በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ቃል ተማር

አምላክ ድርጅት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

አምላክ ድርጅት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶቹን መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።

1. አምላክ እስራኤላውያንን ያደራጃቸው ለምንድን ነው?

አምላክ የአብርሃምን ዘሮች በብሔር ካደራጃቸው በኋላ የሚመሩባቸውን ሕግጋት ሰጥቷቸዋል። ይህን ብሔር፣ እስራኤል ብሎ የጠራው ሲሆን እውነተኛውን አምልኮና ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በአደራ ሰጥቷቸዋል። (መዝሙር 147:19, 20) ይህም ለሁሉም ብሔራት ጥቅም አስገኝቷል።​—ዘፍጥረት 22:18ን አንብብ።

አምላክ እስራኤላውያንን ምሥክሮቹ እንዲሆኑ መርጧቸዋል። እስራኤላውያን ታዛዦች በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ከአምላክ ሕግጋት ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር። (ዘዳግም 4:6) የእስራኤላውያንን ታሪክ በማጥናት ስለ እውነተኛው አምላክ ይበልጥ ማወቅ እንችላለን።​—ኢሳይያስ 43:10, 12ን አንብብ።

2. እውነተኛ ክርስቲያኖች ድርጅት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን የአምላክን ሞገስ አጡ፤ በመሆኑም ይሖዋ ይህን ብሔር በመተው የክርስቲያን ጉባኤን አቋቋመ። (ማቴዎስ 21:43፤ 23:37, 38) ከዚያ ቀደም እስራኤላውያን የአምላክ ምሥክሮች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እውነተኛ ክርስቲያኖች የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ያገለግላሉ።​—የሐዋርያት ሥራ 15:14, 17ን አንብብ።

ኢየሱስ ተከታዮቹን ስለ ይሖዋ እንዲመሠክሩና ከሁሉም ብሔራት ደቀ መዛሙርት እንዲያፈሩ አደራጅቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:7, 11፤ 24:14፤ 28:19, 20) ይህ ሥራ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየተከናወነ ሲሆን ወደ መደምደሚያውም እየተቃረበ ነው። በዛሬው ጊዜ፣ ይሖዋ ከሁሉም ብሔራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በእውነተኛው አምልኮ አንድ እንዲሆኑ አድርጓል። (ራእይ 7:9, 10) እውነተኛ ክርስቲያኖች የተደራጁ መሆናቸው እርስ በርስ ለመበረታታትና ለመረዳዳት ያስችላቸዋል። በዓለም ዙሪያ በስብሰባዎቻቸው ላይ አንድ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጣቸዋል።​—ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።

3. የይሖዋ ምሥክሮች በዘመናችን ሥራቸውን የጀመሩት እንዴት ነው?

በዘመናችን ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት የተቋቋመው በ1870ዎቹ ዓመታት ነበር። የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ያቀፈ አንድ ትንሽ ቡድን ለብዙ ዓመታት ተዳፍነው የቆዩትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች እንደገና ማግኘት ጀመረ። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን ያደራጀው በስብከቱ ሥራ እንዲካፈል እንደሆነ አውቀው ነበር። ስለሆነም በዓለም ዙሪያ ስለ አምላክ መንግሥት የመስበኩን ዘመቻ ተያያዙት። በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም መጠራት ጀመሩ።​—የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ 2:1, 4፤ 5:42ን አንብብ።

4. የይሖዋ ምሥክሮች በዛሬው ጊዜ የተደራጁት እንዴት ነው?

በአንደኛው መቶ ዘመን በበርካታ አገሮች ይገኙ የነበሩት የክርስቲያን ጉባኤዎች መመሪያ የሚያገኙት ኢየሱስን እንደ ጉባኤው ራስ አድርጎ ከሚመለከት አንድ የበላይ አካል ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስን እንደ መሪያቸው አድርገው ይመለከቱታል። (ማቴዎስ 23:9, 10) በተጨማሪም ተሞክሮ ያካበቱ ሽማግሌዎችን ያቀፈው የበላይ አካል ከሚሰጠው አመራር ጥቅም ያገኛሉ፤ ይህ የበላይ አካል ከ100,000 ለሚበልጡ ጉባኤዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻና አመራር ይሰጣል። በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ሆነው የሚያገለግሉ ብቃት ያላቸው ወንዶች አሉ። እነዚህ ወንዶች የአምላክን መንጋ በፍቅር ይንከባከባሉ።​—1 ጴጥሮስ 5:2, 3ን አንብብ።

የይሖዋ ምሥክሮች የተደራጁት ምሥራቹን ለመስበክና ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ነው። በሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ሲሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከ500 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይተረጉማሉ፣ ያትማሉ እንዲሁም ያሰራጫሉ። ልክ እንደ ሐዋርያት ከቤት ወደ ቤት ይሰብካሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:20) የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን የሚወዱ ቅን ሰዎች ሲያገኙ መጽሐፍ ቅዱስን ከእነሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ እንዲያጠኑ ይጋብዟቸዋል። የይሖዋ ሕዝቦች፣ አምላክን በማስደሰትና ሌሎችን በመርዳቱ ሥራ ላይ ስለሚያተኩሩ ድርጅታቸው ደስተኛ በሆኑ ሰዎች የተሞላ ነው።​—መዝሙር 33:12ን እና የሐዋርያት ሥራ 20:35ን አንብብ።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 19 ተመልከት።