ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
በጉርምስና ዕድሜ የሚገኝ ልጃችሁ እምነታችሁን ቢጠራጠር
ብዙ ወጣቶች እያደጉ ሲሄዱ የወላጆቻቸውን ሃይማኖት ለመከተል ይወስናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:14) አንዳንዶች ግን የተለየ አቋም ይኖራቸዋል። ልጃችሁ እያደገ ሲሄድ፣ ስለ እምነታችሁ ያስተማራችሁትን ነገር መጠራጠር ቢጀምር ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ይህ ርዕስ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ዓይነቱን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዴት መወጣት እንደሚችሉ ያብራራል።
“ከአሁን በኋላ የወላጆቼን ሃይማኖት መከተል አልፈልግም።”—ኮራ፣ 18 *
እናንተ የምትከተሉት ሃይማኖት ስለ አምላክ እውነቱን እንደሚያስተምር እርግጠኞች ናችሁ። መጽሐፍ ቅዱስን መከተል ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ለመምራት እንደሚያስችለንም ታምናላችሁ። በመሆኑም የምታምኑባቸውን ነገሮች በልጃችሁ ልብ ውስጥ ለመቅረጽ መፈለጋችሁ የሚጠበቅ ነገር ነው። (ዘዳግም 6:6, 7) ይሁን እንጂ ልጃችሁ እያደገ ሲሄድ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለው ፍላጎት ቢጠፋስ? * በልጅነቱ ደስ እያለው ይቀበል የነበረውን ትምህርት አሁን መጠራጠር ቢጀምርስ?—ገላትያ 5:7
እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠማችሁ ከአንድ ክርስቲያን ወላጅ የሚጠበቀውን ኃላፊነት መወጣት እንዳልቻላችሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ቀጥሎ እንደምናየው ልጃችሁ የእናንተን እምነት እንዲጠራጠር ያደረጉት ሌሎች ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ልታውቁት የሚገባ ነገር አለ፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ጥርጣሬውን ሲገልጽ ምላሽ የምትሰጡበት መንገድ እምነታችሁን እንዲቀበል ወይም እርግፍ አድርጎ እንዲተወው ሊያደርገው ይችላል። ልጃችሁ እምነታችሁን እንደማይቀበል ሲነግራችሁ ቡራከረዩ ካላችሁ የማታሸንፉበት ከባድ ጦርነት ውስጥ የገባችሁ ያህል ነው።—ቆላስይስ 3:21
የተሻለው ነገር ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ምክር መከተል ነው። “የጌታ ባሪያ . . . ሊጣላ አይገባውም፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቁ የሆነና ክፉ ነገር ሲደርስበት በትዕግሥት የሚያሳልፍ ሊሆን ይገባዋል” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24) ታዲያ በጉርምስና ዕድሜ የሚገኝ ልጃችሁ እምነታችሁን ቢጠራጠር “ለማስተማር ብቁ” እንደሆናችሁ ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው?
አስተዋዮች ሁኑ
በመጀመሪያ፣ ልጃችሁ እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲይዝ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ለማስተዋል ሞክሩ። ለምሳሌ ያህል፦
-
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጓደኛ እንደሌለውና ብቸኛ እንደሆነ ይሰማዋል? “ጓደኞች ለማግኘት ስለምፈልግ አብረውኝ ከሚማሩ ብዙ ልጆች ጋር እቀራረብ ነበር፤ ይህ ደግሞ ለዓመታት መንፈሳዊ እድገት እንዳላደርግ እንቅፋት ሆነብኝ። ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለኝ ፍላጎት እንዲጠፋ ያደረገው ዋናው
ነገር መጥፎ ጓደኝነት ነው፤ አሁን ሳስበው ብዙ የሚቆጨኝ ነገር አለ።”—ለኖር፣ 19 -
በራስ የመተማመን ስሜት ስለሚጎድለው ስለ እምነቱ ከመናገር ወደኋላ ይል ይሆን? “ተማሪ እያለሁ ስለማምንበት ነገር ለክፍሌ ልጆች መናገር ያስፈራኝ ነበር። ከሰው የማልገጥም ወይም አክራሪ እንደሆንኩ አድርገው እንዳያዩኝ እፈራ ነበር። ከሌሎች የተለዩ ሆነው የሚታዩ ልጆች ሁሉ ይገለሉ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይህ እንዲደርስብኝ አልፈለግሁም።”—ራሞን፣ 23
-
በክርስቲያናዊ መሥፈርቶች መመራት ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ተሰምቶት ይሆን? “መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለማግኘት ረጅም ደረጃ መውጣት እንዳለብኝ ይሰማኛል፤ እኔ ግን ገና ደረጃውን መውጣት እንኳ እንዳልጀመርኩ እንዲያውም በጣም ሩቅ እንደሆንኩ አድርጌ አስባለሁ። ደረጃውን ለመውጣት በጣም ከመፍራቴ የተነሳ እምነቴን ለመተው ያሰብኩበት ጊዜ ነበር።”—ረኔ፣ 16
ስሜቱን ለማወቅ አነጋግሩት
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ የሚያሳስበው ነገር ምንድን ነው? ይህን ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ እሱኑ መጠየቅ ነው! ይሁንና ውይይታችሁ ወደ ጭቅጭቅ እንዳይቀየር ጥንቃቄ አድርጉ። ከዚህ ይልቅ በያዕቆብ 1:19 ላይ የሚገኘውን “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት” የሚለውን ምክር ተከተሉ። ልጃችሁ የሚናገረውን በትዕግሥት አዳምጡ። የቤተሰባችሁ አባል ያልሆነን ሰው ስታነጋግሩ እንደምታደርጉት ሁሉ ‘ታጋሽ’ ለመሆንና “በማስተማር ጥበብ” ለመጠቀም ጥረት አድርጉ።—2 ጢሞቴዎስ 4:2
ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ እንደማይፈልግ ቢነግራችሁ እንዲህ እንዲል ያደረገው ሌላ የሚያሳስበው ነገር እንዳለ ለማወቅ ሞክሩ። ይሁንና ይህን ስታደርጉ ታጋሾች ሁኑ። ቀጥሎ በተገለጸው ውይይት ላይ እንዳለው ወላጅ የምታደርጉ ከሆነ በልጃችሁ ልብ ውስጥ ያለውን ለማወቅ አትችሉም።
ልጅ፦ ከአሁን በኋላ ስብሰባ መሄድ አልፈልግም።
አባት፦ [ቁጣ ባዘለ ድምፅ] ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
ልጅ፦ በቃ! ይደብረኛል!
አባት፦ ምን! ይደብረኛል? እንዴት ነው አምላክ የሚደብርህ? እዚህ ቤት እስከኖርክ ድረስ ወደድክም ጠላህ አብረኸን ጉባኤ ትሄዳታለህ! ምንም ምርጫ እንደሌለህ እወቅ!
አምላክ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ እሱ እንዲያስተምሯቸው፣ ልጆች ደግሞ ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ ይጠብቅባቸዋል። (ኤፌሶን 6:1) ይሁን እንጂ ልጃችሁ ከአምልኳችሁ ጋር በተያያዘ የምታደርጓቸውን ነገሮች እንዲያው እናንተ ስላደረጋችሁት ብቻ እንዲያደርግና ሳይወድ በግዱ አብሯችሁ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዲሄድ እንደማትፈልጉ የተረጋገጠ ነው። ከዚህ ይልቅ ስብሰባ ላይ የሚገኘው ይህን ማድረግ እንደሚያስፈልገው አምኖበትና ይሖዋን ስለሚወድ እንዲሆን ትፈልጋላችሁ።
እንዲህ ለማድረግ ደግሞ ልጃችሁ እምነቱን ለመተው እንዲያስብ ያደረጉትን ከበስተጀርባ ያሉ ምክንያቶች ማስተዋል ያስፈልጋችኋል። ይህን በአእምሯችሁ ይዛችሁ፣ ከላይ የቀረበውን ውይይት በተሻለ መንገድ ማካሄድ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ልብ በሉ።
ልጅ፦ ከአሁን በኋላ ስብሰባ መሄድ አልፈልግም።
አባት፦ [ረጋ ብሎ] እንዲህ ያልከው ለምንድን ነው?
ልጅ፦ በቃ! ይደብረኛል!
አባት፦ እርግጥ ነው፣ ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዓት ቁጭ ማለት አሰልቺ ሊሆን ይችላል። አንተ ይበልጥ ፈታኝ የሆነብህ ምኑ ነው?
ልጅ፦ እኔ እንጃ። በዚያ ሰዓት ሌላ ቦታ ብሄድ እንደሚሻል ይሰማኛል።
አባት፦ ጓደኞችህም የሚሰማቸው እንደዚህ ነው?
ልጅ፦ ለነገሩ ችግሬ ይሄ ነው መሰለኝ። ምንም ጓደኛ የለኝም! የቅርብ ጓደኛዬ ሰፈር ከቀየረ በኋላ የማዋራው ሰው የለም! ሁሉም ሰው ጓደኛ አለው። እኔ ግን ብቸኛ ነኝ!
ከላይ በቀረበው ውይይት ላይ የተጠቀሰው አባት በጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኘው ልጁ አእምሮ ውስጥ የሚጉላሉትን ነገሮች ማወቅ ችሏል፤ ይህ ልጅ ያሳሰበው ብቸኛ መሆኑ “ታጋሽ ሁኑ!” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
እንደሆነ አባትየው መገንዘብ ችሏል። ከዚህም ሌላ ይህ ወላጅ በመካከላቸው የመተማመን ስሜት እንዲፈጠር ስላደረገ ወደፊት በነፃነት ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል በር ከፍቷል።—ብዙ ወጣቶች ለመንፈሳዊ እድገታቸው እንቅፋት የሆነባቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ ከተወጡት አብዛኛውን ጊዜ በራሳቸው መተማመን እንደሚችሉ እንዲሁም ስለ እምነታቸው ያላቸው አመለካከት እንደሚሻሻል ከጊዜ በኋላ ተገንዝበዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰውንና በትምህርት ቤቱ ክርስቲያን መሆኑን ለማሳወቅ ተሸማቅቆ የነበረውን ራሞንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ራሞን፣ ፌዝ ቢያስከትልበትም እንኳ ስለ እምነቱ መናገር እሱ ያሰበውን ያህል የሚያሳቅቅ ነገር እንዳልሆነ ውሎ አድሮ ተገንዝቧል። እንዲህ ብሏል፦
“በትምህርት ቤት ሳለሁ አንድ ልጅ በሃይማኖቴ ምክንያት ቀለደብኝ። በዚህ ጊዜ በጣም ተጨነቅኩ፤ ደግሞም ክፍሉ ውስጥ ያሉት ልጆች ሁሉ ትኩረታቸው እኛ ላይ ነበር። ከዚያ ግን እሱን ራሱን ስለ እምነቱ ጠየቅኩት። የሚገርመው ነገር ጭራሽ እሱ ራሱ ተደናገጠ! በዚህ ጊዜ፣ ብዙዎቹ ወጣቶች ስለ ሃይማኖታቸው በደንብ እንደማያውቁ ተገነዘብኩ። ቢያንስ እኔ የማምንበትን ነገር ለሌሎች ማስረዳት እችላለሁ። እውነቱን ለመናገር፣ የእምነት ጉዳይ ከተነሳ ማፈር ያለባቸው የክፍሌ ተማሪዎች እንጂ እኔ አይደለሁም!”
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ክርስቲያን በመሆኑ ምን እንደሚሰማው በመጠየቅ በልቡ ያለውን ለማወቅ ጥረት አድርጉ። በእሱ አመለካከት ክርስቲያን መሆን ምን ጥቅሞች አሉት? ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎችስ ያስከትላል? ከተፈታታኝ ሁኔታዎቹ ይልቅ ጥቅሞቹ ያመዝናሉ? ከሆነስ እንዴት? (ማርቆስ 10:29, 30) ልጃችሁ ክርስቲያን መሆን ያሉትን ጥቅሞችና የሚያስከትላቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በወረቀት ላይ እንዲያሰፍር አበረታቱት፤ በወረቀቱ ላይ በስተግራ በኩል ተፈታታኝ ሁኔታዎቹን፣ በስተቀኝ በኩል ደግሞ ጥቅሞቹን መጻፍ ይችላል። ልጃችሁ ሐሳቡን በወረቀት ላይ አስፍሮ ማየቱ የራሱን ችግር ለይቶ ለማወቅና መፍትሔ ለመፈለግ ሊረዳው ይችላል።
የልጃችሁ “የማሰብ ችሎታ”
ወላጆችና አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ትንንሽ ልጆች የሚያስቡበት መንገድ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ከሚያስቡበት መንገድ በጣም ይለያል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) ብዙውን ጊዜ ትንንሽ ልጆች የተነገራቸውን ነገር አለምንም ማንገራገር የሚቀበሉ ሲሆን በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ግን ከተነገራቸው ነገር በስተጀርባ ያሉትን ምክንያቶች ለማወቅ ይሻሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ለአንድ ትንሽ ልጅ አምላክ ሁሉንም ነገሮች እንደፈጠረ ቢነገረው ለመቀበል አያንገራግርም። (ዘፍጥረት 1:1) በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ግን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች በአእምሮው ይፈጠሩ ይሆናል፦ ‘አምላክ እንዳለ እንዴት አውቃለሁ? ፍቅር የሆነ አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? አምላክ መጀመሪያ የለውም የሚለው ሐሳብ እውነት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?’—መዝሙር 90:2
ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን ማንሳቱ እምነቱ እየደከመ እንደሆነ የሚያሳይ ይመስላችሁ ይሆናል። እንደ እውነቱ የሐዋርያት ሥራ 17:2, 3
ከሆነ ግን፣ እምነቱን ለማሳደግ እየጣረ እንደሆነ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ጥያቄ ማንሳት ለአንድ ክርስቲያን መንፈሳዊ እድገት ወሳኝ ነገር ነው።—ከዚህም በላይ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ‘በማሰብ ችሎታው’ መጠቀምን እየተማረ ነው። (ሮም 12:1, 2) በመሆኑም ትንሽ ልጅ እያለ የማይችለውን ነገር ማድረግ ይኸውም የክርስትና እምነት “ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ” መረዳት ይችላል። (ኤፌሶን 3:18) ልጃችሁ፣ የተማራቸው ነገሮች በጠንካራ ማስረጃ የተደገፉ መሆናቸውን በራሱ በማረጋገጥ ጽኑ እምነት እንዲገነባ ለመርዳት ጊዜው አሁን ነው።—ምሳሌ 14:15፤ የሐዋርያት ሥራ 17:11
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ወደኋላ ተመልሳችሁ እናንተና ልጃችሁ በቀላሉ አምናችሁ የተቀበላችኋቸውን መሠረታዊ ትምህርቶች ተወያዩባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ እንደሚከተሉት ባሉት ጥያቄዎች ላይ እንዲያሰላስል አበረታቱት፦ ‘አምላክ እንዳለ እኔን የሚያሳምነኝ ምንድን ነው? አምላክ እንደሚያስብልኝ የሚያሳይ ምን ማስረጃ ተመልክቻለሁ? የአምላክን ሕጎች መታዘዝ ምንጊዜም ጥቅሙ ለራሴ ነው የምለው ለምንድን ነው?’ ልጃችሁ የእናንተን አመለካከት እንዲቀበል እንዳትጫኑት ተጠንቀቁ። ከዚህ ይልቅ እሱ ራሱ በተማረው ነገር ላይ እምነት እንዲያዳብር እርዱት። እንዲህ ካደረጋችሁ ስለሚያምንባቸው ነገሮች እርግጠኛ መሆን ይችላል።
“አሳምነውህ በተቀበልካቸው”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ወጣት ‘ከጨቅላነቱ ጀምሮ’ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያውቅ እንደነበር ይናገራል። ያም ሆኖ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን “በተማርካቸውና ሰዎች አሳምነውህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ቀጥል” በማለት መክሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁም ከጨቅላነቱ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ተምሮ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን የራሱ የሆነ ጽኑ እምነት እንዲኖረው፣ የተማረውን ነገር እንዲያምንበት ልትረዱት ይገባል።
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ ከእናንተ ጋር እስከኖረ ድረስ በምታደርጓቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈል የመጠየቅ መብት አላችሁ። ይሁን እንጂ ግባችሁ፣ ልጃችሁ ለአምላክ ፍቅር እንዲያዳብር መርዳት እንጂ እንዲሁ በዘልማድ ነገሮችን እንዲያከናውን ማድረግ አይደለም።” ይህን ግብ በአእምሯችሁ በመያዝ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ ‘በእምነቱ ጸንቶ እንዲቆም’ እና የክርስትናን ጎዳና እናንተ ስለምትከተሉት ብቻ ሳይሆን እሱ ራሱ አምኖበት እንዲከተል ልትረዱት ትችላላችሁ። *—1 ጴጥሮስ 5:9
^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.5 ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ ርዕስ ውስጥ በጉርምስና ዕድሜ ስለሚገኙ ልጆች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።
^ አን.40 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የግንቦት 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 10-12 እና ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 (እንግሊዝኛ) ከገጽ 315-318 ተመልከት።
ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦
-
ልጄ እምነቴን እንደሚጠራጠር ቢነግረኝ ምን ምላሽ እሰጠዋለሁ?
-
በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረበውን ሐሳብ በመጠቀም የተሻለ ምላሽ መስጠት የምችለው እንዴት ነው?