በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆች መማር የሚኖርባቸው ምንድን ነው?

ልጆች መማር የሚኖርባቸው ምንድን ነው?

ልጆች መማር የሚኖርባቸው ምንድን ነው?

“ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመምከር ይጠቅማል።”​—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ልጆች ስለ አምላክ እውነቱን መማር ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ይህን እውነት ሊማሩ የሚችሉት ከየት ነው? በዓለም ላይ ታላቅ አክብሮትን ካተረፈው የሃይማኖት መጽሐፍ ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ እንደተላከ ደብዳቤ ነው። አምላክ በዚህ ደብዳቤ ላይ ባሕርያቱን የገለጸ ከመሆኑም በላይ ልጅ አዋቂ ሳይል ለሁሉም ልጆቹ የሚሆኑ ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎችን ሰጥቷል። እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ቁም ነገሮች ውስጥ ጥቂቶቹን ብቻ ተመልከት፤ እንዲሁም ትንንሽ ልጆችም እንኳ ሳይቀር ከእነዚህ ሐሳቦች ምን ትምህርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ልብ በል።

አምላክ ስለ እሱ ምን እንድናውቅ ይፈልጋል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ በስሜም እግዚእ ይሖዋ አልታወቅሁላቸውም።”​ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ አምላክ አካል የሌለውና በሁሉ ቦታ የሚገኝ ኃይል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የራሱ የግል ስም ያለው እውን አካል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‘እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራል፤ ሐሳብንም ሁሉ ያውቃል። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ።’​1 ዜና መዋዕል 28:9

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ አምላክ ትንንሽ ልጆችን ጨምሮ ለሁላችንም ያስብልናል። (መዝሙር 10:14፤ 146:9) ስለ እሱ እንድንማርም ይፈልጋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ። ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ።”​ዘፀአት 22:22-24

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ ትንንሽ ልጆችም እንኳ ሳይቀር የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል። አምላክን ዘወትር ማናገር እንዲሁም ሐሳባችንንና የውስጥ ስሜታችንን ለእሱ መግለጽ እንችላለን።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጡት።”​መዝሙር 78:41

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ ንግግራችንና ድርጊታችን ይሖዋን ሊያስደስተው አሊያም ሊያሳዝነው ይችላል፤ ስለዚህ አንድ ነገር ከመናገራችንም ሆነ ከማድረጋችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል።

ከእኛ የተለዩ ሰዎችን እንዴት መያዝ ይኖርብናል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”​የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ አምላክ ከየትኛውም ዘርና የኑሮ ደረጃ የመጡ ሰዎችን ይቀበላል፤ እኛም ሰዎች ከእኛ የተለየ የቆዳ ቀለም ወይም የፊት ገጽታ ስላላቸው ብቻ አድልዎ ልንፈጽምባቸው አይገባም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁዎች [ሁኑ]፤ . . . ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።”​1 ጴጥሮስ 3:15

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ ስለ ሃይማኖት በምንወያይበት ጊዜ አመለካከታችንን በልበ ሙሉነት መግለጽ ይኖርብናል፤ ሆኖም ይህን የምናደርገው ጠብ በሚያነሳሳ መንገድ መሆን የለበትም። በተጨማሪም ከእኛ የተለየ እምነት ላላቸው ሰዎች አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል።

የቤተሰባችንን አባላት እንዴት መያዝ ይኖርብናል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ልጆች ሆይ፣ በጌታ ዘንድ ደስ የሚያሰኝ ስለሆነ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።”​ቆላስይስ 3:20

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ ልጆች ታዛዦች የሚሆኑ ከሆነ ወላጆቻቸውን እንደሚወዱ ብቻ ሳይሆን አምላክንም ማስደሰት እንደሚፈልጉ ያሳያሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”​ቆላስይስ 3:13

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ የቤተሰባችንን አባላት ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ቅር የሚያሰኝ ነገር ሊያደርጉብን ይችላሉ። ይሁን እንጂ አምላክ እኛን ይቅር እንዲለን የምንፈልግ ከሆነ እኛም ሌሎችን ይቅር ማለትን መማር አለብን።​—ማቴዎስ 6:14, 15

ሐቀኞችና ደጎች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ውሸትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።”​ኤፌሶን 4:25

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ እውነቱን የምንናገር ከሆነ የአምላክን ባሕርይ የምናንጸባርቅ ከመሆኑም በላይ እሱን እናስደስተዋለን። ውሸት መናገርን ልማድ ካደረግን የአምላክ ጠላትና “የውሸት አባት” የሆነውን ዲያብሎስን እንመስላለን።​—ዮሐንስ 8:44፤ ቲቶ 1:2

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ አድርጉላቸው።”​ማቴዎስ 7:12

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት፦ የቤተሰባችንን አባላት እንዲሁም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ የሌሎች ሰዎችን ስሜት፣ ሐሳብና ፍላጎት ከግምት የምናስገባ መሆን ይኖርብናል። እኛ ‘የሌላውን ስሜት የምንረዳ’ በምንሆንበት ጊዜ ሌሎችም እኛን በደግነት ለመያዝ ይበልጥ ሊነሳሱ ይችላሉ።​—1 ጴጥሮስ 3:8፤ ሉቃስ 6:38

እንደ ምሳሌ የተጠቀሱት እስከ አሁን የተመለከትናቸው ሐሳቦች እንደሚያሳዩት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ትምህርቶች ልጆች ሲያድጉ አድናቂዎች፣ ሰው አክባሪዎችና የሌላውን ስሜት የሚረዱ እንዲሆኑ ይረዷቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህን ትምህርቶች ለልጆች ማስተማር የሚኖርበት ማን ነው?