ትንቢት 5. የምድር መበላሸት
ትንቢት 5. የምድር መበላሸት
‘አምላክ ምድርን እያጠፉ ያሉትን ያጠፋል።’—ራእይ 11:18
● በክፖር፣ ናይጄሪያ ውስጥ የሚኖረው ሚስተር ፒሪ ከዘንባባ የሚገኝ ወይን ጠጅ በማምረት ተግባር የተሰማራ ነው። በናይጀር ደለል ውስጥ በፈሰሰው ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ዘይት የተነሳ የሚስተር ፒሪ ሥራ ኪሳራ ደርሶበታል። “ነዳጅ ዘይቱ ዓሦቻችንን ፈጅቶብናል፤ ቆዳችንን አበላሽቶብናል፤ ጅረቶቻችንን በክሎብናል” በማለት ሚስተር ፒሪ ተናግሯል። “ሌላ ምንም መተዳደሪያ የለኝም።”
እውነታው ምን ያሳያል? አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ በየዓመቱ 6.5 ሚሊዮን ቶን ቆሻሻ ወደ ውቅያኖሶች ይገባል። ከዚህ ቆሻሻ ውስጥ 50 በመቶ ገደማ የሚሆነው ፕላስቲክ ሲሆን ፕላስቲክ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከመበስበሱ በፊት ለብዙ መቶ ዓመታት ተንሳፍፎ ሊቆይ ይችላል። ሰዎች ምድርን ከመበከላቸውም በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብቷን አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነት እየጨረሱት ነው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ምድራችን፣ ሰዎች በአንድ ዓመት ውስጥ የሚፈጁትን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ አንድ ዓመት ከአምስት ወር ይፈጅባታል። “የዓለም ሕዝብ ቁጥርና የተፈጥሮ ሀብት ፍጆታ እየጨመረ የመምጣቱ ሂደት በዚሁ ከቀጠለ በ2035 ከምድራችን ጋር የሚመጣጠኑ ሁለት ፕላኔቶች ያስፈልጉናል” በማለት ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ የተሰኘው የአውስትራሊያ ጋዜጣ ዘግቧል።
በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው የተቃውሞ ሐሳብ ምንድን ነው? የሰው ልጆች ብልሃተኞች ስለሆኑ መላ አያጡም። አሁን ያሉትን ችግሮች ማስወገድና ምድርን መታደግ እንችላለን።
ይህ የተቃውሞ ሐሳብ ትክክል ነው? በግለሰብም ይሁን በቡድን ደረጃ ብዙዎች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰዎች ስለ አካባቢ መበከል ያላቸው ግንዛቤ ከፍ እንዲል አድርገዋል። ምድር ግን አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየተበከለች ነው።
ምን ይመስልሃል? በቃሉ ላይ በሠፈረው ተስፋ መሠረት አምላክ ጣልቃ በመግባት ፕላኔታችንን ከጥፋት መታደጉ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል?
እስካሁን ከተመለከትናቸው አምስት ትንቢቶች በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ደስ የሚያሰኙ ክንውኖችም እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮአል። በስድስተኛ ደረጃ የተገለጸውን ትንቢት እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ትንሿን ገነቴን ተቀምቼ መርዛማ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ እንደተረከብኩ ሆኖ ይሰማኛል።”—በዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ጠረፍ አካባቢ የሚኖሩት ኤሪን ታምበር የተባሉ ሴት በ2010 በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ላይ ነዳጅ ዘይት መፍሰሱ የፈጠረባቸውን ስጋት አስመልክተው የሰጡት አስተያየት
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተጠያቂው አምላክ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ የምናያቸውን መጥፎ ሁኔታዎች አስቀድሞ መተንበዩ አምላክን ተጠያቂ ያደርገዋል? መከራና ሥቃይ እንዲደርስብን የሚያደርገው እሱ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 11ን ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
U.S. Coast Guard photo