አብርሃም—የእምነት ሰው
አብርሃም—የእምነት ሰው
አብርሃም ረጭ ባለው ምሽት ደጅ ላይ ቆሟል። ቀና ብሎ በከዋክብት የተሞላውን ጥርት ያለ ሰማይ ሲመለከት፣ ዘሮቹ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚበዙ አምላክ የተናገረው ትንቢት በአእምሮው ማቃጨሉ አይቀርም። (ዘፍጥረት 15:5) ከዋክብቱ፣ አብርሃም የይሖዋን ቃል እንዲያስታውስ የሚያደርጉ ምልክቶች ከመሆናቸውም ሌላ ፈጣሪ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ዋስትና ይሆኑለታል። ይሖዋ ግዙፉን አጽናፈ ዓለምና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ለመፍጠር የሚያስችል ኃይል ካለው አብርሃምና ሣራ ልጅ እንዲወልዱ ማድረግስ ያቅተዋል? አብርሃም፣ ይሖዋ ይህን ማድረግ እንደሚችል እምነት ነበረው።
እምነት ምንድን ነው? “እምነት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት አንድ ነገር የማይታይ ቢሆንም እንኳ ተጨባጭ በሆነ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በዚያ ነገር ላይ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆንን ለማመልከት ነው። በአምላክ ላይ እምነት ያለው ሰው፣ ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች የተፈጸሙ ያህል እርግጠኛ እንደሆኑ ይተማመናል።
አብርሃም እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? አብርሃም አምላክ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳለው በተግባሩ አሳይቷል። አብርሃም፣ ይሖዋ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚወስደው የገባውን ቃል እንደሚጠብቅ እርግጠኛ በመሆን በእምነት የትውልድ አገሩን ለቅቆ ሄዷል። አብርሃም፣ ዘሮቹ ከጊዜ በኋላ የከነዓንን ምድር እንደሚወርሱ እርግጠኛ በመሆን በእምነት በዚህ ምድር ኖሯል። አብርሃም፣ አምላክን በመታዘዝ ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ የሞከረውም አስፈላጊ ከሆነ ይሖዋ ይስሐቅን ከሞት እንደሚያስነሳው እምነት ስለነበረው ነው።—ዕብራውያን 11:8, 9, 17-19
አብርሃም ትኩረት ያደረገው ቀድሞ በነበረው ሁኔታ ላይ ሳይሆን ወደፊት በሚያገኘው ነገር ላይ ነበር። አብርሃምና ሣራ ከከነዓን ምድር ይልቅ በዑር ይበልጥ የተመቻቸ ሕይወት የነበራቸው ቢሆንም ‘ትተውት ስለወጡት ዕብራውያን 11:15) ከዚህ ይልቅ አምላክ፣ ለእነሱም ሆነ ለዘሮቻቸው ወደፊት በሚሰጣቸው በረከት ላይ ትኩረት አድርገው ነበር።—ዕብራውያን 11:16
ቦታ’ ሁልጊዜ አያስቡም ነበር። (ይሁንና አብርሃም በአምላክ ለማመን በቂ ምክንያት ነበረው? እንዴታ! ይሖዋ ቃል የገባውን ነገር ሁሉ ፈጽሟል። ከጊዜ በኋላ የአብርሃም ዘሮች እየበዙ የሄዱ ሲሆን እስራኤል በመባል የሚታወቅ ብሔር ሆኑ። ውሎ አድሮም እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ለአብርሃም ቃል የገባለትን ምድር ይኸውም ከነዓንን ወረሱ።—ኢያሱ 11:23
ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ከሰጣቸው ተስፋዎች አንዳንዶቹ በሰው ዓይን ሲታዩ ሊፈጸሙ የሚችሉ ባይመስሉም “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር [እንደሚቻል]” እንተማመናለን።—ማቴዎስ 19:26
አብርሃም የተወው ምሳሌ፣ ቀደም ሲል በነበረን ሁኔታ ላይ ሳይሆን ወደፊት በምናገኛቸው በረከቶች ላይ ማተኮር እንዳለብንም ያስተምረናል። ጄሰን የተባለ አንድ ሰው የአብርሃምን ምሳሌ ተከትሏል። ጄሰን የያዘው በሽታ አቅም የሚያሳጣ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ሽባ አድርጎታል። “ቀድሞ ስለነበረኝ ሁኔታ የማስብባቸው ጊዜያት እንዳሉ አልክድም” ብሏል። አክሎም “ሚስቴን አማንዳን እንደ ማቀፍ ያሉ ቀላል የሚመስሉ ነገሮችን ማድረግ አለመቻሌ ከምንም በላይ ያሳዝነኛል” በማለት ተናግሯል።
ያም ቢሆን ጄሰን፣ ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ሙሉ በሙሉ ይተማመናል፤ ይሖዋ ከገባቸው ቃሎች መካከል ምድራችን በቅርቡ ገነት እንደምትሆንና ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ፍጹም ጤንነት አግኝተው ለዘላለም እንደሚኖሩ የሰጠው ተስፋ ይገኝበታል። * (መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ኢሳይያስ 35:5, 6፤ ራእይ 21:3, 4) ጄሰን እንዲህ ብሏል፦ “ወደፊት ስለሚኖረው የተሻለ ሕይወት ሁልጊዜ ለማሰብ እሞክራለሁ። የሚሰማኝ ውጥረት፣ ጭንቀት፣ ሐዘንና የጥፋተኝነት ስሜት ሁሉ በቅርቡ ጨርሶ ይወገዳል።” በእርግጥም ጄሰን እንደ አብርሃም ያለ ግሩም የእምነት ምሳሌ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.9 ምድር ገነት ስለምትሆንበት ጊዜ ይበልጥ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3, 7 እና 8 ተመልከት።