በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ” ናቸው?

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ” ናቸው?

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ” ናቸው?

በ2002 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል፣ ጀርመን ውስጥ የምትገኘው የሊምበርግ ከተማ ጳጳስ፣ ከውርጃ ጋር በተያያዘ ያስተላለፉትን ውሳኔ የሚሽር አንድ ደብዳቤ ጽፈው ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ፖል ለጳጳሱ ያስተላለፉትን ትእዛዝ የከፈቱት “በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ መሠረት የእያንዳንዱን አብያተ ክርስቲያን ደኅንነትና አንድነት” የመከታተል ኃላፊነት እንዳለባቸው በመግለጽ ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ” እንደሆኑ ስለሚታመን የጳጳሱን ውሳኔ የመሻር ሥልጣን እንዳላቸው ተናግረዋል።

በሮማ ካቶሊክ እምነት መሠረት “ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን በሁሉም ሐዋርያት ላይ አለቃ አድርጎ ሾሞታል።” በተጨማሪም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ የሚል ጥብቅ እምነት አላት፦ “ይህንን የሥልጣን ቦታ በመያዝ በቀጣይነት ጴጥሮስን የሚተኩ ሰዎች መኖር እንዳለባቸው ክርስቶስ ደንግጓል፤ ተተኪዎቹ ደግሞ የሮማ ጳጳሳት ናቸው።”​—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ (2003) ጥራዝ 11፣ ገጽ 495-496

እነዚህ አባባሎች እንደ ቀላል የሚታዩ አይደሉም። ታዲያ አንተ እነዚህ አባባሎች ትክክል መሆናቸውን አረጋግጠሃል? ቀጥሎ ለቀረቡት ሦስት ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች እስቲ እንመልከት፦ (1) ጴጥሮስ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ነበር የሚለውን አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ይደግፈዋል? (2) ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳቱ አንዳቸው ሌላውን እየተኩ ስለሚቀጥሉበት ሂደት አመጣጥ ታሪክ ምን ይላል? (3) የጴጥሮስ ተተኪ እንደሆኑ የሚናገሩት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ምግባራቸውና ትምህርታቸው ከጴጥሮስ ሕይወት ጋር ይስማማል?

ጴጥሮስ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ነበር?

ካቶሊኮች ቤተ ክርስቲያናቸው በጴጥሮስ ላይ እንደተመሠረተች ለማስረዳት ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 16:18 ላይ የተናገረውን “አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚች ዐለት ላይ ጉባኤዬን እገነባለሁ” የሚለውን ሐሳብ ለረዥም ጊዜ ሲጠቅሱ ኖረዋል። እንዲያውም እነዚህ ቃላት በሮም በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ጣሪያ ላይ ከሥር በኩል በላቲን ቋንቋ ተቀርጸዋል።

የተከበረ የቤተ ክርስቲያን አባት የነበረው ኦገስቲን ጉባኤው በጴጥሮስ ላይ እንደተመሠረተ በአንድ ወቅት ያምን ነበር። ይሁን እንጂ በሕይወቱ መገባደጃ ላይ፣ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ የተረዳበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ተገንዘቦ ነበር። ሪትራክቴሽንስ በመባል የሚታወቅ አንድ መጽሐፍ ኦገስቲን ቤተ ክርስቲያን ማለትም የክርስቲያን ጉባኤ የተመሠረተው በጴጥሮስ ላይ ሳይሆን በኢየሱስ ላይ ነው የሚል ሐሳብ አቅርቦ እንደነበር ገልጿል። *

እውነት ነው፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ከሌሎቹ ሐዋርያት ይበልጥ ጎላ ተደርጎ ተጠቅሷል። ኢየሱስ ለየት ባሉ ጥቂት አጋጣሚዎች አብረውት እንዲሆኑ ከሐዋርያቱ መካከል ሦስቱን ማለትም ዮሐንስን፣ ያዕቆብንና ጴጥሮስን ነጥሎ ወስዷቸዋል። (ማርቆስ 5:37, 38፤ 9:2፤ 14:33) ጴጥሮስ፣ በመጀመሪያ ለአይሁድና ወደ ይሁዲነት ለተለወጡ ከዚያም ለሳምራውያን በመጨረሻም ለአሕዛብ ወደ አምላክ መንግሥት የሚያስገባውን በር ለመክፈት የተጠቀመባቸውን “የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች” ከኢየሱስ በአደራ ተቀብሏል። (ማቴዎስ 16:19፤ የሐዋርያት ሥራ 2:5, 41፤ 8:14-17፤ 10:45) ጴጥሮስ ቀልጠፍ ያለ ሰው ከመሆኑ አንጻር ሐዋርያቱን ወክሎ የተናገረባቸው ወቅቶች ነበሩ። (የሐዋርያት ሥራ 1:15፤ 2:14) ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች ጴጥሮስን በዘመኑ የነበረው ጉባኤ ራስ ያደርጉታል?

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ “ለተገረዙት ሐዋርያ ሆኖ እንዲያገለግል” ኃላፊነት እንደተሰጠው ጽፎ ነበር። (ገላትያ 2:8) ይሁን እንጂ በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ጳውሎስ ይህን ሲል ጉባኤው በጴጥሮስ አመራር ሥር እንደሆነ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ጴጥሮስ ለአይሁዳውያን እንዲሰብክ የተሰጠውን የሥራ ድርሻ እየገለጸ ነበር።

ምንም እንኳ ጴጥሮስ ትልቅ ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም የጉባኤው ራስ እንደሆነ አድርጎ መናገሩን የሚያሳይ እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱን ወክሎ ውሳኔ እንዳስተላለፈ የሚጠቁም ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ አናገኝም። ጴጥሮስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ራሱን “ሐዋርያ” እንዲሁም “ሽማግሌ” በማለት ከመጥራት በስተቀር ለየት ባለ የማዕረግ ስም አልተጠቀመም።​—1 ጴጥሮስ 1:1፤ 5:1

ስለ ጵጵስና አመጣጥ ታሪክ ምን ይላል?

ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት አንዳቸው ሌላውን የሚተኩበት ሂደት የጀመረው መቼና እንዴት ነበር? አንድ ሰው በእምነት ባልንጀሮቹ ላይ የበላይ ለመሆን መፈለጉ ትክክል እንደሆነ ተደርጎ መታየት የጀመረው ሐዋርያት ገና በሕይወት እያሉ ነበር። ታዲያ ሐዋርያት እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ እንዴት ተመለከቱት?

ሐዋርያው ጴጥሮስ ራሱ፣ በጉባኤው ውስጥ በአመራር ቦታ ላይ የነበሩት ወንዶች ‘የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናቸውን ማሳየት’ እንደሌለባቸው ነግሯቸዋል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ትሕትናን እንደ ልብስ መታጠቅ ነበረባቸው። (1 ጴጥሮስ 5:1-5) ሐዋርያው ጳውሎስም ከጉባኤው መካከል “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች” እንደሚነሱ አስጠንቅቆ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:30) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ አንድ ደብዳቤ ጽፎ የነበረ ሲሆን በደብዳቤው ላይ ዲዮጥራጢስ የተባለን አንድ ደቀ መዝሙር በጥብቅ አውግዞ ነበር። ዮሐንስ ይህን ሰው ያወገዘው ለምን ነበር? አንዱ ምክንያት ዲዮጥራጢስ በጉባኤው ውስጥ “የመሪነት ቦታ መያዝ” የሚፈልግ ሰው ስለነበር ነው። (3 ዮሐንስ 9) ሐዋርያት እንዲህ ያለ ምክር መስጠታቸው ከሌሎች ልቀው መታየት ይፈልጉ የነበሩ ሰዎችን ለጊዜውም ቢሆን ለማገድና ሥልጣን የመያዝ ምኞታቸውን ለመግታት አስችሏል።​—2 ተሰሎንቄ 2:3-8

የመጨረሻው ሐዋርያ ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንዳንድ ግለሰቦች ከሌሎች የላቀ ቦታ መያዝ ጀመሩ። ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቲያኒቲ የተባለው መጽሐፍ “ምናልባትም እስከ ሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ በሮም ውስጥ ‘እንደ ንጉሥ የሚታይ’ አንድም ጳጳስ አልነበረም” በማለት ገልጿል። በሦስተኛው መቶ ዘመን የሮም ጳጳስ ቢያንስ በቤተ ክርስቲያኗ የተወሰኑ ክፍሎች ላይ ራሱን የመጨረሻው ባለሥልጣን አድርጎ ሾመ። * የሮም ጳጳስ ከፍተኛ ሥልጣን አለው የሚለው አባባል ይበልጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ሲባል አንዳንዶች የጴጥሮስ ተተኪዎች ናቸው የሚባሉ ሰዎችን ስም ዝርዝር አዘጋጅተዋል።

ይሁን እንጂ ያዘጋጁት ዝርዝር ለተናገሩት ነገር ድጋፍ የሚሆን አልነበረም። ለምን? አንደኛ፣ በዝርዝሩ ላይ የሰፈሩትን ሰዎች ማንነት በትክክል ማረጋገጥ አይቻልም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ዝርዝሩን ለማዘጋጀት የተነሳሱበት መሠረታዊ ሐሳብ ራሱ የተሳሳተ ነበር። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመጀመሪያውና በሁለተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጁ አንዳንድ ዓለማዊ ጽሑፎች እንደሚጠቁሙት በእርግጥ ጴጥሮስ በሮም ሰብኮ ከነበረም እንኳ በዚያ በሚገኘው ጉባኤ ላይ ራስ እንደነበረ የሚያመለክት ምንም ማስረጃ የለም።

ጴጥሮስ በሮም በሚገኘው ጉባኤ ላይ ራስ እንዳልነበረ የሚያሳየው አንዱ ማስረጃ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ያሰፈረው የስም ዝርዝር ነው። ጳውሎስ በዚህ ዝርዝር ላይ በሮም የነበሩ የበርካታ ክርስቲያኖችን ስም ቢጠቅስም ጴጥሮስን ግን ፈጽሞ አልጠቀሰውም። (ሮም 16:1-23) ጴጥሮስ በሮም በሚገኘው ጉባኤ ላይ ራስ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ ሳይጠቅሰው ይቀር ነበር? በዝርዝሩ ላይ ያላካተተው ረስቶት አሊያም ችላ ብሎት ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል?

በተጨማሪም ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሁለተኛውን ደብዳቤ የጻፈው ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት የመጀመሪያውን ደብዳቤ በጻፈበት ጊዜ አካባቢ እንደነበረ ልብ በል። ጳውሎስ በደብዳቤው ላይ ስለ ሮም ሳይጠቅስ አላለፈም። እንዲያውም ጳውሎስ ሮም ሆኖ ስድስት ደብዳቤዎችን የጻፈ ቢሆንም በአንዱም ውስጥ ጴጥሮስን አልጠቀሰውም።

ጳውሎስ ደብዳቤዎቹን ከጻፈ ከ30 ዓመታት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ ሦስት ደብዳቤዎችንና የራእይን መጽሐፍ ጽፏል። ዮሐንስ በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ የትም ቦታ ላይ በሮም ያለው ጉባኤ ከሁሉም የሚበልጥ እንደሆነ አልጠቀሰም፤ እንዲሁም የጴጥሮስ ተተኪ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰብ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው የቤተ ክርስቲያን መሪ እንዳለ አልተናገረም። መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የታሪክ ማስረጃ ጴጥሮስ ራሱን በሮም በሚገኘው ጉባኤ ላይ የመጀመሪያው ጳጳስ አድርጎ ሾሟል የሚባለውን ሐሳብ አይደግፍም።

የርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳቱ ምግባርና ትምህርት ከጴጥሮስ ሕይወት ጋር ይስማማል?

“የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ” እንዲሁም “የክርስቶስ ወኪል” እንደሆነ የሚናገር ሰው የጴጥሮስንም ሆነ የክርስቶስን ምግባርና ትምህርት ይከተላል ብለን መጠበቃችን ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹ ለየት ያለ ክብር እንዲሰጡት ይፈልግ ነበር? በፍጹም። እንዲያውም ልዩ አክብሮት በተሰጠው ጊዜ ድርጊቱን ተቃውሟል። (የሐዋርያት ሥራ 10:25, 26) ስለ ኢየሱስስ ምን ማለት ይቻላል? እሱም ቢሆን የመጣው ሌሎችን ለማገልገል እንጂ ሌሎች እሱን እንዲያገለግሉት እንዳልሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:28) በአንጻሩ ደግሞ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳቱ ምን ዓይነት ታሪክ አስመዝግበዋል? ታሪካቸው ሲታይ ለየት ያለ ክብር ከመቀበል የሚርቁ፣ ከፍ ባለ የማዕረግ ስም ለመጠራት የማይፈልጉ እንዲሁም ሀብትና ሥልጣናቸው እንዲታይላቸው ከማድረግ የሚቆጠቡ እንደሆኑ ይመሠክራል?

ጴጥሮስም ሆነ ኢየሱስ ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን የሚከተሉና ለሰላም የቆሙ ሰዎች ነበሩ። እስቲ ጴጥሮስና ኢየሱስ ያስመዘገቡትን ታሪክ ሌክሲከን ፎር ቲኦሎጂ ኡንት ኪርኽ የተሰኘው የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ስለ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥረኛ ከተናገረው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር አወዳድር፦ “በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን ያስገባሉ ብሎም አብዛኛውን ጊዜ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ለሥጋ ዘመዶቻቸው ያዳላሉ እንዲሁም ቅንጦት የሞላበት ዓለማዊ ሕይወት ይመራሉ፤ ሊዮ አሥረኛ አጣዳፊ የሆኑ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውን ተግባራት ችላ ብለዋል።” ካርል አሞን የተባሉ የካቶሊክ ቄስና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፕሮፌሰር፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አሌክሳንደር ስድስተኛን በተመለከተ “እጅግ ሲበዛ እፍረተ ቢስ፣ በሥልጣናቸው አላግባብ የሚጠቀሙ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሹመትን በጉቦ የሚሰጡ እንዲሁም የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ” እንደሆኑ የታመኑ ምንጮች ማጋለጣቸውን ተናግረዋል።

ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሚያስተምሯቸውን ትምህርቶች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? የሚያስተምሩት ትምህርት ጴጥሮስና ኢየሱስ ካስተማሩት ትምህርት ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል? ጴጥሮስ ጥሩ ሰዎች በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚል እምነት አልነበረውም። ጴጥሮስ ጥሩ ሰው የነበረውን ንጉሥ ዳዊትን አስመልክቶ “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 2:34) ጴጥሮስ ሕፃናት መጠመቅ እንዳለባቸውም አላስተማረም። ከዚህ ይልቅ ጥምቀት አንድ ሰው በጥንቃቄ አመዛዝኖ ሊወስደው የሚገባ እርምጃ መሆኑን አስተምሯል።​—1 ጴጥሮስ 3:21

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ከሌላው ልቆ ለመታየት መሞከር እንደሌለባቸው አስተምሯል። ኢየሱስ “መጀመሪያ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉም መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ መሆን አለበት” ብሏል። (ማርቆስ 9:35) ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለተከታዮቹ እንዲህ የሚል ግልጽ መመሪያ ሰጥቷቸዋል፦ “እናንተ ግን መምህራችሁ አንድ ስለሆነ ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ። በተጨማሪም አባታችሁ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ። እንዲሁም መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ ‘መሪ’ ተብላችሁ አትጠሩ።” (ማቴዎስ 23:1, 8-10) ታዲያ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት አኗኗር ጴጥሮስና ክርስቶስ ካስተማሩት ትምህርት ጋር የሚስማማ ይመስልሃል?

አንዳንዶች የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እንደሆነ የሚታሰበው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከአንድ ክርስቲያን የማይጠበቅ አኗኗር ቢከተልም ከሥልጣኑ መሻር እንደሌለበት ይናገራሉ። ይህ ሐሳብ ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማሃል? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን የማይጠቅም ፍሬ ያፈራል። ጥሩ ዛፍ የማይጠቅም ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ የበሰበሰም ዛፍ መልካም ፍሬ ሊያፈራ አይችልም።” የቀረበውን ማስረጃ ስታጤነው ጴጥሮስም ሆነ ክርስቶስ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባፈሯቸው ፍሬዎች የሚደሰቱ ይመስልሃል?​—ማቴዎስ 7:17, 18, 21-23

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ኢየሱስ ከጴጥሮስ ጋር ያደረገው ውይይት ያተኮረው በክርስቶስ ማንነትና በሚጫወተው ሚና ላይ እንጂ ጴጥሮስ በሚኖረው የሥራ ድርሻ ላይ አልነበረም። (ማቴዎስ 16:13-17) ቆየት ብሎም ራሱ ጴጥሮስ ጉባኤው የተገነባበት ድንጋይ ኢየሱስ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 2:4-8) ሐዋርያው ጳውሎስም የክርስቲያን ጉባኤ “የማዕዘኑ የመሠረት ድንጋይ” ጴጥሮስ ሳይሆን ኢየሱስ እንደሆነ አረጋግጧል።​—ኤፌሶን 2:20

^ አን.14 ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ የክርስቲያን ጉባኤ የክህደት ትምህርት በሚያስተምሩ ሰዎች እየተዋጠ እንደሚመጣ አስጠንቅቀው ነበር። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:3፤ 2 ጴጥሮስ 2:1፤ 1 ዮሐንስ 2:18) በሁለተኛው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ አረማዊ ልማዶችን መከተልና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን ከግሪክ ፍልስፍና ጋር መቀላቀል በጀመረ ጊዜ ኢየሱስና ሐዋርያቱ የተናገሩት ነገር ተፈጸመ።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት የጴጥሮስን ምሳሌ እንደተከተሉ ማስረጃዎች ያሳያሉ?