በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መለኮታዊው ስም እና አልፎንሶ ዴ ዘሞራ ትክክለኛ ትርጉም ለማዘጋጀት ያደረገው ጥረት

መለኮታዊው ስም እና አልፎንሶ ዴ ዘሞራ ትክክለኛ ትርጉም ለማዘጋጀት ያደረገው ጥረት

መለኮታዊው ስም እና አልፎንሶ ዴ ዘሞራ ትክክለኛ ትርጉም ለማዘጋጀት ያደረገው ጥረት

በ1492 የስፔኑ ንጉሥ ፈርዲናንድና ንግሥት ኢዛቤላ የሚከተለውን አዋጅ አወጡ፦ “አይሁዳውያን ወንዶችና ሴቶች በሙሉ . . . ትልቅ ትንሽ ሳይል በማንኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን፣ ወንድና ሴት አገልጋዮቻቸውን እንዲሁም አይሁዳዊ የሆኑ የቤተሰባቸውን አባላት ይዘው በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ስማቸው ከተጠቀሰው ንጉሣዊ ግዛቶቻችን እንዲወጡ አዝዘናል፤ ዳግመኛ ቢመለሱ ወዮላቸው።”

አይሁዳውያን ከአገር እንዲወጡ የሚያዝዘው ይህ አዋጅ፣ በስፔን የነበረ እያንዳንዱ የአይሁድ ቤተሰብ ከአገር ከመሰደድ ወይም ሃይማኖቱን ከመካድ አንዱን እንዲመርጥ የሚያስገድድ ነበር። ኹዋን ዴ ዘሞራ የሚባል አንድ የአይሁድ መምህር ከአገር ከመባረር ይልቅ የካቶሊክ ሃይማኖትን መቀበልና ዘር ማንዘሮቹ ለብዙ ትውልድ በኖሩባት በስፔን መቅረት እንደሚሻል ሳይሰማው አልቀረም። ኽዋን ትውልዱ አይሁዳዊ በመሆኑ አልፎንሶ የሚባለውን ልጁን በዘሞራ ወደሚገኝ የታወቀ የዕብራይስጥ ትምህርት ቤት ልኮ አስተምሮት ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ አልፎንሶ በላቲን፣ በግሪክኛና በአረማይክ ቋንቋዎች የተካነ ሆነ። አልፎንሶ ትምህርቱን ሲጨርስ በሳላማንካ ዩኒቨርሲቲ የዕብራይስጥ ቋንቋን ማስተማር ጀመረ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በቋንቋ ችሎታው ተጠቅሞ በመላው አውሮፓ የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንን የሚያግዝ ሥራ አከናወነ።

በ1512 አልካላ ዴ ኤናሬስ የሚባለው አዲሱ ዩኒቨርሲቲ የዕብራይስጥ ቋንቋ ጥናትን በሊቀ መንበርነት እንዲመራ አልፎንሶ ዴ ዘሞራን መረጠው። ዘሞራ በዘመኑ ከነበሩት ታዋቂ ምሁራን አንዱ ነበር፤ በዚህም ምክንያት የዩኒቨርሲቲው መሥራች የሆኑት ካርዲናል ሂሜኔስ ዴ ሲስኔሮስ፣ በርካታ ቋንቋዎችን የያዘውንና ትልቅ ግምት የሚሰጠውን ኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ በመተርጎሙ ሥራ እገዛ እንዲያበረክት ጠየቁት። ይህ ባለ ስድስት ጥራዝ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅዱስ ጽሑፉን በዕብራይስጥ፣ በግሪክኛና በላቲን እንዲሁም የተወሰኑ ክፍሎችን በአረማይክ ይዟል። *

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ማሪያኖ ረቢልያ ሪኮ ይህን ፕሮጀክት አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “በካርዲናል [ሲስኔሮስ] ሥራ ውስጥ ከተሳተፉት ወደ ካቶሊክ ሃይማኖት የተለወጡ ሦስት አይሁዳውያን መካከል ከፍተኛ አድናቆት ያተረፈው አልፎንሶ ዴ ዘሞራ ሲሆን እሱም የላቲን፣ የግሪክኛ፣ የዕብራይስጥና የአረማይክ ምሁር ከመሆኑም ሌላ የሰዋስው ሕጎችን ጠንቅቆ የሚያውቅ መምህር፣ ፈላስፋና የታልሙድ ሊቅ ነበር።” ዘሞራ ያደረገው ጥናት፣ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት ቅዱስ ጽሑፉ የተጻፈባቸውን የመጀመሪያ ቋንቋዎች ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል ወደሚል ድምዳሜ መራው። ዘሞራ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አንጻር በ16ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ማበብ የጀመረው ሕዳሴ አቀንቃኞች ከነበሩት ሰዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል።

ይሁን እንጂ ዘሞራ የኖረበት ዘመንና ቦታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማካሄድ አስቸጋሪና አደገኛ ነበር። ስፓኒሽ ኢንክዊዚሽን በመባል የሚታወቀው የሮም ካቶሊክ ችሎት ያስነሳው ስደት እየተፋፋመ ከመሆኑም ሌላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ “ተቀባይነት ያለው” ብቸኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የላቲን ቩልጌት ነበር። ያም ሆኖ ከመካከለኛው ዘመን (ከ5ኛው-15ኛው መቶ ዘመን) ወዲህ የነበሩ የካቶሊክ ምሁራን የላቲን ቩልጌት ብዙ ስህተቶች እንዳሉበት ገልጸው ነበር። በመሆኑም በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ አልፎንሶ ዴ ዘሞራና ሌሎችም ለዚህ መፍትሔ የሚሆን ሥራ ማከናወኑን ተያያዙት።

‘ለመዳን የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ማግኘት ያስፈልጋል’

ዘሞራ ካከናወናቸው ሥራዎች መካከል በተለምዶ “ብሉይ ኪዳን” ተብሎ የሚጠራው ክፍል የዕብራይስጥ እትምና የላቲን ትርጉም ጉልህ ስፍራ እንደሚሰጣቸው ጥርጥር የለውም። ዘሞራ፣ ይህ ሥራው በርካታ ቋንቋዎችን የያዘውን የኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ሳያስብ አልቀረም። ካዘጋጃቸው ቅጂዎች አንዱ በማድሪድ፣ ስፔን አቅራቢያ በሚገኘው ኤል ኤስኮሪያል ተብሎ የሚጠራ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። ጂ-አይ-4 በሚል ስያሜ የተመዘገበው ይህ ቅጂ ሙሉውን የዘፍጥረት መጽሐፍ በዕብራይስጥ እንዲሁም ቃል በቃል የተተረጎመውን የዚህን መጽሐፍ የላቲን ትርጉም ይዟል።

በመቅድሙ ላይ የሚከተለው ሐሳብ ይገኛል፦ “ሕዝቦች መዳን እንዲያገኙ ቅዱሳን መጻሕፍት ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ሊተረጎሙ ይገባል። . . . ታማኝ የሆኑ ሰዎች፣ ቃል በቃል የተተረጎመ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይኸውም ለእያንዳንዱ የዕብራይስጥ ቃል አቻ የላቲን ፍቺ የተሰጠበት እትም ማግኘታቸው የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶናል።” አልፎንሶ ዴ ዘሞራ እውቅና ያገኘ የዕብራይስጥ ምሁር ስለነበረ እንዲህ ያለ አዲስ የላቲን ትርጉም ለማዘጋጀት አስፈላጊው ብቃት ነበረው።

‘ለመንፈሴ ማረፊያ ማግኘት አልቻልኩም’

በአንድ በኩል ሲታይ ስፔን በ16ኛው መቶ ዘመን እንደ ዘሞራ ላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ሥራ ተስማሚ ቦታ ነበረች። ምክንያቱም በመካከለኛው ዘመን ስፔን የአይሁድ ባሕል ማዕከል ሆና ነበር። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚከተለው ይላል፦ “ስፔን በመካከለኛው ዘመን፣ ብዛት ያላቸው ሙስሊሞችና አይሁዳውያን ይኖሩባት ስለነበር በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የተለያየ ዘርና ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች የሚገኙባት ብቸኛዋ አገር ነበረች፤ ይህም በመካከለኛው ዘመን መገባደጃ አካባቢ በሃይማኖት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በኪነ ጥበብና በሥነ ሕንፃ ረገድ በስፔን ለታየው እድገት መሠረት ሆኗል።”

በስፔን ብዙ አይሁዳውያን ይኖሩ ስለነበር በእጅ የተገለበጡ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች እንደ ልብ ይገኙ ነበር። እነዚህ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች፣ ስፔን ውስጥ በበርካታ ቦታዎች የሚኖሩ አይሁዳውያን ጸሐፍት፣ በምኩራቦች ውስጥ በሕዝብ ፊት ለማንበብ እንዲያገለግሉ ብለው በጥንቃቄ የገለበጧቸው ነበሩ። ላዘረስ ጎልድሽሚት፣ የጥንቶቹ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እትሞች (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “በአይሁድ ምሁራን ዘንድ በትክክለኛነታቸው ስመ ጥር የሆኑት በስፔንና በፖርቱጋል የታተሙት የፔንታቱች [አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት] እትሞች ብቻ ሳይሆኑ ለእነዚህ እትሞችና ምሁራን ላዘጋጇቸው በርካታ ቋንቋዎችን የያዙ ትርጉሞች መሠረት የሆኑት በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች ጭምር ነበሩ።”

ስፔን መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎሙ ሥራ ተስማሚ ቦታ ብትሆንም ይህን ሥራ ለማከናወን ያሰቡ ሰዎች የተቃውሞ ደመና አጥልቶባቸው ነበር። በ1492 ለንጉሥ ፈርዲናንድና ለንግሥት ኢዛቤላ የሚዋጋው የካቶሊክ ሠራዊት፣ ሙሮች በስፔን የነበራቸውን የመጨረሻ ይዞታ ተቆጣጠረ። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በዚያው ዓመት ንጉሡና ንግሥቲቱ የአይሁድን ሃይማኖት የሚከተሉ ሁሉ ከስፔን እንዲባረሩ አዋጅ አወጡ። ከአሥር ዓመት በኋላ ሙስሊሞችም ተመሳሳይ በሆነ አዋጅ ተባረሩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስፔን ውስጥ ካቶሊክ የመንግሥት ሃይማኖት ሆነ፤ ሌላ ሃይማኖት መከተል አይፈቀድም ነበር።

ታዲያ ይህ ሃይማኖታዊ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎሙ ሥራ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን? በአልፎንሶ ዴ ዘሞራ ላይ የደረሰው ነገር ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ይህ አይሁዳዊ ምሁር ወደ ካቶሊክ ሃይማኖት የተለወጠ ቢሆንም እንኳ የስፔን ሃይማኖታዊ ባለሥልጣናት የኋላ ታሪኩን ችላ ብለው ለማለፍ ፈቃደኞች አልሆኑም። ካርዲናል ሲስኔሮስ፣ በርካታ ቋንቋዎችን የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት ወደ ካቶሊክ ሃይማኖት የተቀየሩ አይሁዳውያንን በመጠቀማቸው አንዳንድ ተቃዋሚዎች ነቅፈዋቸዋል። እነዚህ ተቃውሞዎች ዘሞራን በጣም ጎድተውታል። በማድሪድ ዩኒቨርሲቲ በሚገኝ አንድ ጽሑፍ ላይ ዘሞራ እንዲህ በማለት ምሬቱን ገልጿል፦ “ጓደኞቼ በሙሉ የተዉኝና የጠሉኝ ከመሆኑም ሌላ ጠላቶች ስለሆኑብኝ ለመንፈሴም ሆነ ለእግሬ ማረፊያ ማግኘት አልቻልኩም።”

ከዘሞራ ዋነኛ ጠላቶች አንዱ የቶሌዶ ሊቀ ጳጳሳት የነበሩትና ቆየት ብሎም የስፓኒሽ ኢንክዊዚሽን ዋነኛ ቅጣት አስፈጻሚ የሆኑት ኹዋን ታቬራ ነበሩ። ዘሞራ በታቬራ ጥቃት በጣም ከመማረሩ የተነሳ ለሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቤቱታ እስከ ማቅረብ ደርሷል። አቤቱታው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ብፁዕነትዎ እንዲረዱን እንጠይቃለን እንዲሁም እንማጸናለን፤ . . . ጠላታችን ከሆኑት . . . ከዶን ኹዋን ታቬራ አስጥሉን። ምንም ፋታ ሳይሰጡ በየቀኑ ብዙ መከራ እያደረሱብን ነው። . . . በኹዋን ታቬራ አመለካከት ለእርድ እንደተዘጋጀ እንስሳት ስለሆንን በእርግጥም በታላቅ ጭንቅ ውስጥ እንገኛለን። . . . ብፁዕነትዎ ላቀረብነው አቤቱታ ምላሽ ቢሰጡ ‘ያህዌህ ጥበቃ ያደርግልዎታል፤ እግርዎንም ከመሰናከል ይጠብቀዋል።’ (ምሳሌ 3:23)” *

አልፎንሶ ዴ ዘሞራ የተወው ቅርስ

ዘሞራ እንዲህ ያለ ጥቃት ቢደርስበትም ሥራውን የቀጠለ ሲሆን ስኬታማም ሆኗል፤ እሱ ያከናወነውን ሥራ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተጠቅመውበታል። ዘሞራ ቅዱሳን መጻሕፍትን በዘመኑ በሚነገሩ ቋንቋዎች ባይተረጉምም ለሌሎች ተርጓሚዎች ታላቅ ውለታ ውሏል። እሱ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ምንጊዜም ሁለት ዓይነት ምሁራን እንደሚያስፈልጉ ማስታወስ አለብን። በመጀመሪያ፣ በዕብራይስጥና በአረማይክ እንዲሁም በግሪክኛ ጥራት ያለውና ትክክለኛ የሆነ የቅዱስ ጽሑፉ ቅጂ እንዲኖር ቅዱስ ጽሑፉ መጀመሪያ በተጻፈባቸው በእነዚህ ቋንቋዎች የተዘጋጁትን በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች የሚያጠኑ ምሁራን መኖር አለባቸው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእነዚህ ምሁራን ሥራ ላይ ተመሥርተው መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋቸው የሚተረጉሙ ሰዎች ያስፈልጋሉ።

አልፎንሶ ዴ ዘሞራ፣ በመጨረሻ በ1522 በታተመው የኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት ውስጥ የተካተተውን የዕብራይስጥ ጽሑፍ በማዘጋጀቱና በማረሙ ሥራ ዋነኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ምሁር ነው። (በዚህ ሥራው ላይ ያካተተው የዕብራይስጥ-ላቲን መዝገበ ቃላትና የዕብራይስጥ ሰዋስው የብዙ ተርጓሚዎችን ሥራ የሚያቀል ነው።) በዘሞራ ዘመን የኖረው ኢራስመስም በተለምዶ “አዲስ ኪዳን” እየተባሉ ለሚጠሩት የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የዘሞራ ዓይነት ጽሑፍ አዘጋጅቷል። እነዚህ ታርመው የተጣሩ ጽሑፎች በዕብራይስጥና በግሪክኛ ተዘጋጅተው መውጣታቸው ሌሎች ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስን በሕዝቡ ቋንቋ የመተርጎሙን ታላቅ ሥራ ማከናወን ቀላል እንዲሆንላቸው አድርጓል። የኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎትን የዕብራይስጥ ክፍል ከተጠቀሙት የመጀመሪያ ተርጓሚዎች አንዱ ዊልያም ቲንደል ሲሆን ቲንደል ይህን ጽሑፍ መሠረት በማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሟል።

በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት መሰራጨቱ፣ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ይበልጥ እንድናውቅ ለማድረግ ሲሉ ሕይወታቸውን ለዚህ ሥራ ለሰጡ እንደ ዘሞራ ያሉ ሰዎች ልፋት መታሰቢያ ነው። ዘሞራ እንደገለጸው ሰዎች መዳናቸው የተመካው የአምላክን ቃል በመረዳታቸውና መመሪያውን በመከተላቸው ላይ ነው። (ዮሐንስ 17:3) ይህ እንዲሆን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሊገባቸው በሚችል ቋንቋ መተርጎሙ የግድ ነው፤ መልእክቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብና አእምሮ ሊነካ የሚችለው ይህ ከሆነ ብቻ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 የኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ሰፋ ያለ ሐሳብ ለማግኘት የሚያዝያ 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 28-31 ተመልከት።

^ አን.15 ዘሞራ ለሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ባቀረበው አቤቱታ ላይ የአምላክን የማዕረግ ስም ሳይሆን መለኮታዊውን ስም መጠቀሙ ልብ ሊባል ይገባዋል። ወደ ስፓንኛ በተተረጎመው የዘሞራ አቤቱታ ላይ መለኮታዊው ስም “ያህዌህ” ተብሎ ተገልጿል። በላቲን በተጻፈው በመጀመሪያው አቤቱታ ላይ ይህ ስም እንዴት እንደተቀመጠ በእርግጠኝነት አይታወቅም። የዘሞራን ትርጉምና በመለኮታዊው ስም መጠቀሙን በተመለከተ በገጽ 19 ላይ የሚገኘውን “መለኮታዊውን ስም መተርጎም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕሎች]

መለኮታዊውን ስም መተርጎም

የዕብራይስጥን ቋንቋ ጠንቅቆ የሚያውቀው አልፎንሶ ዴ ዘሞራ መለኮታዊውን ስም በላቲን ፊደላት ያስቀመጠበት መንገድ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። በዚህ ገጽ ላይ ባለው ፎቶግራፍ ላይ እንደሚታየው የዘፍጥረትን መጽሐፍ የዕብራይስጥ ጽሑፍ በላቲን ቋንቋ ቃል በቃል እየፈታ ሲያስቀምጥ የአምላክን ስም በሕዳጉ ላይ “jehovah” (ይሖዋ) ብሎ ጽፎታል።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዘሞራ፣ መለኮታዊው ስም በዚህ መንገድ ወደ ላቲን መተርጎሙን ተቀብሎታል። በ16ኛው መቶ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዋና ዋናዎቹ የአውሮፓ ቋንቋዎች በተተረጎመ ጊዜ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ይህን አጻጻፍ ወይም ከዚህ ጋር በጣም የሚቀራረብ አጻጻፍ ተጠቅመዋል፤ ከእነዚህም መካከል ዊልያም ቲንደል (እንግሊዝኛ፣ 1530)፣ ዜባስትያን ሙንስተር (ላቲን፣ 1534)፣ ፒየር ሮቤር ኦሊቬታ (ፈረንሳይኛ፣ 1535) እና ካሲዮደሮ ዴ ሬና (ስፓንኛ፣ 1569) ይገኙበታል።

በመሆኑም ዘሞራ በመለኮታዊው ስም ላይ መጀመሪያ ብርሃን ከፈነጠቁ በርካታ የ16ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አንዱ ሆኗል። ሰዎች ስለ አምላክ ስም እንዳያውቁ እንቅፋት የሆነው ዋነኛው ምክንያት የአምላክ ስም እንዲጠራ የማይፈቅደው የአይሁዳውያን አጉል እምነት ነው። ይህ የአይሁዳውያን እምነት ባሳደረው ተጽዕኖ ምክንያት የሕዝበ ክርስትና የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች (ለምሳሌ የላቲኑን ቩልጌት የተረጎመው ጀሮም) መለኮታዊውን ስም “ጌታ” ወይም “አምላክ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ መጠሪያዎች ተክተውታል።

[ሥዕል]

ዘሞራ የአምላክ ስም የሚጻፍባቸውን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት “JEHOVAH” በማለት ወደ ላቲን ተርጉሟቸዋል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስፔን ንጉሥና ንግሥት ያወጡት አዋጅ፣ 1492

[የሥዕል ምንጭ]

Decree: Courtesy of the Archivo Histórico Provincial, Ávila, Spain

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአልካላ ዴ ኤናሬስ ዩኒቨርሲቲ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዘሞራ የዕብራይስጡን ጽሑፍ በላቲን ቋንቋ ቃል በቃል እየፈታ ያዘጋጀው ጽሑፍ የመጀመሪያ ገጽ