በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለድሆች የሚሆን ምሥራች

ለድሆች የሚሆን ምሥራች

ለድሆች የሚሆን ምሥራች

የአምላክ ቃል “ድሀ ለዘላለም አይረሳም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጣል። (መዝሙር 9:18 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪያችን ሲናገር “አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ” ይላል። (መዝሙር 145:16) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ይህ ተስፋ እንዲያው የሕልም እንጀራ አይደለም። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ድህነትን ለማስወገድ የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰድ ይችላል። ታዲያ ድሆች የሚያስፈልጋቸው ምንድን ነው?

አንዲት አፍሪካዊ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ድሃ አገራት የሚያስፈልጋቸው “ደግ የሆነ ቆራጥ መሪ” መሆኑን ገልጸዋል። እኚህ ባለሙያ ይህን ሲሉ ድህነትን ለማስወገድ ከተፈለገ በአንድ በኩል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ኃይል ያለው በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን የደግነትን ባሕርይ የተላበሰ መሪ ያስፈልጋል ማለታቸው ነው። እሳቸው ያሉት እንዳለ ሆኖ መሪው ድህነትን ከምድረ ገጽ እንዲያጠፋ ከተፈለገ መላዋን ምድር የሚያስተዳድር መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ አስከፊ ለሆነ ድህነት መንስኤው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆችን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት አለመኖሩ ነው። በተጨማሪም ይህ መሪ ድህነትን እንዲያጠፋ ከተፈለገ ለድህነት መንስኤ የሆነውን ነገር ማለትም በሰው ልጆች ላይ የሚታየውን የራስ ወዳድነት ባሕርይ ማስወገድ የሚችል መሆን አለበት። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ብቃት ያለው መሪ ማግኘት ይቻላል?

ኢየሱስ ከአምላክ ዘንድ ለድሆች የሚሆን ምሥራች ይዞ መጥቶ ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ በፊቱ ለተሰበሰቡት ሰዎች አምላክ ስለሰጠው ተልእኮ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲያነብ እንዲህ አለ፦ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ምሥራች እንዳውጅ ቀብቶኛል።”​—ሉቃስ 4:16-18

ምሥራቹ ምንድን ነው?

አምላክ ኢየሱስን ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። በእርግጥም ይህ ምሥራች ነው። ኢየሱስ ድህነትን ለማጥፋት የሚያስችል ብቃት ያለው መሪ ነው፤ ምክንያቱም (1) የሚገዛው መላውን የሰው ዘር ከመሆኑም በላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ኃይል አለው፤ (2) ለድሆች በመራራት እርምጃ ይወስዳል እንዲሁም ተከታዮቹ ለድሆች የሚያስቡ እንዲሆኑ አስተምሯል እንዲሁም (3) የድህነትን መንስኤ ይኸውም ከአዳም የወረስነውን የራስ ወዳድነት ዝንባሌ የማስወገድ ችሎታ አለው። እስቲ እነዚህን ሦስት የምሥራቹ ገጽታዎች አንድ በአንድ እንመልከት።

1. ኢየሱስ በሕዝቦች ሁሉ ላይ ሥልጣን አለው። የአምላክ ቃል ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ሥልጣን . . . ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት” ይላል። (ዳንኤል 7:14) መላው የሰው ዘር በአንድ መንግሥት ሥር መተዳደሩ ምን ያህል ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል መገመት ትችላለህ? በምድር የተፈጥሮ ሀብት ላይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት የሚጋጭና አምባጓሮ የሚፈጥር አይኖርም። ሁሉም ሰው ከምድር ሀብት እኩል ተጠቃሚ ይሆናል። ኢየሱስ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ኃይል ያለው የዓለም መሪ እንደሚሆን ማረጋገጫ ሲሰጥ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ብሎ ነበር።​—ማቴዎስ 28:18

2. ኢየሱስ ለድሆች ይራራል። ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በርኅራኄ ተገፋፍቶ ድሆችን ለመርዳት አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል። ለምሳሌ ያህል፣ ያላትን ጥሪት ሁሉ በሕክምና የጨረሰች አንዲት ሴት እንደምትፈወስ ተስፋ በማድረግ የኢየሱስን ልብስ ነካች። ለ12 ዓመታት ያህል ደም ሲፈስሳት ስለነበር ከፍተኛ በሆነ የደም ማነስ ችግር ትሠቃይ እንደነበር ጥርጥር የለውም። በሕጉ መሠረት እሷ የምትነካው ሰው ሁሉ ይረክሳል። ይሁንና ኢየሱስ ለዚህች ሴት ደግነት አሳይቷታል። “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፣ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም እረፊ” አላት።​—ማርቆስ 5:25-34

የኢየሱስ ትምህርቶች የሰዎችን ልብ የመለወጥ ኃይል ስላላቸው ትምህርቶቹን የሚሰሙ ሰዎች እንደ ኢየሱስ የርኅራኄ ተግባር ለመፈጸም ይነሳሳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክን ማስደሰት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ለጠየቀው አንድ ሰው ኢየሱስ የሰጠውን መልስ ተመልከት። ሰውየው አምላክ ባልንጀራችንን እንድንወድ የሚፈልግ መሆኑን ያውቃል፤ ያም ሆኖ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው።

ኢየሱስ ለዚህ ሰው መልስ ሲሰጥ፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲጓዝ ወንበዴዎች ከዘረፉት በኋላ “በሕይወትና በሞት መካከል” ጥለውት ስለሄዱት ሰው የሚገልጸውን ታዋቂ ምሳሌ ተናገረ። አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲወርድ ሰውየውን አየውና ገለል ብሎ አልፎት ሄደ። አንድ ሌዋዊም ሲያየው ተመሳሳይ ነገር አደረገ። “ሆኖም አንድ ሳምራዊ በዚያ መንገድ ሲጓዝ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ በጣም አዘነለት።” ከዚያም ቁስሉን ከጠራረገለት በኋላ ወደ እንግዶች ማረፊያ በመውሰድ የማረፊያ ቤቱ ባለቤት እንዲያስታምመው ገንዘብ ከፈለለት። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ ጥያቄ አቅርቦለት የነበረውን ሰው “በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ ሆኖ የተገኘው የትኛው ይመስልሃል?” አለው። እሱም “ምሕረት በማሳየት የረዳው ነው” በማለት መለሰ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።​—ሉቃስ 10:25-37

አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር በሚሆንበት ጊዜ ኢየሱስ ያስተማራቸውን እንዲህ የመሰሉ ትምህርቶች ስለሚያጠና በችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን ስለመርዳት ያለው አመለካከት ይለወጣል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ላቲቪያዊት ደራሲ ዊሜን ኢን ሶቪየት ፕሪዝንስ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ በፖትማ የሴቶች እስር ቤት ውስጥ በሥራ ላይ እያሉ ስላጋጠማቸው ሕመም ጽፈው ነበር። “ታምሜ በነበርኩበት ወቅት [የይሖዋ ምሥክሮቹ] ሳይታክቱ አስታምመውኛል። ከዚያ የበለጠ እንክብካቤ ከየትም ማግኘት አልችልም ነበር” ብለዋል። አክለውም “የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ሰው ሃይማኖቱም ሆነ ዜግነቱ ምንም ይሁን ምን ሁሉንም ሰው መርዳት ግዴታቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል” ብለዋል።

ኢኳዶር ውስጥ የኢኮኖሚ ውድቀት በተከሰተበት ጊዜ አንኮን በተባለች ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የገቢ ምንጫቸው ተቋርጦ ነበር፤ በዚህ ጊዜ የእምነት ባልንጀሮቻቸው እነሱን ለመርዳት ገንዘብ የሚያሰባስቡበትን መንገድ ቀየሱ፤ በዚህም መሠረት ሌሊት ዓሣ ሲያጠምዱ አድረው ለሚመለሱ ሰዎች ምግብ አዘጋጅተው መሸጥ ጀመሩ (በስተቀኝ የሚታዩት)። ልጆች ሳይቀሩ ሁሉም የጉባኤው አባላት በዚህ ሥራ ተባበሩ። ጀልባዎቹ የሚመለሱት ሌሊት አሥር ሰዓት ላይ ስለሆነ በዚህ ጊዜ ምግቡን ለማድረስ በየቀኑ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ጀምረው ይሠሩ ነበር። ከሽያጩ የተገኘው ገንዘብ የእያንዳንዱን ወንድም ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ለሁሉም ተከፋፈለ።

እንዲህ የመሰሉ ተሞክሮዎች ኢየሱስ የተወው ምሳሌና ያስተማራቸው ትምህርቶች ሰዎች በችግር ላይ የወደቁትን ስለመርዳት ያላቸውን አመለካከት የመለወጥ ከፍተኛ ኃይል እንዳላቸው ያሳያሉ።

3. ኢየሱስ ከአዳም የወረስናቸውን መጥፎ ዝንባሌዎች የማስወገድ ኃይል አለው። ሰዎች የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ያላቸው መሆኑን ማንም የማይክደው ሐቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ዝንባሌ ኃጢአት ብሎ ይጠራዋል። ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው” በማለት ጽፎ ነበር። አክሎም “እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” ብሏል። (ሮም 7:21-25) ጳውሎስ ይህን ሲል አምላክ ለድህነት ዋነኛ መንስኤ የሆነውን ራስ ወዳድነትን ጨምሮ ከአዳም ከወረስናቸው የኃጢአት ዝንባሌዎች እውነተኛ አገልጋዮቹን እንዴት በኢየሱስ በኩል እንደሚታደግ መጥቀሱ ነበር። ይህ የሚፈጸመው እንዴት ነው?

መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ከተጠመቀ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ እሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!” (ዮሐንስ 1:29) በቅርቡ ምድር የራስ ወዳድነት ዝንባሌን ጨምሮ ከአዳም ከወረሱት ኃጢአት ነፃ በወጡ ሰዎች ትሞላለች። (ኢሳይያስ 11:9) በእርግጥም ኢየሱስ የድህነት መንስኤ የሆነውን ነገር ያስወግዳል።

ሁሉም ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ስለሚያገኝበት ስለዚያ ጊዜ ማሰብ እንዴት ያስደስታል! የአምላክ ቃል “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም” በማለት ይናገራል። (ሚክያስ 4:4) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ሁሉም ሰው የደኅንነት ስሜት ተሰምቶትና አርኪ ሥራ አግኝቶ እንዲሁም ከድህነት ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ተደስቶ የሚኖርበትን ጊዜ ውብ በሆነ መንገድ ይገልጻል፤ ይህ ደግሞ ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል።