የተንጣለለውን ነጭ ምድረ በዳ መጎብኘት
ከኖርዌይ የተላከ ደብዳቤ
የተንጣለለውን ነጭ ምድረ በዳ መጎብኘት
እኔና ባለቤቴ ማለዳ ተነስተን የክረምቱን አየር ለመቃኘት መጋረጃዎቹን ገለጥ አድርገን ተመለከትን። ጥርት ያለውን ሰማይ ስንመለከት በጣም ተደሰትን! ከአርክቲክ ክልል በስተሰሜን ወደሚገኘውና ፊንማርክስቪደ ወደሚባለው ትልቅ ተራራ ሄደን ለሦስት ቀን ለመስበክ ተዘጋጅተናል።
በኖርዌይ ክረምቱ በጣም ቀዝቃዛ በመሆኑ በሰሜናዊው ክፍል ወደሚገኘው ምድረ በዳ ለመሄድ ስናስብ ትንሽ ስጋት ተሰማን። ደግነቱ የምንጓዘው በአካባቢው ከሚኖሩ ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ነው። እነሱም ጉዞው ምን ሊመስል እንደሚችል ስለሚያውቁ ጥሩ ምክር ሰጡን።
እዚህ አካባቢ ብዙ መንገዶች የሉም ማለት ይቻላል። ስለዚህ ሩቅ በሆኑ አካባቢዎች ወደሚኖሩ ሰዎች ለመሄድ ከሁሉ የተሻለው የመጓጓዣ ዘዴ በበረዶ ላይ የሚንሸራተቱ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ነው። በእነዚህ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም በተጎታቹ ላይ ልብሳችንን፣ ስንቃችንንና ተጨማሪ ነዳጅ ጭነን ተነሳን። ከፊት ለፊታችን ነጩ ተራራ ጉብ ብሎ ይታየናል፤ በረዶው ደግሞ የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍበት እንደ አልማዝ ያብረቀርቃል። አካባቢው በጣም ውብና ማራኪ ነው!
ፊንማርክስቪደ የአጋዘን፣ የቀበሮና የአቆስጣ ዝርያ የሆኑ እንስሳት እንዲሁም ሊኒክስ የተባለው የድመት ዝርያ በተጨማሪም ጥንቸልና በቁጥር ጥቂት የሆኑ ድቦች የሚኖሩበት ቦታ ነው። ዋናው ትኩረታችን ግን ራቅ ብሎ በሚገኘው በዚህ አካባቢ በሚኖሩት ሰዎች ላይ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከሴሚ ሕዝብ ጋር ለመገናኘት ጓጉተናል፤ እነዚህ ሰዎች የደጋ አጋዘኖችን በመጠበቅ ወይም በተራራ ላይ በተዘጋጁ ጊዜያዊ ማረፊያዎች ውስጥ በመሥራት ይተዳደራሉ።
መጀመሪያ ካረፍንበት ቤት ደጃፍ ላይ፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር በበረዶ እየተንሸራተቱ አገር አቋርጠው ከመጡ የተወሰኑ ወጣቶች ጋር ተገናኘን። እነሱም ቆም ብለው ምን እየሠራን እንደሆነ ጠየቁን። እኛም ስለ ሥራችን በደስታ ነገርናቸው። ስንሰነባበትም ከመካከላቸው አንዱ “ይቅናችሁ!” አለን። ከዚያም በተሽከርካሪዎቻችን ላይ ወጥተን በረዶ የተጋገረበትን ሐይቅና በበረዶ የተሸፈነውን ጠፍ መሬት አቋርጠን ሄድን። በጉዟችን ላይ የደጋ አጋዘን መንጋ እናይ ይሆን?
ወደ አንዲት ትንሽ ጎጆ ስንሄድ አንድ ሰው ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጠን። ሰውየው እዚህ ቦታ ነዋሪ ከሆኑት ጥቂት ሰዎች አንዱ ነው። በተሽከርካሪያችን ላይ የገጠምነው ተጎታች መሰበሩን ሲያይ ሊጠግንልን እንደሚችል ነገረን። ሥራውን የሚሠራው ቀስ ብሎ ነው፤ ደግሞም በዚህ አካባቢ ያሉ ሰዎች አይቻኮሉም። የእሱ ሁኔታ እኛንም ዘና እንድንል አደረገን። ተጎታቹን ከጠገነልን በኋላ አመሰገንነው፤ ከዚያም አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቂት ነጥቦችን አሳየነው። እሱም በትኩረት
አዳመጠን። ስንለያይ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ እንዲሁም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ሰጠነው። እሱም ፈገግ ብሎ “ለጉብኝታችሁ አመሰግናለሁ” አለን።የተወሰኑ ሰዎችን ካነጋገርን በኋላ ምሽት እየተቃረበ ስለመጣ ወደምናድርበት ቦታ ለመሄድ ተነሳን። በዚህ ጊዜ በድንገት አንድ ቀበሮ አየን። ቀይ ቀለም ያለው ፀጉሩ ነጭ ከሆነው በረዶ ጋር ሲዳመር ውብ የሆነ እይታ ፈጥሯል። ቀበሮው ቆም ብሎ አትኩሮ ከተመለከተን በኋላ ጉዞውን ቀጠለ። በዚህ ጊዜ አመዳይ መጣል ስለ ጀመረ የምንሄድበትን አቅጣጫ መለየት አዳጋች ሆነብን። በመጨረሻ ማደሪያ ስፍራችንን ስናየው በጣም ደስ አለን! ምድጃው ላይ እሳት ስላቀጣጠልን ክፍሉ ቀስ በቀስ እየሞቀ ሄደ። ቀኑን ሙሉ ተሽከርካሪያችን ሲያንገጫግጨን ስለዋለ በጣም የደከመን ቢሆንም በእጅጉ ተደስተናል።
ጠዋት ላይ ድካማችን ገና አልለቀቀንም ነበር። ዕቃችንን ተሽከርካሪያችን ላይ እንደገና ከጫንን በኋላ አንድን ወንዝ ተከትለን ቁልቁል በመጓዝ በተራራ ላይ ወደሚገኝ ሌላ ማረፊያ ሄድን። በዚህ አካባቢ ከአንድ ወጣት ጋር ተገናኘንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንዳንድ የሚያንጹ ሐሳቦችን አካፈልነው። እሱም ወደ መንገዳችን ለመመለስ የሚያስችል አቋራጭ መንገድ በደግነት አሳየን።
እዚህ አካባቢ የምንቆይበት የመጨረሻው ቀን ደረሰ። ወደ ስታበርስዳለን ብሔራዊ ፓርክ ስንገባ ትኩረታችን በዙሪያችን ባለው ዕፁብ ድንቅ መልክዓ ምድር ላይ አረፈ፤ ከርቀት የሚታዩት በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮች የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍባቸው ያንጸባርቃሉ። ከፊት ለፊታችን የደጋ አጋዘን መንጋ ሲመጣ ተመለከትን! የደጋ አጋዘኖቹ ከበረዶ በታች የሚበቅለውን ተክል በትልልቅ ኮቴዎቻቸው ቆፈር ቆፈር አድርገው በማውጣት ተረጋግተው እየበሉ ነው። ከዚያ ራቅ ብሎ የሴሚ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ አንድ ሰው በበረዶ ተሽከርካሪው ላይ ተቀምጦ አየነው። እሱም በጸጥታ የደጋ አጋዘኖቹን እየጠበቀ ነው። የሰውየው ውሻም መንጋው እንዳይበታተን በጥንቃቄ ይጠብቃል። ውሻው ለአንድ አፍታ ቆም ብሎ እኛ ወዳለንበት አቅጣጫ አነፈነፈ። ይሁንና ወዲያውኑ ወደ ሥራው ተመለሰ። እኛም መንጋውን ለሚጠብቀው ሰው መልእክታችንን ነገርነው። ግለሰቡ የሚቀረብ ሰው ሲሆን መልእክታችንንም አዳመጠ።
ወደ ቤታችን በምንመለስበት ጊዜ 300 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው አካባቢ ላይ ስላገኘናቸው ሰዎች እያሰብን ነበር። ተንጣልሎ በሚታየው በዚህ ነጭ ምድረ በዳ ለሚኖሩት ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ አነስተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻላችን ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማናል።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Norway Post