በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተፈጥሮ አደጋዎች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?

የተፈጥሮ አደጋዎች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?

ስለ አደጋ የሚገልጹ ዘገባዎች ዜናውን የተቆጣጠሩት ይመስላል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በርካታ ሰዎች የአደጋዎች ሰለባ እየሆኑ ነው። በቤልጅየም ስለ ተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጠና አንድ ማዕከል በ2010 ብቻ 373 አደጋዎች እንደተከሰቱና በዚህም ሳቢያ ቢያንስ 296,000 ሰዎች እንደሞቱ ዘግቧል።

ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ ሪፖርት የተደረጉት የተፈጥሮ አደጋዎች ቁጥርም ከዚያ በፊት ከነበሩት አሥርተ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ከ1975 እስከ 1999 ባሉት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ የደረሱት አደጋዎች ቁጥር ከ300 ያንሳል። ይሁንና ከ2000 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ ወደ 400 የሚጠጉ አደጋዎች ተከስተዋል። በዚህም የተነሳ አንዳንዶች “በአሁኑ ጊዜ አደጋዎች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?” ብለው ይጠይቃሉ፤ አንተስ እንዲህ ይሰማሃል?

ሰዎች እንዲህ ያሉ አደጋዎችን የሚያመጣው አምላክ እንደሆነ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ቢሆንም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። በዛሬው ጊዜ በብዙዎች ላይ እየደረሱ ላሉት አደጋዎች ተጠያቂው አምላክ አይደለም። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን የተፈጥሮ አደጋዎች እንደሚኖሩ አስቀድሞ ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 24:7, 8 ላይ “በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው” ብሏል። ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች እንደሚከሰቱ አስቀድሞ የተናገረው ለምንድን ነው? የእነዚህ አደጋዎች መከሰት ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ከላይ ያለውን ሐሳብ የተናገረው ደቀ መዛሙርቱ ላቀረቡለት “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ [ምልክት] ምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ነበር። (ማቴዎስ 24:3) ከላይ የተጠቀሱትን የመሰሉ አደጋዎችን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮች እንደሚከሰቱ ነገራቸው። ከዚያም የሚከተለውን ትልቅ ትርጉም ያለው ሐሳብ ተናገረ፤ “እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እወቁ” አላቸው። (ሉቃስ 21:31) እንግዲያው እነዚህ የተፈጥሮ አደጋዎች በቅርቡ ጉልህ ለውጥ እንደሚመጣ ስለሚጠቁሙ ለእኛ ትልቅ ትርጉም አላቸው።

ለአደጋዎች አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች

ያም ሆኖ ብዙ ሰዎች ‘ለእነዚህ አደጋዎች ተጠያቂው አምላክ ካልሆነ ታዲያ ማን ነው? ወይም የአደጋዎቹ መንስኤ ምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። መልሱን ማግኘት የምንችለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን “መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው” የሚለውን ሐቅ ከተገነዘብን ብቻ ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ይህ ጥቅስ በዓለም ላይ ለሚታየው አስጨናቂ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ ተጠያቂው አምላክ ሳይሆን “ክፉው” የተባለው የእሱ ጠላት እንደሆነ በግልጽ ያሳያል፤ ይህ ክፉ ጠላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዲያብሎስ” ተብሎም ተጠርቷል።​—ራእይ 12:9, 12

የራሱን ፍላጎት ስለማሟላት ብቻ የሚያስበው ይህ የአምላክ ጠላት ዓላማው እስከተሳካለት ድረስ ለሰው ልጆች ደኅንነት ደንታ የለውም። መላው ዓለም በቁጥጥሩ ሥር ስለሆነ ሰዎችም ለሌሎች ደንታ ቢስ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰው ልጆች እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ እንደሚያዳብሩ ሲገልጽ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) ከዚህ አንጻር ዲያብሎስ በሚመራው ዓለም ውስጥ እነዚህና ሌሎች አምላካዊ ያልሆኑ ባሕርያት ሰፊ ተቀባይነት ማግኘታቸው ምንም አያስገርምም። ዲያብሎስ፣ ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት በሚንጸባረቅበት መንገድ የምድርን ሀብት መበዝበዝን የሚያበረታታ ሲሆን ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ለጉዳት ይዳርጋል።

በዛሬው ጊዜ የሚታየው ስግብግብነት የሚንጸባረቅበት አካሄድ ለአደጋዎች ምክንያት የሚሆነው እንዴት ነው? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም ዙሪያ የሚደርሱ አደጋዎችን አስመልክቶ ያቀረበው ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ለአደጋ በተጋለጡ አካባቢዎች ለምሳሌ ጎርፍ በሚያጠቃቸው ቦታዎች ላይ በብዛት እንዲሰፍሩ ይደረጋል። በተጨማሪም የደን መመንጠርና ረግረጋማ ቦታዎች መጥፋታቸው ምድራችን አደጋዎችን የመቋቋም አቅሟ እንዲቀንስ አድርጓል።” በዚህ ላይ ደግሞ ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ጋዝ ወደ ከባቢ አየር በመልቀቃቸው የተነሳ የምድር ሙቀት መጨመሩ “ዓለም አቀፍ የአየር ሁኔታ ለውጥ እንዲከሰትና የባሕር መጠን ከፍ እንዲል” እንዳደረገ ዘገባው አክሎ ገልጿል። ከፍተኛ መጠን ያለው ጋዝ ወደ ከባቢ አየር እንዲለቀቅ ምክንያት የሆነው ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት የሚደረገው ጥረት እንደሆነ ቢነገርም እውነታው ሲታይ ግን ለዚህ መንስኤው ዓለማችንን ያጥለቀለቀው የራስ ወዳድነትና የስግብግብነት መንፈስ ነው።

በመሆኑም የሰው ልጆች የሚከተሉት በሚገባ ያልታሰበበት አካሄድ አደጋዎች የሚያስከትሉትን ጉዳት እንዳባባሰው በርካታ ባለሙያዎች ተገንዝበዋል። እንዲያውም ሰይጣን፣ አደጋዎች በሰዎች ላይ የሚያስከትሉትን መከራ ለማባባስ የሚያደርገውን ጥረት የሰው ልጆች ራሳቸው እየደገፉት ነው ሊባል ይችላል።

ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ለአብዛኞቹ አደጋዎች መንስኤው የሰው ልጆች ግድ የለሽነት ነው። አንዳንድ ጊዜ አደጋው የተከሰተበት ቦታ በሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። በበርካታ የዓለም ክፍሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ያደረሱት ጉዳት እንዲባባስ የሚያደርገው አንዱ ምክንያት ክፉ የሆኑ ሰዎች የሚፈጽሙት የማጭበርበር ተግባር ነው፤ ሌላው ደግሞ በዓለማችን ላይ በሚታየው ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ ልዩነት ሳቢያ ብዙ ሰዎች ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ለመኖር መገደዳቸው ነው። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ሰዎች አደጋ የሚደርስባቸው በሌሎች ግድ የለሽነት ወይም ስህተት የተነሳ ሳይሆን ‘ሁሉም ሰው መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ስለሚያጋጥሙት’ ነው።​—መክብብ 9:11 NW

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በምትኖርበት አካባቢ የተፈጥሮ አደጋ ቢደርስ ሁኔታውን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? አደጋ ሲከሰት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ምን ማድረግ እንደሚቻል ከዚህ በመቀጠል እንመለከታለን።