በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእምነታቸው ምሰሏቸው

ከራሷ በላይ ለሕዝቧ የተቆረቆረች ጠቢብና ደፋር ሴት

ከራሷ በላይ ለሕዝቧ የተቆረቆረች ጠቢብና ደፋር ሴት

አስቴር በቀስታ ወደ ዙፋኑ እየቀረበች ስትሄድ ልቧ በኃይል ይመታል። በሱሳ በሚገኘው የፋርስ ቤተ መንግሥት ታላቅ ንጉሣዊ አዳራሽ ውስጥ በድንገት ጸጥታ ሲሰፍን በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ፤ አዳራሹ ረጭ ከማለቱ የተነሳ አስቴር የራሷን ኮቴና የለበሰችው የክብር ልብስ ሲጎተት የሚፈጠረውን ድምፅ መስማት ትችላለች። በዚህ ወቅት አስቴር፣ ስለ ቤተ መንግሥቱ አደባባይ ትልቅነትም ሆነ ስለ ዓምዶቹ ግርማ ሞገስ እንዲሁም ከሊባኖስ በመጣ ዝግባ ስለተሠራው ኮርኒስ ልታስብ አትችልም። ትኩረቷ ሁሉ ያረፈው በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ግለሰብ ላይ ነው፤ ምክንያቱም ሕይወቷ በእሱ እጅ ነው።

ንጉሡ፣ አስቴር ወደ እሱ እየቀረበች ስትመጣ ተመለከታት፤ ከዚያም የወርቅ ዘንጉን ዘረጋላት። ይህ ቀላል የሚመስል ድርጊት የአስቴርን ሕይወት አትርፎላታል፤ ንጉሡ ዘንጉን በመዘርጋቱ፣ አስቴር ሳትጠራ ወደ እሱ በመምጣት ለፈጸመችው ጥፋት ይቅርታ እንዳደረገላት አሳይቷል። አስቴርም ዙፋኑ አጠገብ ስትደርስ እጇን ዘርግታ የንጉሡን ዘንግ ጫፍ በመንካት አመስጋኝነቷን ገለጸች።​—አስቴር 5:1, 2 *

ንጉሥ ጠረክሲስ እጅግ ባለጸጋ እንደሆነና ታላቅ ኃይል እንዳለው በግልጽ ማየት ይቻላል። በዚያ ዘመን የፋርስ ነገሥታት የሚለብሱት ንጉሣዊ ልብስ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሚያወጣ ምሁራን ይናገራሉ። ጠረክሲስ ይህን ያህል ኃያል ቢሆንም ሚስቱን ይወዳት ነበር፤ አስቴርም ባሏ ለእሷ ያለውን ፍቅር ከዓይኑ ማንበብ ችላለች። ንጉሡ እንዲህ አላት፦ “ንግሥት አስቴር ሆይ፤ ለምን መጣሽ? ከእኔ የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይሰጥሻል።”​—አስቴር 5:3

አስቴር ሕዝቧን ከምድር ገጽ ለመደምሰስ ከተጠነሰሰው ሴራ ለመታደግ ስትል ወደ ንጉሡ መምጣቷ በራሱ አስደናቂ እምነትና ድፍረት እንዳላት የሚያሳይ ነው። እስካሁን ያሰበችው የተሳካላት ቢሆንም ይበልጥ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን መወጣት ይጠበቅባታል። ኩሩ የሆነውን ጠረክሲስን፣ በጣም የሚያምነው አማካሪው ክፉ ሰው እንደሆነ ማሳመን ይኖርባታል፤ ከዚህም በተጨማሪ ሐማ ንጉሡን በማታለል በአስቴር ሕዝብ ላይ ሞት እንዲፈርድ እንዳደረገ ለንጉሡ ማስረዳት አለባት። ታዲያ አስቴር፣ ንጉሡን እንዴት አድርጋ ታሳምነው ይሆን? እኛስ ከእሷ እምነት ምን ልንማር እንችላለን?

‘የምትናገርበትን ጊዜ’ በጥበብ መረጠች

አስቴር፣ በንጉሡ ሹማምንት ፊት ጉዳይዋን ግልጥልጥ አድርጋ ለንጉሡ ብትነግረው ይሻል ይሆን? እንዲህ ማድረግ ንጉሡን የሚያዋርድ ከመሆኑም ሌላ ሐማ ስለ ጉዳዩ ለመከራከር አጋጣሚ ያገኝ ነበር። ታዲያ አስቴር ምን አደረገች? ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፎ ነበር። (መክብብ 3:1, 7) የአስቴር አሳዳጊ አባት የሆነው ታማኙ መርዶክዮስ ከትንሽነቷ ጀምሮ እየተንከባከበ በሚያሳድጋት ጊዜ እንዲህ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት አስተምሯት እንደሚሆን ልንገምት እንችላለን። አስቴር “ለመናገር” አመቺ የሆነውን ጊዜ በጥንቃቄ የመምረጥን አስፈላጊነት እንደተገነዘበች ጥርጥር የለውም።

አስቴር “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆን፣ ባዘጋጀሁለት ግብዣ ላይ ንጉሡ ዛሬ ከሐማ ጋር ይገኝልኝ” አለች። (አስቴር 5:4) ንጉሡ ግብዣውን የተቀበለ ሲሆን ሐማንም አስጠራው። የአስቴር አነጋገር ጥበብ የተሞላበት እንደነበር አስተዋልክ? የባሏን ክብር የሚነካ ነገር ሳታደርግ ያሳሰባትን ነገር ለመናገር የሚያስችል ሁኔታ አመቻቸች።

አስቴር ግብዣውን በጥንቃቄ እንዳዘጋጀችና ሁሉም ነገር ልክ ባሏ በሚፈልገው መንገድ መሠራቱን እንደተከታተለች ጥርጥር የለውም። ግብዣው ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን ምርጥ የወይን ጠጅ ቀርቦ ነበር። (መዝሙር 104:15) ጠረክሲስ በግብዣው ስለተደሰተ አስቴር የምትፈልገውን ነገር እንድትነግረው በድጋሚ ጠየቃት። አስቴር ጉዳዩን አሁን ብትነግረው ይሻል ይሆን?

አስቴር እንዲህ አልተሰማትም። እንዲያውም ንጉሡንና ሐማን በቀጣዩ ቀን በምታዘጋጅላቸው ሌላ ግብዣ ላይ እንዲገኙ ጠራቻቸው። (አስቴር 5:7, 8) አስቴር ጉዳይዋን በዚያ ወቅት ከመናገር ወደኋላ ያለችው ለምንድን ነው? የአስቴር ሕዝብ በሙሉ ከምድር ገጽ እንዲጠፉ የሚያዝዝ ንጉሣዊ አዋጅ እንደወጣ አስታውስ። ከጉዳዩ ክብደት አንጻር አስቴር የምትናገርበትን ጊዜ በጥንቃቄ መምረጥ ነበረባት። በመሆኑም ባሏን ምን ያህል እንደምታከብረው የምታሳይበት ሌላ አጋጣሚ ለመፍጠር ስትል የምትናገርበትን ጊዜ አዘገየችው።

ትዕግሥት ብዙውን ጊዜ የማይታይ ውድ ባሕርይ ነው። አስቴር ከመጨነቋም ሌላ በልቧ ያለውን ለመናገር በጣም ብትፈልግም ለመናገር ትክክለኛ የሆነውን ጊዜ በትዕግሥት ጠብቃለች። እኛም አስቴር ከተወችው ምሳሌ ብዙ መማር እንችላለን፤ ሁላችንም ሊስተካከሉ የሚገቡ ስህተቶችን ማየታችን አይቀርም። ሥልጣን ያለው ሰው አንድን ችግር እንዲያስተካክለው ለመጠየቅ ከፈለግን የአስቴርን ምሳሌ በመኮረጅ ትዕግሥተኞች መሆን ሊያስፈልገን ይችላል። ምሳሌ 25:15 “በትዕግሥት ገዥን ማግባባት ይቻላል፤ ለስላሳ አንደበትም ዐጥንት ይሰብራል” ይላል። አስቴር እንዳደረገችው በትዕግሥት ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቀን በለሰለሰ አንደበት የምንናገር ከሆነ እንደ ዐጥንት ጠንካራ የሆነ ተቃውሞን እንኳ መስበር እንችላለን። ታዲያ አስቴር ትዕግሥተኛና ጠቢብ በመሆኗ አምላኳ ይሖዋ ባርኳታል?

ትዕግሥት ለፍትሕ መንገድ ጠረገ

የአስቴር ትዕግሥት እንደ ሰንሰለት እርስ በርስ ለተያያዙ አስገራሚ ክስተቶች መንገድ ጠረገ። ሐማ ከመጀመሪያው ግብዣ በኋላ የንጉሡንና የንግሥቲቱን ሞገስ እንዳገኘ ስለተሰማው ወደ ቤቱ ሲመለስ “ደስ ብሎትና መንፈሱ ረክቶ” ነበር። ይሁንና ሐማ በቤተ መንግሥቱ በር በኩል ሲያልፍ ዓይኑ መርዶክዮስ ላይ አረፈ፤ ይህ አይሁዳዊ አሁንም ቢሆን ለእሱ ልዩ አክብሮት ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም። መርዶክዮስ ለሐማ የማይሰግደው ስለናቀው ሳይሆን ይህን ለማድረግ ሕሊናው ስላልፈቀደለትና ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት ነው። ሆኖም ሐማ፣ መርዶክዮስ እንዳልሰገደለት ሲመለከት “ቁጣው . . . ነደደ።”​—አስቴር 5:9

ሐማ ለሚስቱና ለወዳጆቹ መርዶክዮስ ሊሰግድለት ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲነግራቸው ቁመቱ ከ22 ሜትር በላይ የሚሆን ትልቅ ግንድ እንዲያስተክልና መርዶክዮስን ለመስቀል ከንጉሡ ፈቃድ እንዲጠይቅ መከሩት። ሐማ የሰጡትን ምክር ስለወደደው ወዲያውኑ ያሉትን ለማድረግ ቆርጦ ተነሳ።​—አስቴር 5:12-14

በሌላ በኩል ደግሞ “በዚያች ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ መተኛት አልቻለም።” በመሆኑም የዘመኑ የታሪክ መዛግብት እንዲነበቡለት አዘዘ። መዛግብቱ ሲነበቡ በጠረክሲስ ላይ ስለተጠነሰሰው የግድያ ሴራ የሚናገር ዘገባ ሰፍሮ ተገኘ። ንጉሡም ጉዳዩን አስታወሰው፤ ሊገድሉት ያሴሩት ሰዎች ተይዘው በሞት ተቀጥተው ነበር። ይሁንና ሴራውን ያጋለጠው መርዶክዮስስ ምን ተደረገለት? ንጉሡ፣ መርዶክዮስ ምን ሽልማት እንደተሰጠው ጠየቀ። መልሱ “ምንም አልተደረገለትም” የሚል ነበር።​—አስቴር 6:1-3

ንጉሡም በሁኔታው ያዘነ ሲሆን የተፈጠረውን ስህተት ለማስተካከል ሊረዳው የሚችል የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን በአቅራቢያው መኖሩን ጠየቀ። የሚገርመው ነገር፣ በንጉሡ ቤተ መንግሥት አደባባይ የተገኘው ሐማ ነበር፤ ሐማ ማልዶ የመጣው መርዶክዮስን ለማሰቀል ከንጉሡ ፈቃድ ለማግኘት ቸኩሎ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ ሐማ ፈቃድ ከመጠየቁ በፊት ጠረክሲስ፣ ‘ንጉሡ ሊያከብረው ለሚፈልገው ሰው ምን ቢደረግለት ይሻላል?’ ብሎ ጠየቀው። ሐማም ንጉሡ ሊያከብረው የሚፈልገው እሱን ራሱን እንደሆነ ገመተ። በመሆኑም ሐማ፣ ለግለሰቡ ታላቅ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ተናገረ፤ ንጉሡ ሊያከብረው የሚፈልገው ሰው የንጉሡን ልብሰ መንግሥት እንዲለብስና አንድ ትልቅ ባለሥልጣን በንጉሡ ፈረስ ላይ አስቀምጦት በሱሳ ከተማ እንዲያዘዋውረው እንዲሁም ሁሉ ሰው እየሰማ ጮክ ብሎ እንዲያወድሰው ሐሳብ አቀረበ። ሐማ እንዲህ ያለው ክብር ሊሰጠው የታሰበው ሰው መርዶክዮስ መሆኑን ሲያውቅ ፊቱ ምን ያህል እንደተለዋወጠ መገመት ትችላለህ! ይባስ ብሎ ደግሞ ንጉሡ የመርዶክዮስን ክብር እንዲያውጅ የመደበው ሐማን ነበር!​—አስቴር 6:4-10

ሐማ የተሰጠው ሥራ መርዶክዮስን ይበልጥ እንዲጠላው ሳያደርገው አልቀረም፤ ሳይወድ በግዱ የታዘዘውን ከፈጸመ በኋላ አንጀቱ እርር ብሎ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ሚስቱና ወዳጆቹ፣ ሁኔታዎች በዚህ መልኩ መገለባበጣቸው መጨረሻው እንደማያምር የሚጠቁም መሆኑን እንዲሁም መርዶክዮስ ከተባለው ከዚህ አይሁዳዊ ጋር በገጠመው ትግል መሸነፉ እንደማይቀር ነገሩት።​—አስቴር 6:12, 13

አስቴር ትዕግሥተኛ በመሆን ልመናዋን ለንጉሡ ለማቅረብ አንድ ተጨማሪ ቀን መቆየቷ ሐማ ለራሱ ውድቀት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች አጋጣሚ ፈጠረ። በሌላ በኩል ደግሞ በዚያ ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ እንዲያጣ ያደረገው ይሖዋ አምላክ ይሆን? (ምሳሌ 21:1) የአምላክ ቃል በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ እንድናሳይ የሚያበረታታን መሆኑ ምንም አያስገርምም። (ሚክያስ 7:7) አምላክን በትዕግሥት የምንጠብቅ ከሆነ እሱ ለችግሮቻችን የሚሰጠው መፍትሔ በራሳችን ከምንፈጥረው መላ እጅግ የላቀ መሆኑን እንመለከታለን።

በድፍረት ተናገረች

አስቴር ከዚህ ወዲያ የንጉሡን ትዕግሥት ለመፈታተን አልደፈረችም፤ በሁለተኛው ግብዣ ላይ ሁሉንም ነገር መናገሯ ግድ ነበር። ግን እንዴት አድርጋ ትንገረው? ንጉሡ ራሱ “የምትለምኚው ምንድን ነው?” በማለት እንድትናገር አጋጣሚውን ሰጣት። (አስቴር 7:2) ጉዳይዋን “ለመናገር” ትክክለኛው “ጊዜ” አሁን ነው።

አስቴር ከመናገሯ በፊት በልቧ ወደ አምላኳ ጸልያ ሊሆን ይችላል፤ ከዚያም “ንጉሥ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼና ግርማዊነትህን ደስ የሚያሰኝ ከሆነ፣ ሕይወቴን ታደጋት፤ ልመናዬ ይህ ነው፤ ሕዝቤን አትርፍ፤ ጥያቄዬም ይኸው ነው” አለች። (አስቴር 7:3) አስቴር፣ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘውን ነገር በተመለከተ ውሳኔውን እንደምታከብር መግለጿን ልብ በል። አስቴር፣ ንጉሡን ሆን ብላ ካዋረደችው ከቀድሞ ሚስቱ ከአስጢን ምንኛ የተለየች ነበረች! (አስቴር 1:10-12) ከዚህም በላይ አስቴር፣ ንጉሡ በሐማ ላይ እምነት በመጣሉ እንደተሞኘ በመናገር አልነቀፈችውም። ከዚህ ይልቅ በሕይወቷ ላይ ከተጋረጠው አደጋ እንዲጠብቃት ንጉሡን ለመነችው።

ይህ ልመና የንጉሡን ስሜት በጥልቅ እንደነካውና እንዳስገረመው ጥርጥር የለውም። ለመሆኑ የንግሥቲቱን ሕይወት አደጋ ላይ ለመጣል የደፈረው ማን ነው? አስቴር በመቀጠል እንዲህ አለች፦ “እኔና ሕዝቤ ለጥፋት፣ ለመገደልና ለመደምሰስ ተሸጠናል። የተሸጥነው ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች እንድንሆን ብቻ ቢሆን ኖሮ ዝም ባልኩ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጥፋት በንጉሡም ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል በቸልታ መታለፍ የለበትም።” (አስቴር 7:4 NW) አስቴር የገጠማትን ችግር በግልጽ እንደተናገረች ልብ በል፤ ሆኖም ችግሩ ለባርነት የመዳረግ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ በዝምታ ታልፈው እንደነበረ አክላ ገልጻለች። ይህ የዘር ማጥፋት ሴራ ግን በንጉሡ ላይ ከባድ ኪሣራ ስለሚያስከትል በዝምታ ሊታለፍ አይገባም።

አስቴር የተወችው ምሳሌ የማሳመን ችሎታን በተመለከተ ብዙ ነገር ያስተምረናል። ለአንድ የምትወደው ሰው ሌላው ቀርቶ ለአንድ ባለሥልጣን አሳሳቢ ስለሆነ ጉዳይ መናገር ቢያስፈልግህ ትዕግሥትን፣ አክብሮትንና ግልጽነትን አንድ ላይ አዋሕደህ ሐሳብህን መግለጽህ በእጅጉ ሊጠቅምህ ይችላል።​—ምሳሌ 16:21, 23

ጠረክሲስ “ለመሆኑ እርሱ ማን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ እስከዚህ የደፈረውስ ሰው የታለ?” ሲል ጠየቀ። አስቴርም ጣቷን በሐማ ላይ ቀስራ “ያ ባላጋራና ጠላት ይህ ክፉው ሐማ ነው” አለች። አስቴር የሰነዘረችው ከባድ ክስ ምን ዓይነት ስሜት ፈጥሮ ይሆን? ሐማ በድንጋጤ ክው ብሎ ቀረ። ደሙ ቶሎ የሚፈላው ንጉሥ ጠረክሲስ ደግሞ የሚያምነው አማካሪው እንዳታለለውና ውድ ሚስቱን ለሞት በሚዳርግ አዋጅ ላይ እንዲፈርም እንዳደረገው በተገነዘበ ጊዜ ፊቱ በንዴት ሲቀላ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ! ንጉሡ ቁጣው እንዲበርድለት ወደ አትክልቱ ስፍራ ሄደ።​—አስቴር 7:5-7

ሐማ ያልታወቀበት መሠሪ ጠላት መሆኑ ሲጋለጥ በንግሥቲቱ እግር ላይ ተደፋ። ንጉሡ ተመልሶ ሲመጣ ሐማ፣ አስቴር እንድትምረው በድንክ አልጋዋ ላይ ተደፍቶ ሲማጸን አገኘው፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተናድዶ “ይባስ ብሎ አብራኝ ያለችውን ንግሥት በገዛ ቤቴ ሊደፍራት ያስባልን?” አለው። ይህ ውንጀላ በሐማ ላይ ሞት እንደተበየነበት የሚያሳይ ነበር። ሐማ ፊቱ ተሸፍኖ እንዲወሰድ ተደረገ። በዚህ ጊዜ ከንጉሡ ጃንደረቦች አንዱ፣ ሐማ መርዶክዮስን ሊሰቅልበት ብሎ ስለተከለው ትልቅ ግንድ ለንጉሡ ነገረው። ጠረክሲስም ሐማ ራሱ በዚያ ግንድ ላይ እንዲሰቀል ወዲያውኑ አዘዘ።​—አስቴር 7:8-10

ፍትሕ በጠፋበት በዛሬው ጊዜ ፍትሐዊ እርምጃ ይወሰዳል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። አንተ እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃል? አስቴር ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጠችም፣ ተጠራጣሪ አልሆነችም ወይም ደግሞ ጨርሶ እምነት አላጣችም። ጊዜውን ጠብቃ ትክክል ስለሆነው ነገር በድፍረት የተናገረች ሲሆን ይሖዋ እንደሚረዳት በመተማመን የቀረውን ለእሱ ትታዋለች። እኛም እንዲሁ እናድርግ! ይሖዋ ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። በመሆኑም ልክ በሐማ ላይ እንዳደረገው አሁንም ቢሆን ክፉና አታላይ የሆኑ ሰዎች በራሳቸው ወጥመድ እንዲወድቁ ማድረግ ይችላል።​—መዝሙር 7:11-16

ለይሖዋና ለሕዝቡ በመቆርቆር እርምጃ ወስዳለች

በመጨረሻም ንጉሡ፣ መርዶክዮስ ማን እንደሆነ አወቀ፤ ከተጠነሰሰበት የግድያ ሴራ ያዳነው ታማኝ ሰው ብቻ ሳይሆን የአስቴር አሳዳጊ አባትም ጭምር መሆኑን ተገነዘበ። ጠረክሲስ ሐማ የነበረውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ለመርዶክዮስ ሰጠው። ንጉሡ የሐማን ቤትና የነበረውን ከፍተኛ ሀብት ለአስቴር ሰጣት፤ እሷ ደግሞ መርዶክዮስን በሐማ ንብረት ላይ ሾመችው።​—አስቴር 8:1, 2

አስቴርና መርዶክዮስ ከሞት ስለተረፉ ንግሥቲቱ እፎይ ማለት ትችል ይሆን? ይህ ሊሆን የሚችለው ራስ ወዳድ ከሆነች ብቻ ነው። ሐማ አይሁዳውያንን በሙሉ ለመፍጀት ያወጣው አዋጅ በዚህ ወቅት በግዛቱ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር እየተዳረሰ ነበር። ሐማ ይህን አረመኔያዊ ጥቃት ለመፈጸም አመቺ የሚሆነውን ጊዜ ለይቶ ለማወቅ ፉር የሚባል ዕጣ ጥሎ ነበር፤ ይህ ዕጣ ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም። (አስቴር 9:24-26) አይሁዳውያንን ለማጥፋት የታሰበው ቀን ሊደርስ ብዙ ወራት የሚቀሩ ቢሆንም ቀኑ በፍጥነት እየቀረበ ነበር። እልቂቱ እንዳይደርስ ማድረግ ይቻል ይሆን?

አስቴር ለሁለተኛ ጊዜ ሕይወቷን ለአደጋ በማጋለጥ ንጉሡ ሳይጠራት እንደገና በፊቱ ቀረበች፤ እንዲህ በማድረጓ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ መንፈስ አሳይታለች። በዚህ ጊዜ አስቴር ንጉሡ እግር ላይ ወድቃ ስለ ሕዝቧ በማልቀስ የወጣውን አሰቃቂ አዋጅ እንዲሽር ባሏን ለመነችው። ይሁን እንጂ በፋርስ ነገሥታት ስም የተላለፈ ሕግ ሊሻር አይችልም። (ዳንኤል 6:12, 15) ስለዚህ ንጉሡ አዲስ ሕግ እንዲያጸድቁ ለአስቴርና ለመርዶክዮስ ሥልጣን ሰጣቸው። በመሆኑም አይሁዳውያን ራሳቸውን እንዲከላከሉ መብት የሚሰጣቸው ሁለተኛ አዋጅ ወጣ። ከዚያም ፈረሰኞች በግዛቱ ውስጥ ወዳሉት ስፍራዎች ሁሉ በፍጥነት በመሄድ ለአይሁዳውያን ምሥራቹን አዳረሱ። ብዙዎች የመኖር ተስፋቸው እንደገና ለመለመ። (አስቴር 8:3-16) በዚያ ሰፊ ግዛት በሙሉ የሚኖሩ አይሁዳውያን ራሳቸውን ሲያስታጥቁና ለውጊያ ሲዘጋጁ በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንችላለን፤ አዲሱ አዋጅ ባይወጣ ኖሮ ይህ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነበር። ይሁንና አንድ ትልቅ ጥያቄ ይነሳል፦ ‘የሰራዊት አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ከሕዝቡ ጎን ይቆም ይሆን?​—1 ሳሙኤል 17:45

አይሁዳውያንን ለማጥፋት የተመረጠው ቀን ሲደርስ የአምላክ ሕዝቦች ተዘጋጅተው ነበር። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆነው ስለ አይሁዳዊው መርዶክዮስ የሚገልጸው ዜና በሁሉም ቦታ ስለተዳረሰ ብዙ የፋርስ ባለሥልጣናትም እንኳ ከአይሁዳውያን ጎን ተሰለፉ። ይሖዋ ለሕዝቡ ታላቅ ድል ሰጣቸው። ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ የበቀል እርምጃ እንዳይወሰድ ሲል ጠላቶቻቸው ዳግመኛ በማያንሰራሩበት ሁኔታ እንዲሸነፉ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። *​—አስቴር 9:1-6

ከዚህም በላይ የዚያ ክፉ ሰው ማለትም የሐማ አሥር ልጆች በሕይወት እያሉ መርዶክዮስ የሐማን ቤት ልቆጣጠር ቢል ለሕይወቱ የሚያሰጋ ይሆናል። ስለዚህ እነሱም ተገደሉ። (አስቴር 9:7-10) አምላክ ቀደም ብሎ የሕዝቦቹ ጠላቶች የሆኑት ክፉዎቹ አማሌቃውያን ከምድር ገጽ እንደሚጠፉ ትንቢት ተናግሮ ስለነበር የሐማ ቤተሰብ ሲደመሰስ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተፈጸመ። (ዘዳግም 25:17-19) ጥፋት ከተፈረደበት የአማሌቅ ብሔር ውስጥ በሕይወት የነበሩት የሐማ ልጆች ሳይሆኑ አይቀሩም።

አስቴር ገና በወጣትነቷ በጣም ከባድ ኃላፊነት መሸከም ግድ ሆኖባት ነበር፤ ይህች ወጣት ጦርነትንና የሞት ፍርድ ማስፈጸምን የሚመለከቱ ንጉሣዊ አዋጆችን ከማውጣት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ማከናወን ነበረባት። ይህ ቀላል እንደማይሆንላት ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ የእስራኤል ብሔር እንዲጠፋ አልፈቀደም፤ ምክንያቱም ለሰው ዘር በሙሉ ብቸኛ የተስፋ ምንጭ የሆነው መሲሕ የሚመጣው ከዚህ ብሔር ነበር። (ዘፍጥረት 22:18) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች፣ መሲሑ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላ ተከታዮቹ በጦርነት እንዳይካፈሉ መከልከሉ ያስደስታቸዋል።​—ማቴዎስ 26:52

ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ጦርነት ይካፈላሉ፤ ሰይጣን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለማጥፋት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጦ ተነስቷል። (2 ቆሮንቶስ 10:3, 4) አስቴርን የመሰለች ምሳሌ ያለን መሆኑ ምንኛ በረከት ነው! እኛም እንደ እሷ ሌሎችን ለማሳመን ጥበብና ትዕግሥትን በአንድነት በመጠቀም እንዲሁም ደፋሮች በመሆንና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ከአምላክ ሕዝቦች ጎን በፈቃደኝነት በመቆም እምነት እንዳለን እናሳይ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በዚህ ዓምድ ሥር ከዚህ ቀደም በወጣው ርዕስ ላይ ወላጆቿ የሞቱባትን አስቴርን መርዶክዮስ የሚባል በዕድሜ የሚበልጣት የአጎቷ ልጅ እንዳሳደጋትና ከጊዜ በኋላም የፋርሱ ንጉሥ የጠረክሲስ ሚስት ለመሆን እንደተመረጠች አይተን ነበር። የንጉሡ አማካሪ የነበረው ሐማ የመርዶክዮስ ሕዝብ የሆኑትን አይሁዳውያንን ለመደምሰስ አንድ ክፉ ሴራ ጠንስሶ ነበር። በመሆኑም አስቴር ወደ ንጉሡ ቀርባ ሕዝቧ እንዳይጠፋ ልመና እንድታቀርብ መርዶክዮስ ጠይቋታል።​—በጥቅምት 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በእምነታቸው ምሰሏቸው​—ለአምላክ ሕዝብ ጥብቅና ቆማለች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.32 ንጉሡ፣ አይሁድ በጠላቶቻቸው ላይ የተቀዳጁትን ድል እንዲያጠናቅቁ ተጨማሪ ቀን ፈቀደላቸው። (አስቴር 9:12-14) አይሁዳውያን ይህን ድል ለማሰብ እስከ ዛሬም ድረስ በጸደይ ወቅት ፉሪም ተብሎ የሚጠራ በዓል ያከብራሉ፤ የበዓሉ ስያሜ የመጣው ሐማ እስራኤላውያንን ለመደምሰስ ከጣለው ፉር ከተባለው ዕጣ ነው።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ አስቴር የሚነሱ ጥያቄዎች

አስቴር የይሖዋ አምላኪ ያልሆነ አረማዊ ሰው እንድታገባ መርዶክዮስ የፈቀደው ለምን ነበር?

አንዳንድ ምሁራን፣ መርዶክዮስ ባገኘው አጋጣሚ ለመጠቀም የሚሻ ሰው እንደነበርና አስቴርን ለንጉሡ የዳራት ክብር ለማግኘት አስቦ እንደሆነ ቢናገሩም ይህን ለማመን የሚያበቃ መሠረት የለም። መርዶክዮስ ታማኝ አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ዓይነቱን ጋብቻ እንደማይደግፈው ግልጽ ነው። (ዘዳግም 7:3) የጥንት አይሁዳውያን አፈ ታሪክ፣ መርዶክዮስ ይህን ጋብቻ ለማስቀረት ጥረት አድርጎ እንደነበረ ይገልጻል። ይሁንና እንደ አምላክ የሚከበር አምባገነን መሪ በሚያስተዳድረው አገር ውስጥ በስደት የሚኖሩት መርዶክዮስም ሆነ አስቴር በጉዳዩ ላይ ተሰሚነት ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ከጊዜ በኋላ እንደታየው ይሖዋ በአስቴር ጋብቻ በመጠቀም ሕዝቡን ከጥፋት አድኗል።​—አስቴር 4:14

የአስቴር መጽሐፍ ይሖዋ የሚለውን የአምላክን የግል ስም የማይጠቅሰው ለምንድን ነው?

ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት የአስቴርን መጽሐፍ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጻፈው መርዶክዮስ ነው። መጽሐፉ ወደ ኢየሩሳሌም ከመወሰዱ በፊት ከፋርስ ንጉሣዊ መዛግብት ጋር እንዲቀመጥ ተደርጎ ሊሆን ይችላል። የፋርስን አማልክት የሚያመልኩ ሰዎች በመጽሐፉ ውስጥ ይሖዋ የሚለውን ስም ቢያገኙ መጽሐፉን ሊያጠፉት ይችሉ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በታሪኩ ውስጥ ይሖዋ የተጫወተውን ሚና በግልጽ ማየት ይቻላል። የሚገርመው ነገር፣ በመጀመሪያ በተጻፈው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ውስጥ የአምላክ ስም በአራት ቦታዎች ላይ ሁሉም ሰው ሊያየው በማይችል መንገድ ሰፍሮ ይገኛል፤ በተከታታይ የተጻፉ የተወሰኑ ቃላት የመጀመሪያ ወይም የመጨረሻ ፊደላት አንድ ላይ ተገጣጥመው ሲነበቡ የአምላክን የግል ስም እንዲያስገኙ ተደርገው የተጻፉ ይመስላል።

የአስቴር መጽሐፍ ከታሪክ አንጻር ትክክለኛ ነው?

ተቺዎች መጽሐፉ ከታሪክ አንጻር ትክክለኛ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ምሁራን እንደገለጹት የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ስለ ፋርስ ንጉሣዊ ቤተሰብ ሕይወት፣ ስለ ሕንፃ አሠራር ዘዴያቸውና ባሕላቸው ዝርዝር እውቀት እንዳለው ማየት ይቻላል። እውነት ነው፣ እስከ ዛሬ በቆዩ የፋርስ ሰነዶች ውስጥ የንግሥት አስቴር ስም ተጠቅሶ አይገኝም፤ ይሁንና በመዛግብቱ ላይ ስሟ ያልተጠቀሰው የንጉሣዊው ቤተሰብ አባል አስቴር ብቻ እንዳልሆነች ይታወቃል። ከዚህም በላይ ማርዱካ (መርዶክዮስ የሚለው ስም በፋርስ ቋንቋ ሲጠራ) የተባለ ሰው በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሰው ዘመን ላይ በሱሳ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን ሆኖ እንዳገለገለ ዓለማዊ የታሪክ መዛግብት ይገልጻሉ።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንድ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ

አስቴርና መርዶክዮስ ለአምላክ ሕዝብ በሚዋጉበት ጊዜ አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርገዋል። በብዙ መቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ይሖዋ፣ ያዕቆብን ከልጆቹ ስለ አንዱ የሚከተለውን ትንቢት እንዲናገር በመንፈሱ መርቶት ነበር፦ “ብንያም፣ ነጣቂ ተኵላ ነው፤ ያደነውን ማለዳ ይበላል፤ የማረከውን ማታ ይከፋፈላል።” (ዘፍጥረት 49:27) በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጀመሪያ ወይም በሌላ አባባል “ማለዳ” ላይ ከነበሩት የብንያም ዝርያዎች መካከል ንጉሥ ሳኦልና ለይሖዋ ሕዝቦች የተዋጉ ሌሎች ኃያላን ጦረኞች ይገኙበታል። በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ላይ ጀምበር ከጠለቀች በኋላ ወይም በሌላ አባባል “ማታ” ላይ የብንያም ነገድ አባላት የሆኑት አስቴርና መርዶክዮስ የይሖዋን ጠላቶች ተዋግተው ድል አድርገዋል። ብዛት ያለውን የሐማን ንብረት ስለወረሱም ‘የማረኩትን ተከፋፍለዋል’ ሊባል ይችላል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስቴር ንጉሡ ላሳያት ምሕረት አመስጋኝነቷን በትሕትና ገልጻለች

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስቴር የሐማን ክፋት በድፍረት አጋልጣለች

[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስቴርና መርዶክዮስ በፋርስ ግዛት ለሚገኙ አይሁዳውያን አዋጆችን ልከዋል