በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገሃነም እሳታማ ማሠቃያ ስፍራ ነው?

ገሃነም እሳታማ ማሠቃያ ስፍራ ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ገሃነም እሳታማ ማሠቃያ ስፍራ ነው?

▪ ኢየሱስ የገሃነም ፍርድን አስመልክቶ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያዎች በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ እናገኛለን። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ አድማጮቹ ለእነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ክብደት እንዲሰጡ ፈልጎ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ዘላለማዊ መሠቃያ ስለሆነ እሳታማ ቦታ ነው?​—ማቴዎስ 5:22

እስቲ በመጀመሪያ ገሃነም የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት። ጊኤና የሚለው የግሪክኛ ቃል “የሄኖም ሸለቆ” የሚል ትርጉም ካለው ጌሂኖም ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር አንድ ዓይነት ትርጉም አለው፤ የጌሂኖም የተሟላ አጠራር ጌ በኔ ሂኖም ሲሆን ፍቺውም “የሄኖም ልጆች ሸለቆ” የሚል ነው። (ኢያሱ 15:8፤ 2 ነገሥት 23:10) በዛሬው ጊዜ ዋዲ ኤር ርባቢ ተብሎ የሚጠራው ይህ ቦታ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሚገኝ ጥልቀት ያለውና ጠባብ የሆነ ሸለቆ ነው።

በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በነበሩት የይሁዳ ነገሥታት ዘመን ይህ ቦታ ልጆችን መሥዋዕት ለማድረግ በእሳት ማቃጠልን ጨምሮ የተለያዩ አረማዊ የአምልኮ ሥርዓቶች ይካሄዱበት ነበር። (2 ዜና መዋዕል 28:1-3፤ 33:1-6) አምላክ ባስተላለፈው ፍርድ መሠረት ባቢሎናውያን ክፋት በሠሩት አይሁዳውያን ላይ በዚሁ ሸለቆ እልቂት እንደሚያደርሱባቸው ነቢዩ ኤርምያስ ትንቢት ተናግሯል። *​—ኤርምያስ 7:30-33፤ 19:6, 7

ዴቪድ ኪምሂ የተባሉ አይሁዳዊ ምሑር (ከ1160 እስከ 1235 ዓ.ም. ገደማ) እንዳሉት ከሆነ ከጊዜ በኋላ ሸለቆው የኢየሩሳሌም ከተማ ቆሻሻ መድፊያ ሆነ። ይህ ቦታ እሳቱ የማይጠፋ የቆሻሻ ማቃጠያ ስፍራ ሆኖ ያገለግል ጀመር። ወደዚያ የተጣለ ማንኛውም ነገር ሙሉ በሙሉ ተቃጥሎ ዶግ አመድ ይሆን ነበር።

በርካታ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ጌኤና የሚለውን ግሪክኛ ቃል ለማመልከት የገባው “ገሃነመ እሳት” የሚለው ሐረግ የማሠቃያ ስፍራን እንደሚያመለክት ያስተምራሉ። (ማቴዎስ 5:22 አ.መ.ት.) ለምን? እንዲህ ያደረጉት ክፉዎች ከሞቱ በኋላ እሳታማ ፍርድ ይጠብቃቸዋል የሚለውን አረማዊ ምንጭ ያለውን ትምህርት፣ ከኢየሩሳሌም ውጪ ከሚገኘው የቆሻሻ ማቃጠያ ሸለቆ ጋር ግንኙነት እንዳለው ስላሰቡ ነው። ይሁንና ኢየሱስ አንድም ጊዜ ቢሆን ገሃነምን ከማሠቃየት ጋር አያይዞት አያውቅም።

ኢየሱስ ሰዎችን በሕይወት እያሉ ማቃጠል የሚለውን ሐሳብ በሰማይ ያለው አባቱ ይሖዋ እንደሚጸየፈው ያውቃል። አምላክ በነቢዩ ኤርምያስ ዘመን ገሃነም ምን ዓይነት አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ያላዘዝኋቸውን፣ ከቶም ያላሰብሁትን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አቃጥለው ለመሠዋት በሄኖም ልጅ ሸለቆ የቶፌትን መስገጃ ኰረብቶች ሠሩ።” (ኤርምያስ 7:31) ከዚህም በተጨማሪ የሞቱ ሰዎች በእሳታማ ሲኦል ይሠቃያሉ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ አፍቃሪ የሆነው አምላክ ካሉት ባሕርያት ጋርም ሆነ “ሙታን ግን ምንም አያውቁም” ከሚለው ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጋጫል።​—መክብብ 9:5, 10

ኢየሱስ “ገሃነም” የሚለውን አገላለጽ አምላክን መቃወም የሚያስከትለውን ፍጹም ጥፋት ለማመልከት ተጠቅሞበታል። “ገሃነም” የሚለው ቃል በራእይ መጽሐፍ ላይ ከተጠቀሰው “የእሳት ሐይቅ” ጋር ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም አለው። ሁለቱም ቃላት ትንሣኤ የሌለውን ዘላለማዊ ጥፋት ያመለክታሉ።​—ሉቃስ 12:4, 5፤ ራእይ 20:14, 15

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ይህን ትንቢት አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “በኢየሩሳሌም ላይ በደረሰው ጥፋት የተገደሉት አይሁዳውያን በጣም ብዙ ስለነበሩ አስከሬናቸው ሳይቀበር እንዲበሰብስ ወይም እንዲቃጠል በሸለቆው ውስጥ ተጥሏል።”