በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በመካከላችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’

‘በመካከላችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’

‘በመካከላችሁ ፍቅር ይኑራችሁ’

“እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እየሰጠኋችሁ ነው፤ ልክ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”​—ዮሐንስ 13:34, 35

ይህ ምን ማለት ነው? ክርስቶስ ልክ እሱ እንደወደዳቸው እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። ኢየሱስ እነሱን የወደዳቸው እንዴት ነበር? ኢየሱስ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ በተለየ መልኩ ሰዎችን በብሔር እና በፆታ ሳይለይ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ፍቅር አሳይቷል። (ዮሐንስ 4:7-10) ኢየሱስ ሌሎችን ለመርዳት ሲል ጊዜውን፣ ጉልበቱንና የግል ምቾቱን መሥዋዕት እንዲያደርግ የገፋፋው ፍቅር ነበር። (ማርቆስ 6:30-34) በመጨረሻም ክርስቶስ ከሁሉ በሚበልጠው መንገድ ፍቅሩን አሳይቷል። “እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤ ጥሩ እረኛ ነፍሱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል” በማለት ተናግሯል።​—ዮሐንስ 10:11

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ብቃት አሟልተዋል? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ‘ወንድም’ ወይም ‘እህት’ እየተባባሉ ይጠራሩ ነበር። (ፊልሞና 1, 2) ክርስቲያኖች “የሁሉም ጌታ አንድ ስለሆነ በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ምንም ልዩነት [እንደሌለ]” ያምኑ ነበር፤ በመሆኑም ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ተቀብለዋቸዋል። (ሮም 10:11, 12) በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ በኢየሩሳሌም የነበሩት ደቀ መዛሙርት “ያላቸውን ሀብትና ንብረት በመሸጥ ገንዘቡን ለእያንዳንዱ ሰው እንደሚያስፈልገው ያከፋፍሉ ነበር።” ይህን ያደረጉት ለምንድን ነው? በቅርብ የተጠመቁት ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ቆይተው “የሐዋርያትን ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን” መቀጠል እንዲችሉ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:41-45) ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ሐዋርያት ከሞቱ ወደ 200 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ተርቱሊያን ሌሎች ሰዎች ስለ ክርስቲያኖች የተናገሩትን ጠቅሶ ሲጽፍ “እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዋደዱ፣ . . . አልፎ ተርፎም አንዳቸው ለሌላው ለመሞት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ ተመልከቱ” ብሎ ነበር።

በዛሬው ጊዜ ብቃቱን የሚያሟሉት እነማን ናቸው? ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዲክላይን ኤንድ ፎል ኦቭ ዘ ሮማን ኢምፓየር (1837) የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚናገሩ ግለሰቦች “አንዳቸው በሌላው ላይ የፈጸሙት የጭካኔ ድርጊት የማያምኑ ሰዎች ካደረሱባቸው የከፋ ነው።” በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳሳየው ሃይማኖተኛ ሰዎች (አብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ባዮች ናቸው) ብዙውን ጊዜ የዘር መድሎ ይፈጽማሉ። በአንድ አገር ያሉ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ብዙውን ጊዜ በሌላ አገር ካሉ የራሳቸው ሃይማኖት አባላት ጋር ኅብረት ስለሌላቸው የእምነት አጋሮቻቸውን በችግራቸው ወቅት ለመርዳት አይችሉም ወይም ይህን ለማድረግ አይፈልጉም።

በ2004 ፍሎሪዳ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በተከታታይ በአራት ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች በተመታች ወቅት፣ የፍሎሪዳ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የእርዳታ አቅርቦታቸው በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ለማረጋገጥ ምርመራ አድርገው ነበር። እኚህ ሰው፣ የይሖዋ ምሥክሮችን ያህል በደንብ የተደራጀ ሌላ ቡድን እንዳላዩ የተናገሩ ሲሆን የሚያስፈልጋቸውን የእርዳታ አቅርቦት ለይሖዋ ምሥክሮች ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ከዚያ ቀደም ብሎ ይኸውም በ1997 በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች የእርዳታ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና ሌሎችንም የተቸገሩ ሰዎች ለመርዳት መድኃኒት፣ ምግብና ልብስ ይዘው ወደዚያ ተጉዘው ነበር። እርዳታው የተገኘው በአውሮፓ ያሉ የእምነት አጋሮቻቸው በድምሩ አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የእርዳታ አቅርቦት በኮንጎ ላሉት ወንድሞቻቸው በመለገሳቸው ነው።