በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጥንት ዘመን የነበረው ሕይወት​—ገንዘብ

በጥንት ዘመን የነበረው ሕይወት​—ገንዘብ

በጥንት ዘመን የነበረው ሕይወት​—ገንዘብ

“ኢየሱስ በመዋጮ ዕቃዎቹ ትይዩ ተቀምጦ ሕዝቡ በመዋጮ ዕቃዎቹ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንደሚከቱ መመልከት ጀመረ፤ ብዙ ሀብታሞችም ብዙ ሳንቲሞች ይከቱ ነበር። በዚህ ጊዜ አንዲት ድሃ መበለት መጥታ በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ከተተች።”​—ማርቆስ 12:41, 42

መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ስለ ገንዘብ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ በወንጌል ዘገባዎች ላይ ተገልጾ እንደሚገኘው ኢየሱስ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን ለማስተማር የተለያዩ የሳንቲም ዓይነቶችን ተጠቅሟል። ኢየሱስ ከላይ በቀረበው ጥቅስ ላይ የተጠቀሰችው መበለት በመዋጮ ዕቃው ውስጥ “ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” በመጨመር ያደረገችውን መዋጮ ትምህርት ለመስጠት ተጠቅሞበታል። በሌላ ወቅት ደግሞ ተከታዮቹ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ሊኖራቸው ስለሚገባው አመለካከት እንዲያስተውሉ ለመርዳት ዲናር ተብሎ የሚጠራውን የሳንቲም ዓይነት ተጠቅሟል። *​—ማቴዎስ 22:17-21

ሰዎች ገንዘብን የፈጠሩት ለምንድን ነው? በጥንት ዘመን ገንዘብ ይዘጋጅ የነበረው እንዴት ነው? ይገለገሉበት የነበረውስ እንዴት ነው? ደግሞስ ለገንዘብ ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ምን እንማራለን?

ዕቃን በዕቃ ከመለወጥ ውድ በሆኑ የብረት ዓይነቶች መገበያየት

ገንዘብ ከመፈጠሩ በፊት ሰዎች የሚገበያዩት ዕቃን በዕቃ በመለወጥ ነበር። እኩል ዋጋ ያላቸውን ዕቃዎችና አገልግሎቶች ይለዋወጡ ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ የግብይት ሥርዓት አመቺ የማይሆንባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሁለት ገበያተኞች በዚህ መንገድ ለመገበያየት አንደኛው ግለሰብ ሌላኛው የያዘውን ዕቃ የሚፈልገው ዓይነት መሆን አለበት። በተጨማሪም ገበያተኞች ለመለወጫ የሚጠቀሙባቸውን በቀላሉ ለመያዝ የማይመቹ ነገሮችን ለምሳሌ እንስሳትን መንዳት ወይም በከረጢት እህል መሸከም ያስፈልጋቸው ነበር።

ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ ግን ገበያተኞች ዕቃዎችን ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ የሚያገለግል ለአያያዝ አመቺ የሆነ መገበያያ እንደሚያስፈልግ ተገነዘቡ። መፍትሔ ሆኖ ያገኙት እንደ ወርቅ፣ ብርና መዳብ ያሉ ውድ ብረቶችን መጠቀም ነበር። በዚህ ገጽ ላይ ያለው ሥዕል አንድ ነጋዴ አንዳንድ ዕቃዎችን ለመግዛት ወይም የሚፈልገውን አገልግሎት ለማግኘት በጌጣጌጥና በጥፍጥፍ መልክ በተዘጋጁ ብረቶች ሲጠቀም ያሳያል። ግብይቱ ከመፈጸሙ በፊት እነዚህ ብረቶች በጥሩ ሚዛኖች በደንብ ይመዘኑ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም ለውድ ባለቤቱ ለሣራ የመቃብር ቦታ ሲገዛ የተጠየቀውን ያህል ብር መዝኖ ሰጥቷል።​—ዘፍጥረት 23:14-16

ይሖዋ ለእስራኤላውያን በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ በሰጠበት ጊዜ ስግብግብ ነጋዴዎች ደንበኞቻቸውን ለማታለል የተጭበረበሩ ሚዛኖችን ወይም ትክክለኛ ያልሆኑ መለኪያዎችን ይጠቀሙ ነበር። ይሖዋ ማጭበርበርን ስለሚጸየፍ ለእስራኤላውያን ነጋዴዎች “እውነተኛ መለኪያ፤ [እና] እውነተኛ መመዘኛ” እንዲጠቀሙ አሳስቧቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:36፤ ምሳሌ 11:1) በአሁኑ ጊዜ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ይሖዋ ስለ ስግብግብነትና ስለ ማጭበርበር ያለው አመለካከት ዛሬም ቢሆን እንዳልተለወጠ ልብ ማለት ይገባቸዋል።​—ሚልክያስ 3:6፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

መጀመሪያ ላይ ሳንቲሞች ይመረቱ የነበረው እንዴት ነው?

የመጀመሪያዎቹ ሳንቲሞች የተሠሩት ከ700 ዓ.ዓ. ቀደም ብሎ በሊዲያ (የአሁኗ ቱርክ) ሳይሆን አይቀርም። ብዙም ሳይቆይ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ብረት ሠራተኞች ሳንቲሞችን በገፍ መሥራት ጀመሩ፤ በዚህም ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሱት አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች በሳንቲሞቹ መጠቀም ጀመሩ።

ይሁንና ሳንቲሞች የሚዘጋጁት እንዴት ነበር? የብረት ሠራተኛው የቀለጠውን ብረት ከእቶን እሳት ላይ አንስቶ (1) በቅርጽ ማውጫ ላይ ያፈስሰውና ክብ ቅርጽ ያላቸው ልሙጥ ሳንቲሞች ተቀጣጥለው ይወጣሉ (2)። ከዚያም እነዚህን ልሙጥ ሳንቲሞች አርማ ወይም ምስል በተቀረጸባቸው ሁለት ማተሚያ ብረቶች መሃል ያስገባቸዋል (3)። ቀጥሎም ምስሎቹ በሳንቲሞቹ ላይ እንዲቀረጹ ለማድረግ ማተሚያ ብረቱን በመዶሻ ይመታዋል (4)። በፍጥነት ለመሥራት የሚደረገው ጥረት አብዛኛውን ጊዜ ምስሎቹ በሳንቲሞቹ መሃል ለመሃል እንዳያርፉ ያደርግ ነበር። የብረት ሠራተኞቹ ሳንቲሞቹን ከለዩ በኋላ ክብደታቸው እኩል መሆኑን ለማረጋገጥ ይመዝኗቸዋል፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ከሚዛን ያለፉትን ሳንቲሞች ከርክመው ያስተካክሏቸዋል (5)

ገንዘብ ለዋጮች፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ባለ ባንኮች

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ሰዎች የብዙ አገር ሳንቲሞችን ይዘው ወደ ፓለስቲና ይመጡ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚመጡ ሰዎች የውጭ አገር ሳንቲሞችን ይዘው ይመጡ ነበር። ይሁን እንጂ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች የቤተ መቅደሱን ግብር ሲሰበስቡ የሚቀበሉት የተወሰኑ የሳንቲም ዓይነቶችን ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት ገንዘብ ለዋጮች በቤተ መቅደሱ ውስጥ የራሳቸውን ንግድ አቋቁመው የነበረ ሲሆን ብዙውን ጊዜም የውጭ አገር ሳንቲሞችን ተቀባይነት ባለው ገንዘብ ለመለወጥ ከመጠን ያለፈ ክፍያ ይጠይቁ ነበር። ኢየሱስ እነዚህን ስግብግብ ሰዎች አውግዟቸዋል። ለምን? ምክንያቱም የይሖዋን ቤት “የንግድ ቤት” እና “የወንበዴዎች ዋሻ” አድርገውት ነበር።​—ዮሐንስ 2:13-16፤ ማቴዎስ 21:12, 13

የፓለስቲና ነዋሪዎች የተለያዩ የመንግሥት ግብሮችንና ቀረጦችንም መክፈል ነበረባቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የኢየሱስ ተቃዋሚዎች እሱን ለማጥመድ ሲሉ ጠይቀውት የነበረው ‘የግብር’ ዓይነት ነው። (ማቴዎስ 22:17) ሌሎቹ ደግሞ የመንገድ ቀረጥ እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ በሚገቡም ሆነ ወደ ውጪ በሚላኩ ሸቀጦች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ናቸው። በፓለስቲና ምድር የሚኖሩ የመንግሥት ቀረጥ ሰብሳቢዎች በማጭበርበር ተግባራቸው ስለሚታወቁ ሕዝቡ ይጠላቸው ነበር። (ማርቆስ 2:16) ቀረጥ ሰብሳቢዎቹ ከተገቢው በላይ ክፍያ በመጠየቅና ትርፉን ለራሳቸው በመውሰድ ሀብት ያጋብሱ ነበር። ይሁን እንጂ እንደ ዘኬዎስ ያሉ አንዳንድ ቀረጥ ሰብሳቢዎች ኢየሱስ ለሰበከው መልእክት ምላሽ በመስጠት የማጭበርበር ተግባራቸውን ትተዋል። (ሉቃስ 19:1-10) በዛሬው ጊዜም ክርስቶስን መከተል የሚፈልጉ ሁሉ ከንግድ ጋር በተያያዘም ሆነ በሌላ በማንኛውም ነገር ሐቀኛ መሆን አለባቸው።​—ዕብራውያን 13:18

ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ሥራ በመሥራት የሚታወቁት ሌሎቹ ደግሞ ባለ ባንኮች ናቸው። እነሱም የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የቁጠባ ሥርዓቶችን ይዘረጉ፣ ብድር ይሰጡና በባንኩ ውስጥ ገንዘብ ላስቀመጡ ሰዎች ወለድ ይከፍሉ ነበር። ኢየሱስ ነግደው እንዲያተርፉበት የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ስለተሰጣቸው ባሪያዎች በተናገረው ምሳሌ ላይ ስለ እነዚህ ባለ ባንኮች ጠቅሷል።​—ማቴዎስ 25:26, 27 የ1980 ትርጉም

ለገንዘብ ተገቢ አመለካከት መያዝ

በዛሬው ጊዜ ባሉት አብዛኞቹ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለመግዛት የግድ ገንዘብ ማግኘት አለባቸው። በብዙ መቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት አምላክ ንጉሥ ሰለሞንን በመንፈሱ በመምራት ያስጻፈው ‘ገንዘብ ጥላ ከለላ ነው’ የሚለው ሐሳብ አሁንም ድረስ እውነት ነው። ይሁን እንጂ ሰለሞን አክሎ ‘ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ስለምትጠብቅ’ ከገንዘብ ይልቅ ብልጫ እንዳላት ጽፏል። (መክብብ 7:12) እንዲህ ዓይነቱ ጥበብ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው።

ኢየሱስ ለተከታዮቹ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ ስላልሆነ ተጠንቀቁ፤ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” ብሎ በመናገር ስለ ገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል። (ሉቃስ 12:15) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሁሉ እኛም ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ኃላፊነት የሚሰማንና ሐቀኞች ከሆንን አልፎ ተርፎም ለገንዘብ ፍቅር እንዳያድርብን የምንጠነቀቅ ከሆነ ጥበበኞች እንደሆንን እናሳያለን።​—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

[የግርጌ ማስታወሻ]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕሎች]

 ሳንቲሞችን የተመለከተ መረጃ

● በመጀመሪያው መቶ ዘመን በፓለስቲና ከሚሠራባቸው የመጨረሻ ትንሽ ከሚባሉት ሳንቲሞች አንዱ የመዳብ ሌፕተን ነበር። አንድ የቀን ሠራተኛ ለ15 ደቂቃ ሥራ የሚከፈለው ሁለት ሌፕተኖች ነበር። ኢየሱስ፣ መበለቲቱ በቤተ መቅደሱ የመዋጮ ዕቃ ውስጥ ስትጥል ያያት ሁለት ሌፕተኖች ሳይሆን አይቀርም።​—ማርቆስ 12:42

የብር ድራክማ የግሪክ ሳንቲም ሲሆን ለቀን ሠራተኞች የሚከፈል የአንድ ቀን ደሞዝ ነበር። (ሉቃስ 15:8, 9 የግርጌ ማስታወሻ) ሁሉም አይሁዳውያን ወንዶች ለቤተ መቅደሱ ግብር በየዓመቱ የሚከፍሉት ሁለት ድራክማ ነበር።​—ማቴዎስ 17:24

የብር ዲናር ደግሞ የቄሳር ምስል ያለበት የሮማውያን ሳንቲም ነበር፤ በመሆኑም በሮማውያን ቅኝ ግዛት ወቅት ለአቅመ አዳም የደረሱ አይሁዳውያን ወንዶች በሙሉ “ግብር” የሚከፍሉት በዲናር መሆኑ ምንም አያስገርምም። (ማቴዎስ 22:19) አንድ አሠሪ በቀን ውስጥ 12 ሰዓት ለሠራ የቀን ሠራተኛ የሚከፍለው አንድ ዲናር ነበር።​—ማቴዎስ 20:2-14

● በጢሮስ ከተማ የሚሠራው ንጹሕ የብር ሰቅል ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት በፓለስቲና ጥቅም ላይ ይውል ነበር። የአስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ በመስጠቱ ሊቀ ካህናቱ የከፈለው 30 “የብር ሳንቲሞች” የጢሮስ ሰቅል ሊሆኑ ይችላሉ።​—ማቴዎስ 26:14-16

የሳንቲሞቹ ፎቶ ትክክለኛ መጠናቸውን የሚያሳይ ነው