የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችው መቼ ነው?—ክፍል አንድ
የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችው መቼ ነው?—ክፍል አንድ
ይህን ማወቅ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ማስረጃዎቹ ምን ያሳያሉ?
ይህ ርዕስ የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችበትን ጊዜ በተመለከተ ምሁራን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ ከሚወጡት ሁለት ተከታታይ ርዕሶች የመጀመሪያው ነው። ሁለት ክፍሎች ያሉት ይህ ርዕስ፣ አንዳንድ አንባቢያንን ግራ ካጋቧቸው ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ጥልቅ ምርምር የተደረገባቸውና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መልሶችን ይዟል።
“አብዛኞቹ የታሪክ ምሁራንና የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ586 ወይም በ587 ዓ.ዓ. እንደሆነ ያምናሉ። * ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. እንደሆነ የሚናገሩት ለምንድን ነው? በዚህ ቀን እንደጠፋች የሚያሳይ ምን ማስረጃ አላችሁ?”
ይህን ጥያቄ የላከልን ከመጽሔታችን አንባቢያን አንዱ ነው። ይሁን እንጂ የባቢሎን ንጉሥ የነበረው ዳግማዊ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ያጠፋበትን ትክክለኛ ዓመት ማወቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? አንደኛ፣ ይህ ክንውን በአምላክ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ጉልህ ለውጥ የተፈጸመበት ጊዜ ስለሆነ ነው። አንድ የታሪክ ምሁር ይህ ክንውን “መዓት፣ በእርግጥም ታላቅ እልቂት” ያስከተለ እንደሆነ ተናግረዋል። ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ዓመት፣ ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ ከ400 ለሚበልጡ ዓመታት አምልኮ ሲቀርብበት የኖረው ቤተ መቅደስም ወድሟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ መዝሙራዊ “አምላክ ሆይ፤ ሕዝቦች . . . የተቀደሰውን ቤተ መቅደስህን አረከሱ፤ ኢየሩሳሌምንም አፈራርሰው ጣሏት” በማለት የሐዘን እንጉርጉሮውን ጽፏል።—መዝሙር 79:1
ሁለተኛ፣ ይህ “ታላቅ እልቂት” የጀመረበትን ትክክለኛ ዓመት ማወቃችን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚከናወነው እውነተኛ አምልኮ መልሶ መቋቋሙ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም ያደረገው እንዴት እንደሆነ መረዳታችን የአምላክ ቃል አስተማማኝ ስለመሆኑ ያለንን እምነት ስለሚያጠናክርልን ነው። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሩሳሌም ከጠፋችበት ዓመት ጋር በተያያዘ በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ካለው ዘመን የ20 ዓመት ልዩነት ያለውን ጊዜ ትክክል እንደሆነ አድርገው የሚያምኑት ለምንድን ነው? በአጭሩ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ማስረጃዎች የተነሳ ነው።
“ሰባ ዓመት” የተባለው ለማን ነበር?
ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ ከዓመታት በፊት አይሁዳዊው ነቢይ ኤርምያስ የመጽሐፍ ቅዱስን የዘመን አቆጣጠር ለመረዳት የሚያስችል ፍንጭ ሰጥቶ ነበር። ኤርምያስ ‘በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ሁሉ’ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ላይ “አገሪቱ በሞላ ባድማና ጠፍ ትሆናለች፤ እነዚህም ሕዝቦች ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ” ብሎ ነበር። (ኤርምያስ 25:1, 2, 11) ነቢዩ ቆየት ብሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ሥፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።’” (ኤርምያስ 29:10) “ሰባ ዓመት” የሚለው ሐሳብ ምን ያመለክታል? ይህ ጊዜ ኢየሩሳሌም የጠፋችበትን ዓመት ለማወቅ የሚያስችለንስ እንዴት ነው?
ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እነዚህን 70 ዓመታት የገለጿቸው አይሁዳውያንን ሳይሆን የባቢሎንን አገዛዝ እንደሚያመለክቱ አድርገው ነው። በመሆኑም አንዳንድ የታሪክ ምሁራን እነዚህ ዓመታት የሚያመለክቱት አይሁዳውያን ‘በባቢሎን
የቆዩበትን ጊዜ’ ሳይሆን የባቢሎን አገዛዝ የዘለቀበትን ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ። ዓለማዊ የዘመን አቆጣጠር እንደሚጠቁመው ከሆነ ባቢሎናውያን የጥንቷን ይሁዳና ኢየሩሳሌምን 70 ለሚያህሉ ዓመታት ማለትም ከ609 ዓ.ዓ. ገደማ ጀምሮ የባቢሎን ዋና ከተማ እስከተያዘችበት እስከ 539 ዓ.ዓ. ድረስ ተቆጣጥረው ቆይተዋል።መጽሐፍ ቅዱስ ግን 70ው ዓመት አምላክ እሱን ለመታዘዝ ቃል ኪዳን ገብተው በነበሩት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ላይ ከባድ ቅጣት የሚያመጣበት ጊዜ እንደሚሆን ያመለክታል። (ዘፀአት 19:3-6) ከመጥፎ መንገዶቻቸው ለመመለስ አሻፈረኝ ባሉ ጊዜ አምላክ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እጠራለሁ . . . በዚህች ምድርና በነዋሪዎቿም ላይ፣ በአካባቢዋም ባሉ ሕዝቦች ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ።” (ኤርምያስ 25:4, 5, 8, 9) በእርግጥ የይሁዳ አጎራባች ብሔራትም የባቢሎን ቁጣ ገፈት ቀማሽ ነበሩ፤ ሆኖም ኤርምያስ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰውን ጥፋትና ይህን ተከትሎ ሕዝቡ ለ70 ዓመት በግዞት መወሰዳቸውን አስመልክቶ ሲጽፍ “በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት” ብሎ የተናገረ ሲሆን ይህም የሆነው “ኢየሩሳሌም ከባድ ኃጢአት [ስለሠራች]” መሆኑን ገልጿል።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 1:8፤ 3:42፤ 4:6
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጸው መሠረት 70ው ዓመት ይሁዳ መራራ ቅጣት የቀመሰችበት ጊዜ ሲሆን አምላክ ይህን ከባድ ቅጣት ለማስፈጸም እንደ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመው ባቢሎናውያንን ነው። ሆኖም አምላክ አይሁዳውያንን ‘ሰባው ዓመት በተፈጸመ ጊዜ ወደዚህ ሥፍራ [ወደ ይሁዳና ኢየሩሳሌም] እመልሳችኋለሁ’ ብሏቸው ነበር።—ኤርምያስ 29:10
“ሰባው ዓመት” የጀመረው መቼ ነው?
ኤርምያስ ስለ 70ው ዓመት የተናገረው ትንቢት ከተፈጸመ በኋላ የኖረውና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የታሪክ ዘገባ ያሰፈረው ዕዝራ ስለ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሲጽፍ እንደሚከተለው ብሎ ነበር፦ “ከሰይፍ የተረፉትን ቅሬታዎች በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እስከ ፋርስ መንግሥት መነሣትም ድረስ የእርሱና የልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ። ምድሪቱም የሰንበት ዕረፍት አገኘች፤ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ሰባው ዓመት እስኪያበቃ ድረስ፣ ባድማ በነበረችበት ዘመን ሁሉ ዐረፈች።”—2 ዜና መዋዕል 36:20, 21
በመሆኑም 70ው ዓመት የይሁዳ ምድርና ኢየሩሳሌም “የሰንበት ዕረፍት” የሚያገኙበት ጊዜ ነበር። ይህም ምድሪቱ አትታረስም ማለት ነው፤ ዘር የሚዘራም ሆነ ወይኑን የሚገርዝ ሰው አይኖርም። (ዘሌዋውያን 25:1-5) የአምላክ ሕዝቦች ሁሉንም የሰንበት ዓመታት እንዲያከብሩ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ጨምሮ የአምላክን ሕግጋት ባለመታዘዛቸው የተነሳ ምድራቸው ሳይታረስ ለ70 ዓመት ባድማ ሆኖ እንዲቆይ በማድረግ አምላክ ቀጥቷቸዋል።—ዘሌዋውያን 26:27, 32-35, 42, 43
ታዲያ የይሁዳ ምድር ምንም የማይሠራባት ባድማ የሆነችው መቼ ነበር? በናቡከደነፆር የሚመሩት ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት የሰነዘሩት ሁለት ጊዜ ሲሆን በሁለቱ ጥቃቶች መካከል የተወሰኑ ዓመታት አልፈዋል። ታዲያ 70ው ዓመት የጀመረው መቼ ነበር? ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን መጀመሪያ በከበበበት ጊዜ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ለምን? በዚያ ጊዜ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ብዙ ምርኮኞችን ወደ ባቢሎን የወሰደ ቢሆንም በምድሪቱ ላይ እንዲኖሩ የተዋቸው ሰዎች ነበሩ። ከተማዋንም ቢሆን አላጠፋትም። ናቡከደነፆር፣ አይሁዳውያንን ለመጀመሪያ ጊዜ በግዞት ከወሰደ በኋላ በይሁዳ የቀሩት “የመጨረሻዎቹ ያገሪቱ ድኾች” ለበርካታ ዓመታት መሬታቸውን እያረሱ ይኖሩ ነበር። (2 ነገሥት 24:8-17) ይሁን እንጂ ሁኔታዎች በድንገት ተለወጡ።
አይሁዳውያን በማመፃቸው የተነሳ ባቢሎናውያን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው መጡ። (2 ነገሥት 24:20፤ 25:8-10) ባቢሎናውያን ቅዱስ የሆነውን ቤተ መቅደስ ጨምሮ ከተማዋን ድምጥማጧን አጠፏት፤ እንዲሁም ብዙዎቹን የከተማዋን ነዋሪዎች ወደ ባቢሎን በግዞት ወሰዷቸው። በምድሪቱ የቀሩት ሕዝብ “ባቢሎናውያንን ከመፍራታቸው የተነሣ” በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ “ትንሽ ትልቅ ሳይባል . . . [ሁሉም] ከሰራዊቱ የጦር አለቆች ጋር ወደ ግብፅ ሸሹ።” (2 ነገሥት 25:25, 26) በመሆኑም ምድሪቱ ምንም የማይሠራባትና ባድማ ሆና የሰንበት እረፍት ማድረግ ጀመረች ሊባል የሚችለው ይህ በሆነበት ዓመት፣ ቲሽሪ (መስከረም/ጥቅምት) በሚባለው የአይሁዳውያን ሰባተኛው ወር ነው። አምላክ በግብፅ የነበሩትን አይሁዳውያን ስደተኞች በኤርምያስ በኩል እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ያመጣሁትን ታላቅ ጥፋት አይታችኋል፤ ዛሬ ማንም የማይኖርባቸው ባድማ ሆነው ይታያሉ።” (ኤርምያስ 44:1, 2) በመሆኑም 70ው ዓመት የጀመረው ይህ ክስተት በተፈጸመበት ዓመት እንደሆነ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለን። ታዲያ ይህ ዓመት መቼ ነበር? ይህን ጥያቄ ለመመለስ 70ው ዓመት ያበቃበትን ጊዜ ማወቅ ያስፈልገናል።
“ሰባው ዓመት” ያበቃው መቼ ነው?
“እስከ ፋርስ መንግሥት መነሣት” ድረስ በሕይወት የነበረው ነቢዩ ዳንኤል በዚያን ጊዜ በባቢሎን የነበረ ሲሆን 70ው ዓመት የሚፈጸምበትን ጊዜ አስልቶ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እኔ ዳንኤል ለነቢዩ ለኤርምያስ በተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ የኢየሩሳሌም መፈራረስ ሰባ ዓመት እንደሚቈይ ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተዋልሁ።”—ዳንኤል 9:1, 2
ዕዝራ፣ ነቢዩ ኤርምያስ በተናገራቸው ትንቢቶች ላይ ካሰላሰለ በኋላ “ሰባው ዓመት” ያበቃበት ጊዜ ‘የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ ዐዋጅ እንዲያስነግር እግዚአብሔር መንፈሱን ካነሣሣበት’ ወቅት ጋር እንደሚያያዝ ገልጿል። (2 ዜና መዋዕል 36:21, 22) አይሁዳውያን ነፃ የወጡት መቼ ነበር? ከግዞት ነፃ መሆናቸውን የሚገልጸው አዋጅ የወጣው “በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ዓመት” ነበር። ( “በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ዓመት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በመሆኑም በ537 ዓ.ዓ. የመጸው ወቅት አይሁዳውያን እውነተኛውን አምልኮ እንደገና ለማቋቋም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ነበር።—ዕዝራ 1:1-5፤ 2:1፤ 3:1-5
እንግዲያው በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር መሠረት 70ው ዓመት ቃል በቃል የሚወሰድ ጊዜ ሲሆን ያበቃውም በ537 ዓ.ዓ. ነበር። ከዚህ ዓመት ተነስተን 70 ዓመት ወደኋላ ስንቆጥር ሰባው ዓመት የጀመረበት ዓመት ላይ ይኸውም 607 ዓ.ዓ. እንደርሳለን።
ታዲያ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉት መጻሕፍት የሚያቀርቡት ማስረጃ ኢየሩሳሌም የጠፋችበት ዓመት 607 ዓ.ዓ. መሆኑን በግልጽ የሚያመለክት ከሆነ ብዙ የታሪክ ምሁራን በ587 ዓ.ዓ. ይህች ከተማ እንደጠፋች የሚናገሩት ለምንድን ነው? ይህንን የሚሉት በሁለት የመረጃ ምንጮች ይኸውም ጥንታዊ የታሪክ ምሁራን ባዘጋጇቸው ጽሑፎች እና ቶለሚ ባዘጋጀው የነገሥታት ስም ዝርዝር ላይ ተንተርሰው ነው። ታዲያ እነዚህ የታሪክ ምንጮች ከቅዱሳን መጻሕፍት ይልቅ እምነት የሚጣልባቸው ናቸው? እስቲ እንመልከት።
ጥንታዊ የታሪክ ምሁራን ምን ያህል እምነት የሚጣልባቸው ናቸው?
ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ጊዜ አካባቢ የኖሩ የታሪክ ምሁራን፣ “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ተብሎ በሚጠራው ጊዜ ስለነበሩት የባቢሎን ነገሥታት የሚሰጡት መረጃ የተምታታ ነው። * ( “‘የሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ’ ነገሥታት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) እነሱ ባዘጋጁት የዘመናት ስሌት ላይ ተመሥርቶ የሚሰላው የታሪክና የጊዜ ቅደም ተከተል መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው መረጃ ጋር አይስማማም። ይሁንና የእነዚህ ሰዎች ጽሑፎች የያዟቸው መረጃዎች ምን ያህል እምነት የሚጣልባቸው ናቸው?
“ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ተብሎ በሚጠራው ጊዜ አካባቢ ከኖሩት የታሪክ ምሁራን መካከል አንዱ በራሰስ የተባለ ባቢሎናዊ “የቤል ካህን” ነው። ባቢሎኒያካ የተሰኘውና በ281 ዓ.ዓ. ገደማ የተጻፈው የመጀመሪያ ሥራው ጠፍቷል፤ ሌሎች የታሪክ ምሁራን በሥራዎቻቸው ውስጥ ያካተቷቸው ከእሱ ጽሑፍ የተወሰዱ ክፍሎችም ቢሆኑ ጥቂት ናቸው። በራሰስ “በባቢሎን በከፍተኛ ጥንቃቄ ተጠብቀው የቆዩ መጻሕፍትን” እንደተጠቀመ ተናግሯል።1 ታዲያ በራሰስ በእርግጥ እምነት የሚጣልበት የታሪክ ምሁር ነበር? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
በራሰስ፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ሥልጣን ላይ የወጣው “ከወንድሙ” ቀጥሎ እንደነበረና “ከእሱ በኋላ ልጁ [አስራዶን] ለ8 ዓመት፣ ቀጥሎም ሳሙጄስ [ሻማሽ ሹማ ዩኪን] ለ21 ዓመት” እንደገዛ ጽፏል። (III, 2.1, 4) ይሁን እንጂ በራሰስ ከኖረበት ዘመን ከረጅም ጊዜ በፊት የተጻፉ የባቢሎን ታሪካዊ ሰነዶች፣ ሰናክሬም ዙፋኑን የወረሰው ከአባቱ ከዳግማዊ ሳርጎን እንጂ ከወንድሙ እንዳልሆነ ይገልጻሉ፤ አስራዶን የገዛው ለ8 ዓመት ሳይሆን ለ12 ዓመት እንደሆነ ሻማሽ ሹማ ዩኪን ደግሞ ለ21 ዓመት ሳይሆን ለ20 ዓመት እንደገዛ ይናገራሉ። ሮባርተስ ቫን ደር ስፔክ የተሰኙ ምሁር፣ በራሰስ የባቢሎንን ዜና ታሪኮች እንዳመሣከረ ቢያምኑም “ይህ ግን የራሱን ሐሳብና ማብራሪያ ከመጨማመር አላገደውም” በማለት ጽፈዋል።2
ሌሎች ምሁራንስ ስለ በራሰስ ምን አመለካከት አላቸው? በበራሰስ ጽሑፎች ላይ ጥልቅ ጥናት ያካሄዱት ስታንሊ በርስታይን “ቀደም ሲል ብዙዎች በራሰስን እንደ ታሪክ ምሁር አድርገው ይቆጥሩት ነበር” ብለዋል። ሆኖም በማጠቃለያቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “ከአንድ የታሪክ ምሁር አንጻር ሥራው ብቃት ይጎድለዋል። ባቢሎኒያካ ከተባለው ሥራው ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ጥቂት ክፍሎች [ሲሆኑ በእነዚያ] ላይ እንኳ ምንም በማያሻሙ ጉዳዮች ላይ በርካታ የሚያስገርሙ ስህተቶች ይታያሉ። . . . ከአንድ የታሪክ ምሁር እንዲህ ዓይነት ስህተት አይጠበቅም፤ ለነገሩ በራሰስ ጽሑፉን ያዘጋጀበት ዓላማ የታሪክ መዝገብ ለማጠናቀር አልነበረም።”3
ከላይ ከቀረቡት ሐሳቦች አንጻር አንተ ምን ይመስልሃል? የበራሰስ ስሌቶች ሁልጊዜ ትክክል እንደሆኑ ተደርገው መታየት ይኖርባቸዋል? በአብዛኛው በበራሰስ ጽሑፎች ላይ ተንተርሰው የዘመን አቆጣጠር ስሌት ስለሠሩ ሌሎች ጥንታዊ የታሪክ ምሁራንስ ምን ሊባል ይችላል? ከታሪክ አንጻር እነሱ የደረሱበት ድምዳሜ በእርግጥ እምነት ሊጣልበት ይችላል?
የቶለሚ የነገሥታት ስም ዝርዝር
በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረው ቀላውዴዎስ ቶለሚ የተባለ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ያጠናቀረው የነገሥታት ስም ዝርዝርም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. ነው የሚለውን ሐሳብ ለመደገፍ አገልግሏል። ቶለሚ ያዘጋጀው የነገሥታት ስም ዝርዝር “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ተብሎ የሚጠራውን
ዘመን ጨምሮ ለጥንታዊው ታሪክ የዘመናት ስሌት ዋና መሠረት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።ቶለሚ የስም ዝርዝሮቹን ያቀናበረው “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ተብሎ የሚጠራው ዘመን ካበቃ ከ600 ዓመታት ገደማ በኋላ ነው። ታዲያ በዚህ ዝርዝር ላይ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ንጉሥ መግዛት የጀመረበትን ዓመት እንዴት ሊያውቅ ቻለ? ቶለሚ፣ በተወሰነ መጠን የጨረቃ ግርዶሽን መሠረት ያደረጉ የሥነ ፈለክ ስሌቶችን ተጠቅሞ “ወደኋላ በመቁጠር ናቦናሳር [በዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ንጉሥ] መግዛት የጀመረበትን ጊዜ ማስላት” እንደቻለ ተናግሯል።4 በመሆኑም የብሪትሽ ቤተ መዘክር ባልደረባ የሆኑት ክሪስቶፈር ዎከር እንዲህ ብለዋል፦ “ቶለሚ ያዘጋጀው የስም ዝርዝር [ዓላማ] የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች . . . የማይለዋወጥ የዘመን አቆጣጠር እንዲኖራቸው ለማድረግ . . . እንጂ ነገሥታቱ ሥልጣን ላይ ስለወጡበትና ስለሞቱበት ጊዜ ለታሪክ ምሁራን ትክክለኛ ታሪካዊ መዝገብ ለማቅረብ ተብሎ የተዘጋጀ አይደለም።”5
ከቶለሚ ደጋፊዎች አንዱ የሆኑት ሌኦ ደፓውት እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ የስም ዝርዝር ከሥነ ፈለክ አንጻር አስተማማኝ መሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት የታወቀ ነገር ነው። . . . ይህ ሲባል ግን ከታሪክ አንጻር እምነት የሚጣልበት ነው ማለት አይደለም።” የቶለሚን የነገሥታት ስም ዝርዝር በተመለከተ ፕሮፌሰር ደፓውት አክለው እንዲህ ብለዋል፦ “ቀደም ሲል ከነበሩት ገዢዎች ጋር በተያያዘ [“ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ተብሎ በሚጠራው ዘመን የነበሩትንም ይጨምራል] እያንዳንዱ ንጉሥ የገዛበትን ዘመን ለማወቅ ይህን ዝርዝር ከኪዩኒፎርም የታሪክ መዛግብት ጋር ማነጻጸር ያስፈልጋል።”6
የቶለሚን የነገሥታት ስም ዝርዝር ታሪካዊ ትክክለኛነት ለመመዘን የሚያስችሉን ‘የኪዩኒፎርም የታሪክ መዛግብት’ ምንድን ናቸው? የባቢሎንን ዜና ታሪኮች፣ የነገሥታትን ስም ዝርዝርና የንግድ ጉዳይ የተጻፈባቸውን ጽላቶች የሚጨምሩ ሲሆን “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ተብሎ በሚጠራው ዘመን ወይም ከዚያ ብዙም ሳይርቅ የኖሩ ጸሐፍት ያዘጋጇቸው የኪዩኒፎርም ሰነዶች ናቸው።7
ታዲያ ቶለሚ ያዘጋጀውን ስም ዝርዝር ከኪዩኒፎርም የታሪክ መዛግብት ጋር ስናነጻጽረው ምን እናገኛለን? “የቶለሚ የነገሥታት ስም ዝርዝር ከጥንታዊ ጽላቶች ጋር ሲነጻጸር” (ከታች ተመልከት) የሚለው ሣጥን የስም ዝርዝሩን የተወሰነ ክፍል ከጥንታዊ የኪዩኒፎርም ሰነድ ጋር ያነጻጽረዋል። በቶለሚ ዝርዝር ላይ ካንዳላኑና ናቦኒደስ በተባሉት ባቢሎናውያን ገዢዎች መካከል የሰፈሩት አራት ነገሥታት ብቻ እንደሆኑ ልብ በል። ይሁን እንጂ ከኪዩኒፎርም የታሪክ መዛግብት አንዱ የሆነው የዩሩክ የነገሥታት ስም ዝርዝር፣ በካንዳላኑና በናቦኒደስ መካከል ሰባት ነገሥታት እንደነበሩ ያሳያል። ቶለሚ እነዚህን ሦስት ነገሥታት ያልጠቀሳቸው የግዛት ዘመናቸው አጭርና ከቁጥር የማይገባ ስለሆነ ነው? የኪዩኒፎርም የንግድ ጉዳይ ጽላቶች በሚገልጹት መሠረት ከእነዚህ ነገሥታት አንዱ ለሰባት ዓመት ገዝቷል።8
ከናቦፖላሳር (“የሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” የመጀመሪያው ንጉሥ) በፊት በባቢሎን ሌላ ንጉሥ (አሹር ኤቴል ኢላኒ) ለአራት ዓመት እንደገዛ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ በኪዩኒፎርም ሰነዶች ላይ ተገኝቷል። በተጨማሪም ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ በምድሪቱ ላይ ንጉሥ አልነበረም።9 ሆኖም ይህ ሁሉ በቶለሚ ዝርዝር ውስጥ አልተጠቀሰም።
ቶለሚ አንዳንዶቹን ገዢዎች ያልጠቀሳቸው ለምንድን ነው? ትክክለኛ የባቢሎን ገዢዎች እንደሆኑ አድርጎ ስላልቆጠራቸው እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።10 ለምሳሌ ያህል፣ “በሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ዘመን ንጉሥ የነበረውን ላባሺ ማርዱክን ሳይጠቅሰው ቀርቷል። ይሁን እንጂ የኪዩኒፎርም ሰነዶች በሚሰጡን መረጃ መሠረት፣ ቶለሚ ሳይጠቅሳቸው የቀሩት ነገሥታት በባቢሎን ላይ ገዝተዋል።
የቶለሚ ዝርዝር በብዙዎች ዘንድ ትክክለኛ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ይሁን እንጂ ቶለሚ ሳይጠቅሳቸው የቀሩ ነገሥታት ከመኖራቸው አንጻር ታሪክን በትክክለኛው ቅደም ተከተል እንዳሰፈረ ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል?
በማስረጃው ላይ የተመሠረተ ማጠቃለያ
ጉዳዩን ለማጠቃለል ያህል፦ መጽሐፍ ቅዱስ አይሁዳውያን ለ70 ዓመት በግዞት እንደቆዩ በግልጽ ይናገራል። እነዚህ አይሁዳውያን ግዞተኞች በ537 ዓ.ዓ. ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው እንደነበር የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ያለ ሲሆን አብዛኞቹ ምሁራንም በዚህ ይስማማሉ። ከ537 ዓ.ዓ. ጀምሮ ወደኋላ ስንቆጥር ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. መሆኑን እንገነዘባለን። ጥንታዊ የታሪክ ምሁራንና የቶለሚ የነገሥታት ዝርዝር ይህን ዓመት ባይደግፉትም የእነዚህን ሰዎች ሥራዎች ትክክለኛነት በተመለከተ ሊነሱ የሚችሉ አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች አሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ ሁለት የታሪክ ምንጮች የመጽሐፍ ቅዱስን የዘመን አቆጣጠር ውድቅ ለማድረግ የሚያስችል አጥጋቢ ማስረጃ አያቀርቡም።
ይሁን እንጂ መልስ የሚያሻቸው ሌሎች ጥያቄዎችም አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. እንደጠፋች የሚገልጸውን ሐሳብ የሚደግፍ ታሪካዊ ማስረጃ የለም ማለት ነው? የተጻፉበት ጊዜ በግልጽ የሚታወቅ የኪዩኒፎርም ሰነዶች (አብዛኞቹ በጥንት ዘመን በኖሩ የዓይን ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው) ምን ማስረጃ ይፋ አድርገዋል? እነዚህን ጥያቄዎች በሚቀጥለው እትም ላይ እንወያይባቸዋለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 ዓለማዊ የታሪክ ምንጮች ሁለቱንም ዓመታት ይጠቅሳሉ። ይሁንና ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ 587 ዓ.ዓ. ላይ ብቻ ትኩረት እናደርጋለን።
^ አን.23 “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” የጀመረው በናቡከደነፆር አባት በናቦፖላሳር የግዛት ዘመን ሲሆን ያበቃው ደግሞ የናቦኒደስ የግዛት ዘመን ሲያከትም ነው። ኢየሩሳሌም ባድማ ከሆነችበት የ70 ዓመት ጊዜ ውስጥ አብዛኛው የሚካተተው “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” በሚባለው ዘመን ውስጥ ነው፤ በመሆኑም ይህ ጊዜ የምሁራንን ትኩረት ይስባል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ዓመት
ዳግማዊ ቂሮስ ባቢሎንን ድል ያደረገው በ539 ዓ.ዓ. እንደሆነ የምንናገረው የሚከተሉትን የታሪክ ምንጮች ዋቢ በማድረግ ነው፦
▪ ጥንታዊ የታሪክ ምንጮችና የኪዩኒፎርም ጽላቶች፦ የሲሲሊው ዳየዶረስ (ከ80-20 ዓ.ዓ. ገደማ) እንደጻፈው ቂሮስ የፋርስ ንጉሥ የሆነው “በሃምሳ አምስተኛው ኦሎምፒያድ የመጀመሪያ ዓመት” ላይ ነው። (ሂስቶሪካል ላይብረሪ፣ 9ኛ መጽሐፍ 21) ይህም 560 ዓ.ዓ. ነው። ግሪካዊው የታሪክ ምሁር ሄሮዶተስ (ከ485-425 ዓ.ዓ. ገደማ) እንደገለጸው ቂሮስ የሞተው “ሃያ ዘጠኝ ዓመታት ከገዛ በኋላ” ሲሆን ይህም በ30ኛው የግዛት ዓመቱ ማለትም በ530 ዓ.ዓ. ነው። (ሂስቶሪስ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ክሊዮ፣ 214) የኪዩኒፎርም ጽላቶች ቂሮስ ከመሞቱ በፊት ባቢሎንን ለዘጠኝ ዓመታት እንደገዛ ያሳያሉ። በመሆኑም ቂሮስ ባቢሎንን ድል ያደረገው በ530 ዓ.ዓ. ከመሞቱ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ይኸውም በ539 ዓ.ዓ. ነው ማለት ነው።
የኪዩኒፎርም ጽላት የሚሰጠው ማስረጃ፦ ሥነ ፈለካዊ መረጃ የያዘ አንድ የባቢሎን የሸክላ ጽላት (ቢኤም 33066) ቂሮስ የሞተው በ530 ዓ.ዓ. እንደሆነ ያረጋግጣል። ምንም እንኳ ይህ ጽላት የሰማይ አካላትን አቀማመጥ በተመለከተ አንዳንድ ስህተቶች ቢኖሩትም የቂሮስ ልጅና አልጋ ወራሽ በነበረው በዳግማዊ ካምቢሰስ ግዛት ሰባተኛ ዓመት ላይ ሁለት የጨረቃ ግርዶሾች እንደታዩ ይገልጻል። እነዚህ የጨረቃ ግርዶሾች ሐምሌ 16, 523 ዓ.ዓ. እና ጥር 10, 522 ዓ.ዓ. በባቢሎን እንደታዩ ታውቋል፤ በመሆኑም የካምቢሰስ ሰባተኛ ዓመት የግዛት ዘመን የጀመረው በ523 ዓ.ዓ. መጀመሪያ አካባቢ ነበር ማለት ነው። ከዚህ አንጻር የካምቢሰስ የመጀመሪያ የግዛት ዓመት 529 ዓ.ዓ. ይሆናል። እንግዲያው የቂሮስ የመጨረሻው የግዛት ዓመት 530 ዓ.ዓ. ሲሆን ባቢሎንን መግዛት የጀመረው ደግሞ በ539 ዓ.ዓ. ነው።
[የሥዕሉ መግለጫ]
Tablet: © The Trustees of the British Museum
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አጭር ማጠቃለያ
▪ ብዙውን ጊዜ ዓለማዊ የታሪክ ምሁራን ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. እንደሆነ ይናገራሉ።
▪ የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር ከተማዋ የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. እንደሆነ የሚጠቁም አሳማኝ ማስረጃ ይሰጣል።
▪ ዓለማዊ የታሪክ ምሁራን ለደረሱበት መደምደሚያ በዋነኝነት መሠረት ያደረጉት የጥንታዊ የታሪክ ምሁራንን ሥራዎችና የቶለሚን የነገሥታት ስም ዝርዝር ነው።
▪ የጥንታዊ የታሪክ ምሁራን ጽሑፎች ጉልህ ስህተቶች የሚታዩባቸው ከመሆኑም ሌላ በሸክላ ጽላቶች ላይ ተጽፈው ከሚገኙት የታሪክ መዛግብት ጋር የሚስማሙት ሁልጊዜ አይደለም።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተጨማሪ መረጃ
1. ባቢሎኒያካ (ካልዴኦረም ሂስቶራዬ)፣ መጽሐፍ አንድ፣ 1.1
2. ስተዲስ ኢን ኤንሸንት ኒር ኢስተርን ዎርልድ ቪው ኤንድ ሶሳይቲ፣ ገጽ 295
3. ዘ ባቢሎኒያካ ኦቭ በራሰስ፣ ገጽ 8
4. አልማጄስት ሦስተኛ፣ 7 ከቶለሚ አልማጄስት በ1998 የታተመ፣ ገጽ 166 በጄራልድ ቱመር የተተረጎመ። ባቢሎናውያን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ተመሳሳይ የሆኑ ግርዶሾች የሚታዩት በየ18 ዓመቱ እንደሆነ ስለሚያምኑ ቀደም ሲል የታዩና ወደፊት የሚታዩ ግርዶሾች የሚከሰቱበትን ጊዜ “ለማስላት” በሒሳብ ቀመር እንደሚጠቀሙ ቶለሚ ያውቅ ነበር።—አልማጄስት አራተኛ፣ 2
5. ሜሶፖታሚያ ኤንድ ኢራን ኢን ዘ ፐርዢያን ፔሬድ፣ ገጽ 17, 18
6. ጆርናል ኦቭ ኪዩኒፎርም ስተዲስ፣ ጥራዝ 47, 1995 ገጽ 106, 107
7. ኪዩኒፎርም ማለት አንድ ጸሐፊ ሹል የሆነና ጫፉ ላይ የሽብልቅ ቅርጽ ያለው መጻፊያ እየተጠቀመ ባልደረቀ የሸክላ ጽላት ላይ የተለያዩ ምልክቶችን በመቅረጽ የሚጽፍበት የጽሑፍ ዓይነት ነው።
8. ሲን ሻራ ኢሽኩን ለሰባት ዓመት ገዝቷል፤ የዚህ ንጉሥ 57 የንግድ ጽላቶች የተዘጋጁት ንጉሡ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ዓመት ጀምሮ ባሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ነው። ጆርናል ኦቭ ኪዩኒፎርም ስተዲስ፣ ጥራዝ 35, 1983 ከገጽ 54-59 ተመልከት።
9. ሲ.ቢ.ኤም. 2152 የተባለው ጽላት የተዘጋጀው በአሹር ኤቴል ኢላኒ አራተኛ ዓመት ነው። (ሌጋል ኤንድ ከመርሻል ትራንዛክሽንስ ዴትድ ኢን ዚ አሲሪያን፣ ኒዎ ባቢሎኒያን ኤንድ ፐርዢያን ፔሬድስ—ቺፍሊ ፍሮም ኒፑር፣ በክሌይ የተዘጋጀ፣ 1908 ገጽ 74) በሃራን የተቀረጸው የናቦኒደስ ጽሑፍ ደግሞ (ኤች1ቢ)፣ በመጀመሪያው ረድፍ 30ኛው መስመር ላይ ከናፖቦላሳር በፊት አስፍሮታል። (አናቶሊያን ስተዲስ፣ ጥራዝ 8, 1958 ገጽ 35, 47) ንጉሥ ያልነበረበትን ዘመን በተመለከተ አሲሪያን ኤንድ ባቢሎኒያን ክሮኒክልስ፣ 2ተኛው ዜና ታሪክ፣ 14ኛ መስመር ገጽ 87, 88ን ተመልከት።
10. አንዳንድ ምሁራን፣ ቶለሚ በነገሥታት ስም ዝርዝሩ ውስጥ እንዳሰፈረ የገለጸው የባቢሎን ነገሥታትን ብቻ በመሆኑ የተወሰኑ ነገሥታትን ከዝርዝሩ ውስጥ ያወጣቸው “የአሦር ንጉሥ” በሚል ስያሜ ስለተጠሩ ነው ብለው ይከራከራሉ። ይሁንና በገጽ 30 ላይ ከሚገኘው ሣጥን መመልከት እንደምትችለው ቶለሚ በዝርዝሩ ላይ ያሰፈራቸው አንዳንድ ነገሥታትም “የአሦር ንጉሥ” በሚል ስያሜ ተጠርተዋል። የንግድ ጽላቶች እንዲሁም የኪዩኒፎርም ደብዳቤዎችና ጽላቶች በግልጽ እንደሚያሳዩት አሹር ኤቴል ኢላኒ፣ ሲን ሹሙ ሊሺር እንዲሁም ሲን ሻራ ኢሽኩን የተባሉት ነገሥታት በባቢሎን ላይ ገዝተዋል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
“የሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ነገሥታት
እነዚህ ታሪክ ጸሐፊዎች የሚሰጡት መረጃ አስተማማኝ ከሆነ እርስ በርሱ የማይስማማው ለምንድን ነው?
ነገሥታት
ናቦፖላሳር
በራሰስ ከ350-270 ዓ.ዓ. ገደማ (21)
ፖሊሂስተር ከ105-? ዓ.ዓ. (20)
ጆሴፈስ ከ37-?100 ዓ.ም. (—)
ቶለሚ ከ100-170 ዓ.ም. ገደማ (21)
ዳግማዊ ናቡከደነፆር
በራሰስ ከ350-270 ዓ.ዓ. ገደማ (43)
ፖሊሂስተር ከ105-? ዓ.ዓ. (43)
ጆሴፈስ ከ37-?100 ዓ.ም. (43)
ቶለሚ ከ100-170 ዓ.ም. ገደማ (43)
አሜል ማርዱክ
በራሰስ ከ350-270 ዓ.ዓ. ገደማ (2)
ፖሊሂስተር ከ105-? ዓ.ዓ. (12)
ጆሴፈስ ከ37-?100 ዓ.ም. (18)
ቶለሚ ከ100-170 ዓ.ም. ገደማ (2)
ኔሪግሊሳር
በራሰስ ከ350-270 ዓ.ዓ. ገደማ (4)
ፖሊሂስተር ከ105-? ዓ.ዓ. (4)
ጆሴፈስ ከ37-?100 ዓ.ም. (40)
ቶለሚ ከ100-170 ዓ.ም. ገደማ (4)
ላባሺ ማርዱክ
በራሰስ ከ350-270 ዓ.ዓ. ገደማ (9 ወራት)
ፖሊሂስተር ከ105-? ዓ.ዓ. (—)
ጆሴፈስ ከ37-?100 ዓ.ም. (9 ወራት)
ቶለሚ ከ100-170 ዓ.ም. ገደማ (—)
ናቦኒደስ
በራሰስ ከ350-270 ዓ.ዓ. ገደማ (17)
ፖሊሂስተር ከ105-? ዓ.ዓ. (17)
ጆሴፈስ ከ37-?100 ዓ.ም. (17)
ቶለሚ ከ100-170 ዓ.ም. ገደማ (17)
(#) = ነገሥታቱ የገዙበት ዘመን (በዓመታት) ጥንታዊ የታሪክ ምሁራን እንዳስቀመጡት
[የሥዕሉ ምንጭ]
Photograph taken by courtesy of the British Museum
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕሎች]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የቶለሚ የነገሥታት ስም ዝርዝር ከጥንታዊ ጽላቶች ጋር ሲነጻጸር
ቶለሚ በጻፈው ዝርዝር ውስጥ የአንዳንድ ነገሥታትን ስም ሳይጠቅስ ቀርቷል። ለምን?
የቶለሚ የነገሥታት ዝርዝር
ናቦናሳር
ናቡ ናዲን ዜሪ (ናዲኑ)
ሙኪን ዜሪ እና ፑል
ዩሉላዩ (ስልምናሶር አምስተኛ)“የአሦር ንጉሥ”
ሜሮዳክ ባልዳን
ዳግማዊ ሳርጎን “የአሦር ንጉሥ”
ንጉሥ ያልነበረበት የመጀመሪያው ዘመን
ቤል ኢብኒ
አሹር ናዲን ሹሚ
ኔርጋል ዩሼዚብ
ሙሼዚብ ማርዱክ
ንጉሥ ያልነበረበት ሁለተኛው ዘመን
አስራዶን “የአሦር ንጉሥ”
ሻማሽ ሹማ ዩኪን
ካንዳላኑ
ናቦፖላሳር
ናቡከደነፆር
አሜል ማርዱክ
ኔሪግሊሳር
ናቦኒደስ
ቂሮስ
ካምቢሰስ
በጥንታዊ ጽላቶች ላይ የተገኘው የዩሩክ የነገሥታት ስም ዝርዝር
ካንዳላኑ
ሲን ሹሙ ሊሺር
ሲን ሻራ ኢሽኩን
ናቦፖላሳር
ናቡከደነፆር
አሜል ማርዱክ
ኔሪግሊሳር
ላባሺ ማርዱክ
ናቦኒደስ
[ሥዕል]
የቶለሚን የነገሥታት ስም ዝርዝር ትክክለኛነት ለመመዘን ከሚረዱን የኪዩኒፎርም መዛግብት መካከል የባቢሎናውያን ዜና ታሪኮች ይገኙበታል
[የሥዕሉ ምንጭ]
Photograph taken by courtesy of the British Museum
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Photograph taken by courtesy of the British Museum