም ከአምላክ የተላከ እንደነበረ አረጋግጠዋል። *

ይሁንና ኢየሱስ መሠቃየቱና መሞቱ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ የሞተው ለተነሱት ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ለማስገኘት ነው፦

ኢየሱስ በኤደን ገነት ስለተነሱትና አጽናፈ ዓለማዊ ይዘት ስላላቸው ወሳኝ ጥያቄዎች ያውቅ ነበር። አዳምና ሔዋን አንድ ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር የነገራቸውን ቃል ሰምተው አምላክን ላለመታዘዝ መረጡ። እነዚህ ባልና ሚስት የተከተሉት የዓመፅ አካሄድ ‘አምላክ ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት አለው?’ የሚል ጥያቄ አስነሳ። በተጨማሪም ‘ፈተና ሲደርስበት ለአምላክ ያለውን ታማኝነት መጠበቅ የሚችል ሰው ይኖራል?’ የሚል ጥያቄ አስነስቷል።​—ዘፍጥረት 3:1-6፤ ኢዮብ 2:1-5

ኢየሱስ ከይሖዋ ሉዓላዊነትም ሆነ ሰዎች ንጹሕ አቋማቸውን ከመጠበቃቸው ጋር በተያያዘ ለተነሱት ሁለት ጥያቄዎች የማያወላዳ መልስ ሰጥቷል። ኢየሱስ “በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ” ፍጹም ታዛዥነት በማሳየት የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፏል። (ፊልጵስዩስ 2:8) በተጨማሪም ኢየሱስ ፍጹም የሆነ ሰው በጣም ከባድ መከራ ቢደርስበትም እንኳ ንጹሕ አቋሙን መጠበቅ እንደሚችል አረጋግጧል።

ኢየሱስ የሞተው ለሰው ልጆች ቤዛ ለመሆን ሲል ነው፦

ነቢዩ ኢሳይያስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሠቃየቱና መሞቱ ለሰዎች ኃጢአት ስርየት እንደሚያስገኝ ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 53:5, 10) ኢየሱስ ይህን በግልጽ ተረድቶ ስለነበር “በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ” በፈቃደኝነት ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት መሞቱ ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲመሠርቱ ብሎም ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚሆኑበት መንገድ እንዲከፈትላቸው አስችሏል። በተጨማሪም የኢየሱስ ሞት ሰዎች አዳምና ሔዋን ያጡትን ነገር ይኸውም ፍጹም በሆነ መንገድ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋን እንዲያገኙ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። *​—ራእይ 21:3, 4

ምን ማድረግ ትችላለህ?

በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ማለት ከየት እንደመጣ፣ ሕይወቱ ምን ይመስል እንደነበርና የሞተው ለምን እንደሆነ መርምረናል። ስለ ኢየሱስ እነዚህን እውነቶች ማወቃችን ስለ እሱ ያለንን የተሳሳተ አመለካከት ለማስተካከል ይረዳናል። በተጨማሪም እሱን በሚመለከት ያገኘነውን እውቀት ተግባራዊ ማድረጋችን ሌሎች በረከቶችንም ያስገኝልናል፤ በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ጥቅሞችን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል።

  • ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና እሱ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና የበለጠ ለማወቅ ጥረት አድርግ።​—ዮሐንስ 17:3

  • ኢየሱስ አዳኝህ መሆኑን እንደምትቀበል በአኗኗርህ በማንጸባረቅ በእሱ ላይ እምነት እንዳለህ በተግባር አሳይ።​—ዮሐንስ 3:36፤ የሐዋርያት ሥራ 5:31

“የዘላለም ሕይወት” ማግኘት የምንችለው የአምላክ ‘አንድያ ልጅ’ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው፤ በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ እንድታውቅ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው።​—ዮሐንስ 3:16

^ አን.5 ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ራሱን “የሰው ልጅ” በማለት ይጠራ ነበር። (ማቴዎስ 8:20) ይህ አገላለጽ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው መሆኑን ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‘የሰው ልጅ’ ተብሎ ትንቢት የተነገረለት እሱ መሆኑን ይጠቁማል።​—ዳንኤል 7:13, 14

^ አን.13 በኢየሱስ ላይ ስለተፈጸሙት ትንቢቶች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ​—አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ” የሚለውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።

^ አን.17 የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ስላለው ጥቅም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ “ቤዛው​—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ” የሚለውን ምዕራፍ 5⁠ን ተመልከት።