በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጨቅላ ሕፃናት መጠመቅ አለባቸው?

ጨቅላ ሕፃናት መጠመቅ አለባቸው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ጨቅላ ሕፃናት መጠመቅ አለባቸው?

▪ “ትንሹ ወንድሜ ጆን ሊምቦ * ገብቷል የሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር” በማለት ቪክቶሪያ ተናግራለች። እንዲህ ያለ ስጋት ያደረባት ለምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ጆን የሞተው ከመጠመቁ በፊት ነበር፤ በዚህም የተነሳ ጆን ሊምቦ ውስጥ ለዘላለም እንደሚቆይ አንድ የካቶሊክ ቄስ ነግረውን ነበር።” እንዲህ ያለው ሐሳብ ፍርሃት የሚያሳድር እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና ይህ አመለካከት የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ አለው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሳይጠመቁ የሞቱ ሕፃናት ለዘላለም እንደሚቀጡ ያስተምራል?

እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች መጠመቅ እንዳለባቸው ያስተምራል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል፦ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) የሚጠመቁ ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆን እንዳለባቸው ልብ በል። በሌላ አባባል እነዚህ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ተምረው እሱን ለመከተል የመረጡ ሰዎች ናቸው ማለት ነው፤ የትኛውም ሕፃን እንዲህ ያለውን ምርጫ ማድረግ አይችልም።

እንደዛም ሆኖ ግን በርካታ ሰዎች ኢየሱስ የሰጠው ትእዛዝ ትንንሽ ልጆችንም የሚያካትት ነው የሚል ጥብቅ አቋም አላቸው። የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ቄስ የሆኑት ሪቻርድ በቸር “ጨቅላ ሕፃናትን ጨምሮ ሁሉም ሰው መጠመቅ አለበት” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “[ሕፃናት] እንዳይጠመቁ መከልከል የኃጢአት ይቅርታ እንዳያገኙ ማድረግ ብሎም ለኩነኔ መዳረግ ይሆናል” ብለዋል። ይሁንና እንዲህ ያለው ሐሳብ ቢያንስ በሦስት መንገዶች ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር ይጋጫል።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ ጨቅላ ሕፃናት መጠመቅ እንዳለባቸው አላስተማረም። ይህ ሐቅ ትልቅ ትርጉም ያለው የሆነው ለምንድን ነው? እስቲ የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦ ኢየሱስ የአምላክን መሥፈርቶች በተመለከተ ደቀ መዛሙርቱ ማወቅ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ በትጋት አስተምሯቸዋል። እንዲያውም ቁልፍ የሆኑ ትምህርቶችን በተደጋጋሚ የነገራቸው ጊዜ ነበር። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ደቀ መዛሙርቱ የተማሩት ነገር በትክክል እንዲገባቸው ለማድረግ ነው። (ማቴዎስ 24:42፤ 25:13፤ ማርቆስ 9:34-37፤ 10:35-45) ይሁንና ጨቅላ ሕፃናት መጠመቅ እንዳለባቸው አንድ ጊዜም እንኳ አላስተማረም። ኢየሱስ ይህ አስፈላጊ መሥፈርት ቢሆን ኖሮ ሳይጠቅሰው ያልፍ ነበር? በፍጹም! ጨቅላ ሕፃናት መጠመቅ የሚያስፈልጋቸው ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ እንደሚናገር ምንም ጥርጥር የለውም።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ ሰው ከሞተ በኋላ እንደሚሠቃይ ፈጽሞ አላስተማረም። “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በሚለው ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያምን ነበር። (መክብብ 9:5) ኢየሱስ ሙታን በመንጽሔ፣ በገሃነመ እሳት ወይም በሌላ ቦታ እየተሠቃዩ እንዳልሆኑ አሊያም ሊምቦ በሚባል የመቆያ ቦታ ውስጥ እንዳልሆኑ ያውቃል። ከዚህ ይልቅ የሞቱ ሰዎች ልክ እንቅልፍ እንደወሰደው ሰው ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አስተምሯል።​—ዮሐንስ 11:1-14

በሦስተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ” ዳግመኛ ሕይወት እንደሚያገኙ አስተምሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ከሞት ከሚነሱት መካከል ጨርሶ ያልተጠመቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚገኙበት ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ሰዎች ትንሣኤ ካገኙ በኋላ የአምላክን መሥፈርቶች በመማር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚችሉበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። *​—መዝሙር 37:29

ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ጨቅላ ሕፃናት መጠመቅ እንዳለባቸው አያስተምርም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረው “ሊምቦ” ሳይጠመቁ የሞቱ ሕፃናት እንዲሁም ከኢየሱስ በፊት የኖሩ ጻድቃን የሚገቡበት ቦታ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ወደ ሰማይ እንዳይገቡ የተከለከሉ ቢሆንም በገሃነመ እሳት ለዘላለም እንዲሠቃዩም አልተፈረደባቸውም።

^ አን.8 ገነት ስለምትሆነው ምድር እና ስለ ትንሣኤ ተስፋ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 እና 7 ተመልከት።