በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትንቢት 4. የተፈጥሯዊ ፍቅር መጥፋት

ትንቢት 4. የተፈጥሯዊ ፍቅር መጥፋት

ትንቢት 4. የተፈጥሯዊ ፍቅር መጥፋት

‘ሰዎች ለቤተሰባቸው ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው ይሆናሉ።’​—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3 ጎድስ ዎርድ ባይብል

● ክሪስ የሚሠራው በቤት ውስጥ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች በሚረዳ በሰሜናዊ ዌልስ የሚገኝ አንድ ማኅበር ውስጥ ነው። “ከዚህ በፊት የማውቃት አንዲት ሴት ማንነቷን መለየት እስኪያቅተኝ ድረስ ክፉኛ ተደብድባ ስትመጣ ትዝ ይለኛል” በማለት ክሪስ ይናገራል። “ሌሎች ሴቶች ደግሞ ከፍተኛ የስሜት ጉዳት ስለደረሰባቸው ቀና ብለው ማየት እንኳ ይፈራሉ።”

እውነታው ምን ያሳያል? በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ ከ3 ሴቶች መካከል 1ዷ በልጅነቷ የፆታ ጥቃት እንደተፈጸመባት ይገመታል።በዚያች አገር የተካሄደ አንድ ጥናት ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ወንዶች ሚስቶቻቸውን መደብደብ ምንም እንደማይመስላቸው ደርሶበታል። ይሁንና በቤት ውስጥ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሴቶች ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ በካናዳ ከ10 ወንዶች መካከል 3ቱ በትዳር ጓደኞቻቸው ተደብድበዋል ወይም ሌላ ዓይነት ጥቃት ደርሶባቸዋል።

በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው የተቃውሞ ሐሳብ ምንድን ነው? በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት ምንጊዜም ያለ ነገር ነው። አሁን የበዛ የመሰለው ከቀድሞ የበለጠ ትኩረት ስለተሰጠው ብቻ ነው።

ይህ የተቃውሞ ሐሳብ ትክክል ነው? በቤት ውስጥ ለሚፈጸም ጥቃት የሚሰጠው ትኩረት ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ መጨመሩ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ለችግሩ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑ በቤት ውስጥ የሚፈጸመው ጥቃት ቁጥሩ እየቀነሰ እንዲሄድ አድርጎታል? በጭራሽ አላደረገውም። እንዲያውም ከምንጊዜውም የበለጠ ተፈጥሯዊ ፍቅር እየጠፋ መጥቷል።

ምን ይመስልሃል? ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1-3 በመፈጸም ላይ እንደሆነ ይሰማሃል? ብዙ ሰዎች በተፈጥሮ ሊኖራቸው የሚገባውን ቤተሰባዊ ፍቅር እንዳጡ ይሰማሃል?

በአሁኑ ጊዜ ሲፈጸም እያየህ ያለኸው አምስተኛው ትንቢት መኖሪያችን የሆነችውን ምድርን የሚመለከት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን እንደሚል ልብ በል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት በማኅበረሰቡ ውስጥ በብዛት ይፋ ከማይወጡ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይታመናል። አንዲት ሴት ለፖሊስ ቀርባ ከማመልከቷ በፊት በትዳር ጓደኛዋ በአማካይ 35 ጊዜ ትደበደባለች።”​—በዌልስ የሚገኘው የቤት ውስጥ ጥቃት ለደረሰባቸው በስልክ የምክር አገልግሎት የሚሰጠው ተቋም ቃል አቀባይ