በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታማኝ ክርስቲያኖች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

ታማኝ ክርስቲያኖች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ታማኝ ክርስቲያኖች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

▪ ብዙ ሰዎች “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል” የሚሉትን ኢየሱስ የተናገራቸውን የሚያጽናኑ ቃላት አንብበዋል። (ዮሐንስ 3:16) ታዲያ ኢየሱስ እንዲህ ሲል አባቱን ይሖዋ አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ ሰዎች በሙሉ እውነተኛ ደስታ አግኝተው ለዘላለም ለመኖር ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ መናገሩ ነበር?

ኢየሱስ “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” የሚል ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:13) ይህ ሐሳብ እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴና ዳዊት ያሉ በጥንት ጊዜ የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ወደ ሰማይ እንዳልሄዱ ይጠቁማል። (የሐዋርያት ሥራ 2:34) ታዲያ እነዚህ ሁሉ ሰዎች የሄዱት ወዴት ነው? በአጭሩ፣ በጥንት ጊዜ የነበሩ ታማኝ ሰዎች በመቃብር ውስጥ ናቸው፤ እነዚህ ሰዎች በሞት ያንቀላፉ ሲሆን ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፤ እንዲሁም ትንሣኤ እስከሚያገኙበት ጊዜ ድረስ በመቃብር ውስጥ ይቆያሉ።​—መክብብ 9:5, 6፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሞት ተነስቶ ሰማያዊ ሕይወት ማግኘት እንደሚቻል ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረውም ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ በሰማይ ቦታ እንደሚያዘጋጅላቸው ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 14:2, 3) ይህ ለአምላክ ሕዝቦች አዲስ ነገር ነበር። ቆየት ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ‘ለደቀ መዛሙርቱ አዲስና ሕያው መንገድ’ ማለትም ከዚህ በፊት ማንም ሰው ሄዶበት የማያውቅ መንገድ ‘እንደከፈተላቸው’ ተናግሯል።​—ዕብራውያን 10:19, 20

ታዲያ እንዲህ ሲባል ከዚያ ጊዜ አንስቶ ታማኝ ሰዎች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ማለት ነው? በፍጹም፤ ምክንያቱም ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት ለየት ያለ የሥራ ድርሻ የተሰጣቸው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ በሰማይ ባለው መንግሥቱ ‘ዙፋን ላይ ተቀምጠው እንደሚፈርዱ’ ለሐዋርያቱ ነግሯቸው ነበር። በመሆኑም የእነዚህ ሰዎች የሥራ ድርሻ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር መግዛት ነው።​—ሉቃስ 22:28-30

ከሐዋርያቱ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችም አስደናቂ የሆነው ይህ የሥራ ድርሻ ይሰጣቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስን ‘መንግሥትና ካህናት ሆነው በምድር ላይ እንደሚገዙ’ ከተነገረላቸው ከሞት የተነሱ በርካታ ሰዎች ጋር በሰማይ ሆኖ በራእይ ተመልክቶታል። (ራእይ 3:21፤ 5:10) እዚያ የነበሩት ምን ያህል ሰዎች ናቸው? በየትኛውም መንግሥት ውስጥ ቢሆን አስተዳዳሪ የሚሆኑት የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። በሰማይ ከሚገኘው መንግሥት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የአምላክ በግ የሆነው ኢየሱስ ‘ከሰዎች መካከል ከተዋጁት’ 144,000 ተባባሪ ገዢዎች ጋር ሆኖ ይገዛል።​—ራእይ 14:1, 4, 5

እርግጥ ነው፣ በጥንት ጊዜ ከነበሩትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ካሉት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ቁጥር አንጻር ሲታይ 144,000 በጣም ትንሽ ቁጥር ነው። ይሁንና 144,000ዎቹ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት ለየት ያለ ቅዱስ ሥራ ለማከናወን ስለሆነ ቁጥራቸው ማነሱ ምክንያታዊ ነው። አንድ ቤት ለመሥራት ብትፈልግ በአካባቢህ ያሉትን የግንባታ ሙያ ያላቸውን ሰዎች በሙሉ ትቀጥራለህ? እንደዚያ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። የምትቀጥረው ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልጉትን ያህል ብቻ ነው። በተመሳሳይም አምላክ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ልዩ መብት እንዲያገኙ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን በሙሉ አልመረጠም።

በሰማይ የሚገኘው ይህ መንግሥት አምላክ መጀመሪያ ላይ ለሰው ልጆች ያወጣውን ዓላማ ከዳር ያደርሳል። ኢየሱስና 144,000ዎቹ ተባባሪ ገዥዎች መላዋ ምድር ስፍር ቁጥር የሌላቸው ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ለዘላለም በደስታ የሚኖሩባት ገነት እንድትሆን የማድረጉን ሥራ በበላይነት ይቆጣጠራሉ። (ኢሳይያስ 45:18፤ ራእይ 21:3, 4) ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ከሚኖሩት መካከል አምላክ የሚያስባቸው ሰዎች ይኸውም ከሞት የሚነሱ ሰዎች ይገኙበታል።​—ዮሐንስ 5:28, 29

በጥንት ጊዜ የነበሩም ሆኑ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ አስደናቂ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ያገኛሉ። (ሮም 6:23) ጥቂት ሰዎች ለየት ያለ ሥራ ለማከናወን ወደ ሰማይ ሲሄዱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሰዎች ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር መብት ያገኛሉ።