በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር በ2012 ትጠፋ ይሆን?

ምድር በ2012 ትጠፋ ይሆን?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ምድር በ2012 ትጠፋ ይሆን?

▪ “አፖካሊፕስ [የዓለም መጨረሻ] ይመጣል ብለው የሚያምኑ ሰዎች ወደ አንዲት የፈረንሳይ መንደር ጎርፈዋል። . . . እነዚህ ሰዎች፣ 5,125 ዓመት ርዝመት ያለው የጥንቶቹ ማያዎች የቀን መቁጠሪያ በሚያበቃበት ዕለት ይኸውም ታኅሣሥ 21 ቀን 2012 የዓለም መጨረሻ እንደሚመጣ ያምናሉ።”​—ቢቢሲ የዜና አገልግሎት

የሃይማኖት መሪዎችም ሆኑ የሳይንስ ሊቅ ነን ባዮች እንዲሁም ሌሎች የ21ኛው መቶ ዘመን ነቢያት ጥፋት እንደሚመጣ ቢተነብዩም ምድር በ2012 አትጠፋም። እንዲያውም ምድራችን በዚያ ዓመት ቀርቶ መቼም ቢሆን አትጠፋም።

መጽሐፍ ቅዱስ “ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች” ይላል። (መክብብ 1:4) ኢሳይያስ 45:18⁠ም እንዲህ ይላል፦ “ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።’”

አንድ አፍቃሪ አባት ልጁን ለማስደሰት ሲል ረጅም ጊዜ ወስዶ አሻንጉሊት ወይም ሌላ መጫወቻ ከሠራ በኋላ ልጁ ገና መጫወት ሲጀምር መጫወቻውን ቀምቶ ይሰባብረዋል? እንዲህ ማድረግ ክፋት ነው! አምላክ ምድርን የፈጠረበት ዋነኛው ምክንያት የእጁ ሥራ የሆኑትን የሰው ልጆች ለማስደሰት ነው። አምላክ፣ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ለሆኑት ለአዳምና ለሔዋን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” ብሏቸው ነበር። ዘገባው ሲቀጥል እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ።” (ዘፍጥረት 1:27, 28, 31) አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ አልቀየረም፤ በመሆኑም ምድራችን እንድትጠፋ አይፈቅድም። ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች በተመለከተ እንደሚከተለው በማለት አስረግጦ ተናግሯል፦ “ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።”​—ኢሳይያስ 55:11

ይሖዋ፣ ምድር እንድትጠፋ ባይፈቅድም “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [ለማጥፋት]” ወስኗል። (ራእይ 11:18) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚከተለው በማለት ቃል ገብቷል፦ “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።”​—ምሳሌ 2:21, 22

ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ቀኑን ማንም ሰው አያውቀውም። ኢየሱስ “ስለዚያ ቀን ወይም ሰዓት ከአብ በቀር በሰማይ ያሉ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም” ብሏል። (ማርቆስ 13:32) የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክ ክፉዎችን የሚያጠፋበትን ጊዜ ለመተንበይ አይሞክሩም። መጨረሻው መቅረቡን የሚጠቁመውን “ምልክት” በንቃት የሚከታተሉና መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር የሚያምኑ ቢሆንም “ፍጻሜው” መቼ እንደሚሆን በትክክል ማወቅ አይችሉም። (ማርቆስ 13:4-8, 33፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) ቀኑን የሚያውቁት የሰማዩ አምላካቸውና ልጁ እንደሆኑ ያምናሉ።

እስከዚያው ድረስ ግን የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ራሳቸውን ያስጠምዳሉ፤ በሰማይ የሚገኘው ይህ መንግሥት ወደፊት ምድርን የሚገዛ ሲሆን ፕላኔታችንን ሰላም የሰፈነባት ገነት እንድትሆን ያደርጋታል። በዚያን ጊዜ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”​—መዝሙር 37:29

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Image Science and Analysis Laboratory, NASA-Johnson Space Center