በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ፆታ ግንኙነት የሚነሱ አሥር ጥያቄዎች መልስ

ስለ ፆታ ግንኙነት የሚነሱ አሥር ጥያቄዎች መልስ

ስለ ፆታ ግንኙነት የሚነሱ አሥር ጥያቄዎች መልስ

1 አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት የፈጸሙት የመጀመሪያው ኃጢአት የፆታ ግንኙነት ነበር?

▪ መልስ፦ ብዙ ሰዎች በኤደን ገነት ውስጥ የነበረው የተከለከለ ፍሬ የፆታ ግንኙነትን እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህን አያስተምርም።

እስቲ አስበው፦ ሔዋን ከመፈጠሯ በፊትም እንኳ አምላክ “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” ፍሬ እንዳይበላ አዳምን አዝዞት ነበር። (ዘፍጥረት 2:15-18) በወቅቱ አዳም ብቻውን ስለነበረ ይህ ትእዛዝ የፆታ ግንኙነትን የሚከለክል ሊሆን አይችልም። በተጨማሪም አምላክ ለአዳምና ለሔዋን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” የሚል ግልጽ ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) አፍቃሪ የሆነ አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት “ምድርን ሙሏት” የሚለውን የፆታ ግንኙነት መፈጸምን የሚጠይቀውን ትእዛዝ ከሰጣቸው በኋላ ይህን ትእዛዝ በመጠበቃቸው በሞት ይቀጣቸዋል?​—1 ዮሐንስ 4:8

ከዚህም በተጨማሪ ሔዋን ከተከለከለው ‘ፍሬ ወስዳ የበላችው’ አዳም በሌለበት ወቅት ነበር፤ ዘገባው “በኋላም ባሏ አብሯት ሲሆን ለእሱም የተወሰነ ሰጠችው፤ እሱም በላ” ይላል።​—ዘፍጥረት 3:6 NW

በመጨረሻም፣ አዳምና ሔዋን የፆታ ግንኙነት ፈጽመው ልጆች በወለዱ ጊዜ አምላክ ይህን በማድረጋቸው አላወገዛቸውም። (ዘፍጥረት 4:1, 2) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የአዳምና የሔዋን ኃጢአት የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው ሳይሆን ቃል በቃል ፍሬውን መብላታቸው ነው።

2 መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ፍላጎትን ማርካትን ይከለክላል?

▪ መልስ፦ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፣ የሰው ልጆችን “ወንድና ሴት” አድርጎ የፈጠራቸው አምላክ እንደሆነ ይናገራል። አምላክ የፍጥረት ሥራው “እጅግ መልካም” እንደሆነ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:27, 31) ከጊዜ በኋላም አምላክ፣ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ለባሎች የሚከተለውን መመሪያ እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል፦ “በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ። . . . ጡቶቿ ዘወትር ያርኩህ።” (ምሳሌ 5:18, 19) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ከፆታ ግንኙነት የሚገኘውን እርካታ ይከለክላል ማለት ይቻላል?

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ የፆታ አካላትን የፈጠረው ባልና ሚስት ዘር መተካት ብቻ ሳይሆን አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር በመግለጽ እርካታ ማግኘት እንዲችሉ አድርጎ ነው። እንዲህ ያለው ግንኙነት እርስ በርስ የሚዋደዱ ወንድና ሴት ያላቸውን አካላዊና ስሜታዊ ፍላጎት የሚያሟላ ነው።

3 መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሕግ ሳይጋቡ አብረው እንዲኖሩ ይፈቅዳል?

▪ መልስ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ሴሰኞችን . . . ይፈርድባቸዋል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ዕብራውያን 13:4) እዚህ ላይ “ሴሰኞች” ተብሎ የተተረጎመው ፖርኒያ የሚለው የግሪክኛ ቃል ሰፊ ትርጉም ያለው ሲሆን ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን ማንኛውንም ዓይነት የፆታ ግንኙነት ያመለክታል። * በመሆኑም ያልተጋቡ ወንድና ሴት ወደፊት ትዳር ለመመሥረት ቢያስቡም እንኳ ሳይጋቡ አብረው መኖራቸው በአምላክ ፊት ስህተት ነው።

አንድ ወንድና ሴት ከልብ ቢዋደዱም እንኳ የፆታ ግንኙነት ከመፈጸማቸው በፊት መጋባት እንዳለባቸው የአምላክ ሕግ ይገልጻል። ማፍቀር እንድንችል አድርጎ የፈጠረን አምላክ ነው። ዋነኛው የአምላክ ባሕርይም ፍቅር ነው። በመሆኑም የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚችሉት የተጋቡ ወንድና ሴት ብቻ እንደሆኑ የገለጸበት በቂ ምክንያት አለው፤ የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።

4 መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ በላይ ማግባትን ይደግፋል?

▪ መልስ፦ አምላክ፣ ሰዎች ከአንድ በላይ እንዲያገቡ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ፈቅዶ ነበር። (ዘፍጥረት 4:19፤ 16:1-4፤ 29:18 እስከ 30:24) ይሁንና ከአንድ በላይ የማግባትን ልማድ ያስጀመረው አምላክ አይደለም። ለአዳም የሰጠው አንዲት ሚስት ብቻ ነበር።

አምላክ፣ አንድ ወንድ አንዲት ሴት ብቻ እንዲያገባ የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስ በድጋሚ ለሰዎች እንዲገልጽ አድርጓል። (ዮሐንስ 8:28) ኢየሱስ ስለ ትዳር ጥያቄ ሲቀርብለት እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቷል፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘በዚህ ምክንያት ሰው ከአባትና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’”​—ማቴዎስ 19:4, 5

ከጊዜ በኋላም ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት።” (1 ቆሮንቶስ 7:2) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ያገባ ወንድ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተለየ ኃላፊነት እንዲሰጠው “የአንዲት ሚስት ባል” መሆን እንዳለበት ይናገራል።​—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 12

5 የትዳር ጓደኛሞች የወሊድ መከላከያ መጠቀማቸው ስህተት ነው?

▪ መልስ፦ ኢየሱስ ተከታዮቹ ልጆች እንዲወልዱ አላዘዘም። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ እንዲህ ዓይነት መመሪያ አልሰጡም። መጽሐፍ ቅዱስ እርግዝናን መከላከልን አንድም ቦታ ላይ አያወግዝም።

በመሆኑም ባለትዳሮች ልጆች ለመውለድ ወይም ላለመውለድ የመወሰን ነፃነት አላቸው። ከዚህም ሌላ ስንት ልጆች እንደሚኖሯቸውና መቼ እንደሚወልዱ መወሰን ይችላሉ። አንድ ባልና ሚስት ፅንስን የማያስወርዱ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን ለመጠቀም ከመረጡ ይህ የራሳቸው ውሳኔና ኃላፊነት ነው። * ማንም ሰው ሊፈርድባቸው አይገባም።​—ሮም 14:4, 10-13

6 ፅንስ ማስወረድ ስህተት ነው?

▪ መልስ፦ ሕይወት በአምላክ ፊት ቅዱስ ነው፤ በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ እንኳ አምላክ እንደ አንድ ሕያው አካል አድርጎ ይመለከተዋል። (መዝሙር 139:16) አምላክ፣ ባልተወለደ ሕፃን ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሰው ተጠያቂ እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። በመሆኑም አምላክ፣ ፅንስ ማስወረድን ሕይወት ከማጥፋት ለይቶ አያየውም።​—ዘፀአት 20:13፤ 21:22, 23 የ1954 ትርጉም

ይሁን እንጂ አንዲት እናት በምትወልድበት ወቅት ድንገተኛ ሁኔታ ቢፈጠርና ከእናትየው ወይም ከሕፃኑ በሕይወት ማትረፍ የሚቻለው አንዳቸውን ብቻ ቢሆን ምን ማድረግ ይቻላል? በዚህ ጊዜ የማንን ሕይወት ለማትረፍ መሞከሩ የተሻለ እንደሚሆን ባልና ሚስቱ መወሰን ይኖርባቸዋል። *

7 መጽሐፍ ቅዱስ ፍቺን ይፈቅዳል?

▪ መልስ፦ አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቺን ይፈቅዳል። ይሁንና ትዳርን ማፍረስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው በአንድ ምክንያት ብቻ ነው፤ ይህንንም ኢየሱስ እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “በዝሙት [ከትዳር ውጭ በሚፈጸም የፆታ ግንኙነት] ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ምንዝር ይፈጽማል።”​—ማቴዎስ 19:9

አምላክ በተንኮልና በማታለል የሚፈጸም ፍቺን ይጠላል። ትዳራቸውን በማይረባ ምክንያት የሚያፈርሱ በተለይ ደግሞ ከሌላ ሰው ጋር ለመኖር ሲሉ የትዳር ጓደኛቸውን የሚተዉ ሰዎች በአምላክ ፊት ተጠያቂ ከመሆን አያመልጡም።​—ሚልክያስ 2:13-16፤ ማርቆስ 10:9

8 አምላክ ግብረ ሰዶምን ይፈቅዳል?

▪ መልስ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዝሙትን በግልጽ የሚያወግዝ ሲሆን ይህም ግብረ ሰዶምን ይጨምራል። (ሮም 1:26, 27፤ ገላትያ 5:19-21) አምላክ ግብረ ሰዶምን እንደሚጠላ መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማ መንገድ የሚገልጽ ቢሆንም “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል” በማለት እንደሚናገርም እናውቃለን።​—ዮሐንስ 3:16

እውነተኛ ክርስቲያኖች ግብረ ሰዶማዊነትን የሚቃወሙ ቢሆንም ለሁሉም ሰዎች ደግነት ያሳያሉ። (ማቴዎስ 7:12) አምላክ “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ” ብሎናል። በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች ለግብረ ሰዶማውያን ጥላቻ የላቸውም።​—1 ጴጥሮስ 2:17

9 በስልክ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት የሥነ ምግባር ብልግና መፈጸም ስህተት ነው?

▪ መልስ፦ አንዳንዶች በስልክ የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ የብልግና ወሬዎችን ያዳምጣሉ ወይም ስለ ፆታ ግንኙነት ተገቢ ያልሆነ ነገር ያወራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በሞባይል ስልኮች ተጠቅመው ለፆታ ብልግና የሚያነሳሱ ምስሎችንና የስልክ መልእክቶችን የሚላላኩም አሉ። ሌሎች በኢንተርኔት አማካኝነት የብልግና ወሬ ያወራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደነዚህ ዓይነት ዘመን አመጣሽ ድርጊቶችን አስመልክቶ በቀጥታ የሚናገረው ነገር የለም። ይሁንና እንዲህ ይላል፦ “ለቅዱሳን የማይገባ ስለሆነ ዝሙትና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ፤ አሳፋሪ ምግባር፣ የማይረባ ንግግርም ሆነ ጸያፍ ቀልድ የማይገቡ ነገሮች ናቸው።” (ኤፌሶን 5:3, 4) በስልክ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት የሚፈጸሙ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ድርጊቶች ሰዎች ስለ ፆታ ግንኙነት የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ ከጋብቻ ውጭ የፆታ ፍላጎታቸውን እንዲያረኩ ይገፋፏቸዋል። እንዲሁም የፆታ ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ ከመርዳት ይልቅ በራሳቸው ፍላጎት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያደርጓቸዋል።

10 መጽሐፍ ቅዱስ ማስተርቤሽንን በተመለከተ ምን ይላል?

▪ መልስ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማስተርቤሽን (ስሜትን ለማነሳሳትና ለማርካት ብሎ የፆታ አካልን የማሻሸት ልማድ) በቀጥታ አይናገርም። ይሁንና የአምላክ ቃል ለክርስቲያኖች የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷል፦ “በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ [ተገቢ ያልሆነ] የፆታ ምኞት . . . ናቸው።”​—ቆላስይስ 3:5

ማስተርቤሽን አንድ ሰው ስለ ፆታ ግንኙነት የተዛባና ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት አመለካከት እንዲኖረው ያደርጋል። ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ ልባዊ ጥረት ለሚያደርጉ ሰዎች አምላክ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ እንደሚሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል።​—2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:13

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.11 ፖርኒያ የሚለው ቃል የፆታ አካላትን አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥር ከነበረው የመጀመሪያ ዓላማ በተለየ መንገድ መጠቀምን የሚያካትቱ ሌሎች ድርጊቶችንም ለምሳሌ ምንዝርን፣ ግብረ ሰዶምንና ከእንስሳት ጋር የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን ያመለክታል።

^ አን.19 በቀዶ ሕክምና ስለማምከን መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል የበለጠ መረጃ ለማግኘት የሰኔ 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 27, 28 ላይ የሚገኘውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” የሚለውን ዓምድ ተመልከት።

^ አን.22 አንዲት ተገድዳ የተደፈረች ሴት ብታረግዝ ፅንሱን ማስወረዷ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ከጥር እስከ መጋቢት 1994 ንቁ! (የግንቦት 22, 1993 ንቁ! [እንግሊዝኛ]) ገጽ 10, 11⁠ን ተመልከት።