በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በርባን የፈጸመው ወንጀል ምን ነበር?

▪ አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች ሮማዊው ገዥ ጳንጥዮስ ጲላጦስ በኢየሱስ ፋንታ ስለ ፈታው በርባን የተባለ ሰው ተናግረዋል። ይህ ሰው ‘በዓመፀኝነቱ የታወቀ እስረኛ’ እና “ወንበዴ” ተብሎ ተጠርቷል። (ማቴዎስ 27:16፤ ዮሐንስ 18:40) በርባን “ዓመፅ በማነሳሳት ሰው ገድለው” በኢየሩሳሌም በሚገኘው የሮማውያን እስር ቤት ውስጥ “ከታሰሩ ዓመፀኞች መካከል” አንዱ ነበር።—ማርቆስ 15:7

በርባን ስለሠራው ወንጀል የሚናገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሆነ ማስረጃ ባይገኝም ከዓመፀኞች ጋር መመደቡ አንዳንድ ምሑራንን በመጀመሪያው መቶ ዘመን በእስራኤል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደርጉ ከነበሩ የዓማፂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ነበረው ወደሚል መደምደሚያ አድርሷቸዋል። የታሪክ ምሑር የሆነው ፍላቭየስ ጆሴፈስ፣ በወቅቱ የነበሩት የዓማፂያን ቡድኖች ከፍተኛ ሕዝባዊ ትግል ያደርጉ እንደነበር ጽፏል፤ እነዚህ ወንጀለኞች ለአይሁዳውያን ጭቁን ገበሬዎች ፍትሕ ለማስገኘት እንደሚታገሉ ይናገሩ ነበር። ሮማውያንና የአይሁድ ባለሥልጣናት የሚፈጽሙትን ኢፍትሐዊ ድርጊት የሚቃወሙ የዓማፂያን ቡድኖች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. አጋማሽ ላይ እንደ አሸን ፈልተው ነበር። በ66 ዓ.ም. ሮማውያንን ከይሁዳ ያባረረው የአይሁድ ጦር ሠራዊት በአብዛኛው የተገነባው በእነዚህ የዓማፂ ቡድኖች ነበር።

አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ ብሏል፦ “በገጠር ከሚገኙት የወንበዴ ቡድኖች አንዱ በበርባን የሚመራ ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ የወንበዴ ቡድኖች በተራው ሕዝብ የተወደዱ ነበሩ፤ ምክንያቱም በእስራኤል የሚኖሩ ሀብታሞችን ያጠቁ የነበረ ሲሆን ለሮማ መንግሥትም ራስ ምታት ሆነው ነበር።”

በሮማውያን ዘመን ኢየሱስ በተገደለበት መንገድ የሚቀጡት ምን ዓይነት ወንጀል የሠሩ ሰዎች ነበሩ?

▪ ሮማውያን ወንበዴዎችን፣ ወንጀለኞችንና በመንግሥት ወይም በሥልጣን ላይ የሚያምፁ ሌሎች ሰዎችን ለመቅጣት የሚጠቀሙበት ዘዴ በእንጨት ላይ ከቸነከሯቸው በኋላ እንዲሞቱ እዚያው መተው ነበር። ይህ ዘዴ ከሁሉ የከፋ የሞት ቅጣት ማስፈጸሚያ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር።

ፓለስታይን ኢን ዘ ታይም ኦቭ ጂሰስ የተባለው መጽሐፍ “ይህ ቅጣት በሕዝብ ፊት የሚደረግ፣ የሚያዋርድና ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል ነበር። እንዲሁም በመንግሥት አሠራር ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰዎችን ልብ ለማራድ ተብሎ የተዘጋጀ ነበር” ብሏል። በጥንት ጊዜ የኖረ አንድ ሮማዊ ጸሐፊ ወንጀለኞች በሞት ስለሚቀጡበት መንገድ ሲናገር “ብዙ ሰዎች እንዲያዩትና ፍርሃት እንዲያድርባቸው ለማድረግ ሲባል ሰው በጣም የሚበዛባቸው መንገዶች ይመረጡ ነበር” ብሏል።

ጆሴፈስ እንደገለጸው የቲቶ ወታደሮች በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን ሲከቡ አይሁዳውያን በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ አንድን የጦር ምርኮኛ ከከተማዋ ቅጥር ፊት ለፊት ከላይ በተገለጸው መንገድ በሞት ቀጥተው ነበር። በመጨረሻም ከተማዋ በሮማውያን እጅ ስትወድቅ ብዙዎች ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል።

በታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት በአንድ ጊዜ ብዙ ሰው ካለቀባቸው በዚህ መልክ የተፈጸሙ የሞት ቅጣቶች ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ የያዘው በስፓርታከስ (73-71 ዓ.ዓ.) መሪነት የተካሄደውን ዓመፅ ለማስቆም ከካፑዌ ወደ ሮም በሚወስደው መንገድ ላይ 6,000 ባሪያዎችና ግላዲያተሮች እንጨት ላይ የተሰቀሉበት ቅጣት ነው።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በርባንን ፍታልን” በቻርልስ ሙለር፣ 1878