በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

አብርሃም ልጁን መሥዋዕት እንዲያደርግ አምላክ የጠየቀው ለምንድን ነው?

አብርሃም ልጁን መሥዋዕት እንዲያደርግ አምላክ የጠየቀው ለምንድን ነው?

▪ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ እንደሚገልጸው አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ይሖዋ አምላክ ጠይቆት ነበር። (ዘፍጥረት 22:2) አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ አምላክ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ያቀረበበትን ምክንያት መረዳት ይከብዳቸዋል። ካረል ዴላኒ የተባሉ ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “ልጅ እያለሁ ይህን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሰማ በጣም ተበሳጭቼ ነበር። እንዲህ ያለ ነገር የሚጠይቅ ምን ዓይነት አምላክ ነው?” እኚህ ፕሮፌሰር እንዲህ ዓይነት ስሜት ለምን ተሰማቸው ባንልም ሁኔታውን ለመረዳት የተወሰኑ ነጥቦችን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ያላደረገውን ነገር እንመልከት። አብርሃም ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ይህን እንዲያደርግ አልፈቀደም፤ ከዚያም በኋላ ቢሆን አምላክ ለማንም ሰው እንዲህ ያለ ጥያቄ አቅርቦ አያውቅም። ይሖዋ ልጆችን ጨምሮ ሁሉም አገልጋዮቹ ረጅምና የሚያረካ ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት እንዲያደርግ ይሖዋ የጠየቀበት ልዩ ምክንያት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ አምላክ፣ የገዛ ልጁ * ኢየሱስ ለእኛ ሲል እንዲሞት እንደሚፈቅድ ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 20:28) ይሖዋ፣ ልጁ እንዲሞት ሲፈቀድ ምን ያህል ትልቅ መሥዋዕት እንደሚከፍል እንድንገነዘብ ፈልጎ ነበር። አብርሃምን የጠየቀው ነገር እሱ ወደፊት የሚከፍለውን መሥዋዕት ሕያው በሆነ መንገድ የሚያሳይ ምሳሌ ነበር። እንዴት?

አምላክ ለአብርሃም የተናገረውን ሐሳብ እንመልከት፦ “የምትወደውን አንዱን ልጅህን፣ ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ . . . የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው።” (ዘፍጥረት 22:2) ይሖዋ ስለ ይስሐቅ ሲናገር “የምትወደውን . . . ልጅህን” ማለቱን ልብ በል። አብርሃም ይስሐቅን ምን ያህል እንደሚወደው ይሖዋ ያውቅ ነበር። አምላክ፣ እሱ ራሱም ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚሰማው ያውቃል። ይሖዋ ኢየሱስን በጣም የሚወደው ከመሆኑ የተነሳ ከሰማይ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “የምወድህ ልጄ” እና “የምወደው ልጄ” ብሏል።​—ማርቆስ 1:11፤ 9:7

ይሖዋ ለአብርሃም ጥያቄውን ያቀረበበት መንገድ “የጠየቀው ነገር ምን ያህል ከባድ መሥዋዕትነት የሚያስከፍል መሆኑን እንደተገነዘበ” የሚያሳይ እንደሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ተናግረዋል። አምላክ ያቀረበው ጥያቄ አብርሃምን በጥልቅ እንዲያዝን አድርጎት ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን፤ በተመሳሳይም ይሖዋ፣ የሚወደው ልጁ ተሠቃይቶ ሲሞት በሚመለከትበት ወቅት የተሰማው ጥልቅ ሐዘን እኛ ልናስበው ከምንችለው በላይ ነው። የልጁ ሞት ይሖዋ ከዚያ በፊት ካጋጠመውም ሆነ ከዚያ በኋላ ሊያጋጥመው ከሚችል ከማንኛውም ሁኔታ የከፋ ሐዘን እንዳስከተለበት ጥርጥር የለውም።

ይሖዋ፣ አብርሃምን የጠየቀውን ነገር ስናስበው ቢዘገንነንም አምላክ ይህ ታማኝ ሰው ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ እንዳልፈቀደ ማስታወሳችን ጥበብ ነው። አምላክ፣ ይስሐቅ እንዲሞት ባለመፍቀድ አንድ ወላጅ ሊደርስበት የሚችለው ከሁሉ የከፋ ሐዘን አብርሃም ላይ እንዳይደርስ አድርጓል። ያም ሆኖ ይሖዋ ‘ለገዛ ልጁ ሳይሳሳ ለእኛ አሳልፎ ሰጥቶታል።’ (ሮም 8:32) አምላክ እንዲህ ያለ ከባድ ሥቃይ በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይህን ያደረገው “ሕይወት ማግኘት እንድንችል” ሲል ነው። (1 ዮሐንስ 4:9) አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያረጋግጥ እንዴት ያለ ታላቅ መሥዋዕት ነው! ታዲያ ይህ እኛም በምላሹ እሱን እንድንወደው ሊያነሳሳን አይገባም? *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 አምላክ፣ ኢየሱስን ከአንዲት ሴት ቃል በቃል እንደወለደው መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ ይህን መንፈሳዊ አካል የፈጠረው ሲሆን በኋላም ከድንግል ማርያም እንዲወለድ ወደ ምድር ላከው። አምላክ፣ የኢየሱስ ፈጣሪ በመሆኑ አባቱ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።

^ አን.8 የኢየሱስ ሞት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያትና ለዚህ መሥዋዕት አድናቆታችንን ማሳየት የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ተመልከት።