ሕይወትን ትርጉም የለሽ እንዲመስል ያደረገው ምንድን ነው?
ሕይወትን ትርጉም የለሽ እንዲመስል ያደረገው ምንድን ነው?
ንጉሥ ሰሎሞን ሕይወት ‘እንደ ጥላ የሚያልፍ አጭርና ባዶ ሕልውና ነው’ በማለት የገለጸው ዓይነት ሆኖ እንደማይቀር ማመን የሚኖርብህ ለምንድን ነው? (መክብብ 6:12 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) አምላክ በመንፈሱ መሪነት ያጻፈውና አስተማማኝ የሆነ መረጃ የያዘው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት ወደፊት ትርጉም ያለው እንደሚሆን ተስፋ ይሰጣል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ምን እንደሆነ ይነግረናል። በተጨማሪም በዓለም ላይ የፍትሕ መዛባት፣ ጭቆናና መከራ የበዛው ለምን እንደሆነ ይገልጻል። ስለ እነዚህ ነገሮች ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰዎች፣ ሕይወት ምንም ዓይነት ትርጉም እንደሌለው አድርገው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ዋነኛው ነገር አምላክ ለዚህች ፕላኔትና በላይዋ ለሚኖረው የሰው ዘር ያለውን ዓላማ አለማወቃቸው ወይም ለማወቅ አለመፈለጋቸው ነው።
አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
ይሖዋ አምላክ * ምድርን የሠራት ለሰው ልጅ መኖሪያነት ፍጹም ተስማሚ የሆነች ገነት ማለትም ወንዶችና ሴቶች ምንም የሚጎድላቸው ነገር ሳይኖር ፍጽምናን ተላብሰው ለዘላለም አርኪ ሕይወት የሚኖሩባት ቦታ እንድትሆን ነበር። ይህ መሠረታዊ እውነት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ካገኘውና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ከሌለው ሐሳብ ጋር ይኸውም አምላክ ምድርን የሠራት ሰዎች ወደ አንድ መንፈሳዊ ዓለም ተሻግረው ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ የመፈተኛ ቦታ እንድትሆን ነው ከሚለው አመለካከት ጋር ይጋጫል።— “ትርጉም ያለው ሕይወት ለማጣጣም ምድርን ትተን መሄድ አለብን?” የሚለውን በገጽ 6 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
አምላክ ወንድንና ሴትን የእሱን ድንቅ ባሕርያት የማንፀባረቅ ችሎታ እንዲኖራቸው በማድረግ በአምሳሉ ሠርቷቸዋል። (ዘፍጥረት 1:26, 27) የሠራቸው ፍጹም አድርጎ ነበር። ለዘላለም ደስተኛ የሆነና ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ተሟልቶላቸው ነበር። ይህ ደግሞ ምድርን መሙላትንና መግዛትን ይኸውም መላዋን ፕላኔት በኤደን የነበረችውን የአትክልት ስፍራ ወደምትመስል ገነት መለወጥን ይጨምር ነበር።—ዘፍጥረት 1:28-31፤ 2:8, 9
ታዲያ ምን ችግር ተፈጠረ?
በዛሬው ጊዜ ያለው ሁኔታ በግልጽ እንደሚያሳየው አንድ የተፈጠረ ችግር አለ። በጥቅሉ ሲታይ የሰው ዘር የአምላክን ባሕርይ ማንጸባረቅ ተስኖታል። ምድርም ቢሆን ገነት አልሆነችም። ምን ተከስቶ ይሆን? የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነታቸውን አላግባብ ተጠቀሙበት። ከሥነ ምግባር አንፃር “መልካምና ክፉ” የሆነውን ነገር ለራሳቸው በመወሰን “እንደ እግዚአብሔር” መሆን ፈለጉ። እንዲህ በማድረግ ቀደም ሲል ሰይጣን ዲያብሎስ የመረጠውን የዓመፅ ጎዳና ተከተሉ።—ዘፍጥረት 3:1-6
በመሆኑም ክፋት በአምላክ እቅድ ውስጥ አስቀድሞ የነበረና ለጊዜው ሚስጥር የሆነ ነገር አልነበረም። ክፋት የጀመረው ሰይጣን በኋላም አዳምና ሔዋን በአምላክ አገዛዝ ላይ ባመፁ ጊዜ ነው። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በማመፃቸው ምክንያት ከገነት የተባረሩ ሲሆን ፍጽምናን አጡ፤ በዚህም የተነሳ ኃጢአትንና ሞትን በራሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በዘሮቻቸውም ላይ ማለትም በመላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ላይ አመጡ። (ዘፍጥረት 3:17-19፤ ሮም 5:12) ይህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ሕይወት ትርጉም የለሽ እንዲመስል ያደረጉትን ሁኔታዎች አስከትሏል።
አምላክ ክፋትን ወዲያውኑ ያላስወገደው ለምንድን ነው?
አንዳንዶች ‘ታዲያ አምላክ ሰይጣንንና ሌሎቹን ዓመፀኞች በማጥፋት ክፋትን ወዲያውኑ ያላስወገደውና ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ ያልጀመረው ለምንድን ነው?’ በማለት ይጠይቃሉ። አምላክ እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ በእርግጥ የጥበብ እርምጃ ይሆን ነበር? አንድ ኃያል መንግሥት ሥልጣኑን የተገዳደሩትን ሰዎች ወዲያውኑ እንዳጠፋ ብትሰማ ምን ይሰማሃል? እንዲህ ዓይነቱ አድራጎት ቀና አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች የሚያሸሽና አንድ መንግሥት ከሥነ ምግባር አኳያ የሚኖረውን ስም የሚያጎድፍ አይሆንም?
በተመሳሳይም አምላክ በዓመፀኞቹ ላይ ወዲያውኑ እርምጃ ላለመውሰድ መርጧል። አገዛዙን በተመለከተ በኤደን የተነሱት አወዛጋቢ ጉዳዮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ ሲል ጊዜ እንዲያልፍ በመፍቀድ የጥበብ እርምጃ ወስዷል።
ክፋት በሙሉ ይወገዳል
ማስታወስ ያለብን ዋነኛ ነገር ቢኖር አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መሆኑን ነው። ይህንንም ያደረገው የእሱን አገዛዝ በመቃወም የተነሱት ዋነኛ አከራካሪ ጉዳዮች ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ካገኙ በኋላ በዓመፅ የተነሳ የመጡትን አሳዛኝ መዘዞች ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንደሚችል ስለሚያውቅ ነው።
አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር የነበረው ዓላማ አልተለወጠም። ይሖዋ ምድርን እሱ እንደሠራት እንዲሁም ምድርን ‘የፈጠራት የሰው መኖሪያ እንጂ ባዶ እንድትሆን’ እንዳልሆነ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ኢሳይያስ 45:18) ይሖዋ በመጀመሪያ ዓላማው መሠረት በምድር ላይ ያለው ሁኔታ ፍጹም በሆነ መንገድ እንዲስተካከል ለማድረግ በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። አገዛዙ ትክክል መሆኑ በማያዳግም ሁኔታ ከተረጋገጠ በኋላ አምላክ ዓላማውን ለማስፈጸምና ክፋትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ማንም ሊቋቋመው የማይችለውን ኃይሉን ቢጠቀም ፍትሕ ይሆናል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ አምላክ ይህን እርምጃ እንዲወስድ የቀረበ ልመና ይገኝበታል። ኢየሱስ “ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይህ ምንን ይጨምራል?
አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድ
ከአምላክ ፈቃድ አንዱ ‘ገሮች ምድርን ይወርሳሉ’ የሚለው ነው። (መዝሙር 37:9-11, 29፤ ምሳሌ 2:21, 22) ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እሱ የሚጮኹትን ‘ችግረኞችና ምስኪኖች ይታደጋቸዋል።’ እንዲሁም “ከጭቈናና ከግፍ” ያድናቸዋል። (መዝሙር 72:12-14) ከዚያ በኋላ ጦርነት፣ ሞት፣ እንባ፣ ሐዘን ወይም ሥቃይ አይኖርም። (መዝሙር 46:9፤ ራእይ 21:1-4) አምላክ ክፋትን በታገሠበት ዘመን የሞቱ እጅግ ብዙ ሰዎች፣ በዚህች ምድር ላይ ለመኖር በትንሣኤ ከተነሱ በኋላ ቀደም ሲል የተጠቀሱትንም ሆነ ሌሎች በረከቶችን እንዲያገኙ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29
በተጨማሪም ይሖዋ የሰይጣን ዓመፅ ያስከተለውን ጉዳት በሙሉ ይሽራል። ይህ የመፍትሔ እርምጃ ፍጹም የተሟላ ከመሆኑ የተነሳ ‘ያለፉት ነገሮች [በዛሬው ጊዜ ያለውን ሐዘንና ሥቃይ ያስከተሉት ነገሮች በሙሉ] ይረሳሉ።’ (ኢሳይያስ 65:16-19) ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም የተረጋገጠ ነው። ምክንያቱም አምላክ አይዋሽም። የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ ይፈጸማሉ። ከዚያ በኋላ ሕይወት “ባዶ፣ ነፋስንም እንደ ማሳደድ” አይሆንም። (መክብብ 2:17 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) በዚህ ፈንታ ሕይወት ትርጉም ያለው ይሆናል።
በዛሬው ጊዜስ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ማወቅና አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ መረዳት ሕይወትህ እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል? የዚህ ርዕስ የመጨረሻ ክፍል ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ትርጉም ያለው ሕይወት ለማጣጣም ምድርን ትተን መሄድ አለብን?
አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ የማያውቁ ሰዎች እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት ለማጣጣም ምድርን ትተን መሄድ እንዳለብን ለብዙ መቶ ዓመታት ሲያስተምሩ ኖረዋል።
አንዳንዶች የሰው ነፍስ “ወደ እያንዳንዱ ግለሰብ አካል ውስጥ ከመግባቷ በፊት የላቀ ሕልውና ነበራት” ይላሉ። (ኒው ዲክሽነሪ ኦቭ ቲኦሎጂ) ሌሎች ደግሞ ነፍስ “ወደ ሰው አካል የምትገባው በሰማይ ሳለች ለፈጸመቻቸው ኃጢአቶች ቅጣት ለመቀበል ነው” ብለዋል።—ሳይክሎፒዲያ ኦቭ ቢቢሊካል፣ ቲኦሎጂካል፣ ኤንድ ኤክሊሲያስቲካል ሊትሬቸር
እንደ ሶቅራጥስና ፕላቶ ያሉት የግሪክ ፈላስፎች የሚከተለውን ሐሳብ አስተምረዋል፦ ነፍስ “ከመንከራተት፣ ከከንቱነት፣ ከፍርሃትና መረን ከለቀቀ ምኞቷ እንዲሁም የሰውን ልጅ ከሚያምሱት ሌሎች ሥቃዮች ነፃ” የምትሆነው የአቅም ገደብ ካለበት የሰው አካል ተላቅቃ “ከአማልክት ጋር ለሁልጊዜ” መኖር ስትችል ብቻ ነው።—ፕላቶስ ፋይዶ፣ 81፣ ኤ
ከጊዜ በኋላ ደግሞ ክርስቲያን ነን የሚሉ መሪዎች የግሪክ ፈላስፎች የሚያራምዷቸውን “ነፍስ ስላላት ያለመሞት ባሕርይ የሚገልጹ ግምታዊ ሐሳቦች” በሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ውስጥ አካተቷቸው።—ክርስቲያኒቲ—ኤ ግሎባል ሂስትሪ
እስቲ እነዚህን ሐሳቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ሦስት መሠረታዊ እውነቶች ጋር አወዳድራቸው፦
1. የአምላክ ዓላማ፣ ምድር ለሰው ዘር ቋሚ መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ወደ ሰማይ ሄደው ከእሱ ጋር ለመኖር ብቁ የሆኑ ሰዎች የሚመረጡባት ጊዜያዊ የመፈተኛ ቦታ እንድትሆን አይደለም። አዳምና ሔዋን የአምላክን ሕግ ታዘው ቢሆን ኖሮ ገነት በምትሆነው በዚህች ምድር ላይ እስካሁን ድረስ ይኖሩ ነበር።—ዘፍጥረት 1:27, 28፤ መዝሙር 115:16
2. አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ‘ሰው ነፍስ አለው’ ማለትም ‘በውስጡ የምትኖር ረቂቅ ነገር አለች’ ብለው የሚያስተምሩ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ የተለየ ለመረዳት ቀላል የሆነ ትምህርት ያስተምራል። ሰው “ከምድር ዐፈር” የተሠራ “ሕያው ነፍስ” ነው። (ዘፍጥረት 2:7) መጽሐፍ ቅዱስ ይህች ነፍስ የማትሞት እንደሆነች በጭራሽ አይናገርም። በተቃራኒው ነፍስ ልትገደል ወይም ልትጠፋ አሊያም ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጭ ልትሆን እንደምትችል ይናገራል። (መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4, 20) የመጀመሪያው ነፍስ አዳም በሞተበት ጊዜ ከመፈጠሩ በፊት ወደነበረበት አፈር ተመልሷል። በሌላ አባባል ወደ አለመኖር ተመልሷል ማለት ነው።—ዘፍጥረት 2:17፤ 3:19
3. አምላክ ለሰው ዘር የሰጠው የወደፊት ተስፋ የማትሞት ነፍስ ይዞ ወደ መንፈሳዊው ዓለም መሄድ ሳይሆን ከሞት ተነስቶ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር ነው።—ዳንኤል 12:13፤ ዮሐንስ 11:24-26፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15