በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ቀለሞችና ጨርቆች

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ቀለሞችና ጨርቆች

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ቀለሞችና ጨርቆች

በጥንት ዘመን የኖሩ ሰዎች የነበራቸውን አለባበስ እንዲሁም ልብስ ለመስፋት የሚጠቀሙባቸውን ጨርቆችና የጨርቆቹን ቀለም በተመለከተ ብዙ መረጃዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት እንችላለን።

እርግጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፋሽንና አለባበስ ለመግለጽ የተጻፈ መጽሐፍ አይደለም። ሆኖም የተጠቀሱት ዝርዝር መግለጫዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ሕያው እንዲሆኑልን ስለሚያደርጉ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል ያስችሉናል።

ለምሳሌ አዳምና ሔዋን እርቃናቸውን ለመሸፈን የበለስ ቅጠል ሰፍተው እንዳገለደሙ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በኋላ ላይ ግን አምላክ በዚህ የቅጠል ግልድም ፋንታ፣ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ‘የቈዳ ልብስ አዘጋጅቶ’ ሰጥቷቸዋል።​—ዘፍጥረት 3:7, 21

በተጨማሪም በ⁠ዘፀአት ምዕራፍ 28 እና 39 ላይ የእስራኤል ሊቀ ካህናት ስለሚለብሳቸው ልብሶች ዝርዝር መግለጫ እናገኛለን። ሊቀ ካህናቱ ከሚጠቀምባቸው አልባሳት መካከል ከበፍታ የተሠራ ቁምጣ፣ ነጭ ቀሚስ፣ በቀጭኑ የተፈተለ መታጠቂያ፣ ሰማያዊ ቀሚስ፣ የተጠለፈ ኤፉድና የደረት ኪስ የሚገኙ ሲሆን ራሱ ላይ ደግሞ ጥምጥም እና የሚያንጸባርቅ ጥፍጥፍ ወርቅ ያደርግ ነበር። እነዚህ አልባሳት ውድ ከሆኑ በርካታ ነገሮች እንዴት እንደተሠሩ የሚገልጸውን ዘገባ ማንበብ ብቻ እንኳ አልባሳቱ ምን ያህል ውብ እንደነበሩ መገመት ያስችለናል።​—ዘፀአት 39:1-5, 22-29

የነቢዩ ኤልያስ ልብስ ደግሞ በጣም የተለየ ነበር፤ በመሆኑም “ሰውየው ጠጕራም ልብስ የለበሰ ነው፤ በወገቡም ላይ ጠፍር ታጥቆአል” የሚለውን መግለጫ የሰሙ ሰዎች ግለሰቡ ኤልያስ መሆኑን በቀላሉ ማወቅ ችለዋል። በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ አንዳንድ ሰዎች አጥማቂው ዮሐንስን ሲያዩ ኤልያስ መስሏቸው ነበር፤ ይህን ያሉት ልብሳቸው ይመሳሰል ስለነበረ ሊሆን ይችላል።​—2 ነገሥት 1:8፤ ማቴዎስ 3:4፤ ዮሐንስ 1:21

ጨርቆችና ቀለሞች መጽሐፍ ቅዱስ ልብስ ለመስፋት ያገለግሉ ስለነበሩ የጨርቅ ዓይነቶች፣ ስለ ቀለሞችና ለማቅለሚያ ስለሚያገለግሉ ንጥረ ነገሮች እንዲሁም ስለ ፈትል፣ ሽመናና ስፌት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይናገራል። * በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ዋነኞቹ የጨርቃ ጨርቅ ዓይነቶች ከቤት እንስሳት የሚገኘው ሱፍና ከተልባ ተክል የሚገኘው በፍታ (የተልባ እግር) ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አቤል “የበግ እረኛ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘፍጥረት 4:2) አቤል በጎችን ያረባ የነበረው ለሱፋቸው ብሎ ይሁን አይሁን መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከጥሩ የተልባ እግር ወይም በፍታ ስለተሠራ ልብስ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው ፈርዖን ለዮሴፍ ስላለበሰው ልብስ በሚናገረው ታሪክ ላይ ሲሆን ይህም የሆነው በ18ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነው። (ዘፍጥረት 41:42) ጥጥ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከጥንት ጀምሮ ለልብስ መሥሪያነት ያገለግል የነበረ ቢሆንም አይሁዳውያን ልብስ ለማዘጋጀት ይጠቀሙበት እንደነበረ የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም።

የተልባ እግርም ሆነ ሱፍ ሲፈተሉ የተለያየ ውፍረት ያለው ድርና ማግ ያስገኙ ነበር። ከዚያም ፈትሎቹ ተሸምነው ጨርቅ ያስገኛሉ። ፈትሎችና የተሸመኑ ጨርቆች የተለያዩ ቀለሞች ይነከራሉ። ከዚያ በኋላ ጨርቆቹ በለባሹ ልክ ተቆራርጠው ይዘጋጃሉ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች፣ ልብሶቹን የተለያየ ሕብረ ቀለም ባላቸው ክሮች በመጥለፍ ያስጌጧቸው ነበር፤ ይህም ለልብሶቹ ውበት የሚሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ዋጋቸውን ከፍ ያደርገዋል።​—መሳፍንት 5:30

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሱት የልብስ ቀለሞች ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ናቸው። እስራኤላውያን ከአምላካቸው ከይሖዋ ጋር የተለየ ዝምድና እንዳላቸው እንዲያስታውሱ ‘በልብሳቸው ጫፍ ላይ ሰማያዊ ጥለትና ዘርፍ’ እንዲያደርጉ ታዝዘው ነበር። (ዘኍልቍ 15:38-40) ከሊቀ ካህናቱ ልብስ እንዲሁም ከማደሪያው ድንኳንና በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከነበሩት ማስጌጫዎች ጋር በተያያዘ የተጠቀሱትን ቀለሞች ለመግለጽ የተሠራባቸው የዕብራይስጥ ቃላት፣ ወደ ሰማያዊ የሚጠጋ ቀለምን የሚያመለክተው ተኼሌት እና አብዛኛውን ጊዜ “ሐምራዊ” ተብሎ የተተረጎመው አርጋማን ናቸው።

የማደሪያው ድንኳንና የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች በምድረ በዳ የነበረው የማደሪያ ድንኳንና በኋላም በኢየሩሳሌም የተሠራው ቤተ መቅደስ ለእስራኤላውያን የአምልኮ ማዕከል ነበሩ። በመሆኑም የማደሪያውን ድንኳንና የሰለሞንን ቤተ መቅደስ አሠራር እንዲሁም በውስጣቸው የሚቀመጡትን ዕቃዎች በተመለከተ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች መገለጻቸው የሚያስገርም አይደለም። የድንኳኑን መጋረጃዎች ለመሥራት ስለሚያገለግሉት ነገሮችና ስለ ቀለማቸው ብቻ ሳይሆን ጨርቆቹ ስለሚሸመኑበት፣ ስለሚቀልሙበትና ስለሚሰፉበት እንዲሁም ስለሚጠለፉበት መንገድ ዝርዝር መግለጫ እናገኛለን።

የተዋጣላቸው የእጅ ሙያተኞች የነበሩት ባስልኤልና ኤልያብ እንዲሁም ሌሎች ወንዶችና ሴቶች በአምላክ መንፈስ እየተመሩ ለይሖዋ አምልኮ የሚመጥን የመገናኛ ድንኳን በመሥራት የተሰጣቸውን ልዩ ኃላፊነት በታማኝነት ተወጥተዋል። (ዘፀአት 35:30-35) በ⁠ዘፀአት ምዕራፍ 26 ላይ የማደሪያውን ድንኳን ለመሥራት ስላገለገሉት ቁሳቁሶችና የድንኳኑ ክፍሎች በሙሉ እንዴት እንደተሠሩ በዝርዝር ተገልጾ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ሰፊ የሆነው የድንኳኑ ጨርቅ “በቀጭኑ ከተፈተለ የበፍታ ድርና በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ” የተሠራ ነበር። እስራኤላውያን ከእነዚህ ጥሬ ዕቃዎች አብዛኞቹን ያመጧቸው ከግብፅ ሲወጡ ሊሆን ይችላል። የኪሩቤል ምስሎች ለተጠለፈበትና በማደሪያው ድንኳን ውስጥ “በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ” ሆኖ ለሚያገለግለው የሚያምር ቀለም ያለው ወፍራም መጋረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ነበር። (ዘፀአት 26:1, 31-33 የ1954 ትርጉም) በንጉሥ ሰለሞን መሪነት በኢየሩሳሌም በተሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉትን ጨርቆች ላዘጋጁት ሰዎችም በተመሳሳይ ዝርዝር መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር።​—2 ዜና መዋዕል 2:1, 7

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠብቆልን ከቆየው ዝርዝር መግለጫ ማየት እንደምንችለው የጥንቶቹ ዕብራውያን ሊያገኟቸው በሚችሏቸው ጥሬ ዕቃዎች በመጠቀም የተለያዩ ነገሮችን በብልሃት ይሠሩና አዳዲስ ነገሮችን ይፈጥሩ ነበር። ስለ እስራኤላውያን ስናስብ ወደ አእምሯችን የሚመጡት የማይስብና የማያምር ልብስ የሚለብሱ እንዲሁም መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ከማሟላት ውጪ ሌላ ነገር የማያውቁ አሰልቺ ሕይወት ያላቸው ሕዝቦች አይደሉም፤ ከዚህ በተቃራኒ ሕዝቡ፣ እንደየቤተሰቡ የአቅም ሁኔታ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶችና ወቅቶች ላይ የሚለብሷቸው ልዩ ልዩ ቀለምና አሠራር ያላቸው የሚያምሩ ልብሶች ነበሯቸው።

እስራኤላውያን ‘ማርና ወተት የምታፈስ’ መልካም ምድር ርስት ሆና እንደተሰጠቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፀአት 3:8፤ ዘዳግም 26:9, 15) እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ብቻ እስካመለኩ ድረስ ይሖዋ ይባርካቸው ነበር። ጥሩ ሕይወት የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ተደስተውና ረክተው ይኖሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ “[በንጉሥ] ሰሎሞን ዘመን ሁሉ ከዳን አንሥቶ እስከ ቤርሳቤህ ያለው ይሁዳና እስራኤል፣ እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ ጥላ ሥር በሰላም ለመኖር በቃ” ይላል።​—1 ነገሥት 4:25

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ሣጥኖቹን ተመልከት።

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]

ሱፍ እና በፍታ

በጥንት ዘመን፣ ሰዎች በዋነኝነት በጎች የሚያረቡት ለወተታቸውና ከእነሱ ለሚገኘው ሱፍ ነበር። አንድ ገበሬ ከጥቂት በጎች ለቤተሰቡ ልብስ ለማዘጋጀት የሚበቃ ሱፍ ማግኘት ይችላል። ገበሬው ብዙ በጎች የሚያረባ ከሆነ የተረፈውን ሱፍ ለልብስ አምራቾች መሸጥ ይችላል። በአንዳንድ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ማኅበራት ነበሩ። ከጥንት ዘመን ጀምሮ፣ በጎችን መሸለት ሕዝቡ በየዓመቱ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች አንዱ ነበር።​—ዘፍጥረት 31:19፤ 38:13፤ 1 ሳሙኤል 25:4, 11

ተወዳጅ የሆነው የበፍታ ጨርቅ የሚዘጋጀው ከተልባ ተክል ነበር። (ዘፀአት 9:31) ተልባው የሚታጨደው እድገቱን ሊጨርስ ሲቃረብ ነው። አገዳው ፀሐይ ላይ ተሰጥቶ ከደረቀ በኋላ እንዲለሰልስ ውኃ ውስጥ ይዘፈዘፋል። ከውኃው ወጥቶ ከደረቀ በኋላ ቃጫውን ከአገዳው ለመለየት ይቀጠቀጣል፤ ከዚያም ቃጫዎቹ ተፈትለው ይሸመናሉ። የንጉሣውያን ቤተሰቦችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከተልባ እግር የተሠራ ልብስ ይመርጡ ነበር።

[ሥዕል]

የደረቀ የተልባ እግር ውኃ ውስጥ ከመነከሩ በፊት

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]

መፍተል

የበግም ሆነ የፍየል አንዷ ፀጉር ወይም አንዷ የተልባ እግር ቃጫ ብቻዋን በጣም አጭርና በቀላሉ የምትበጠስ በመሆኗ ጥቅም ላይ ልትውል አትችልም። ስለሆነም የሚፈለገውን ያህል ውፍረትና ርዝመት ያላቸው ድሮች ለማግኘት በርከት ያሉ ፀጉሮች ወይም ቃጫዎች አንድ ላይ ይፈተላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ባለሙያ ስለሆነች ሚስት ሲናገር “በእጇ እንዝርት ትይዛለች፤ በጣቶቿም ዘንጉን ታሾራለች” ይላል። (ምሳሌ 31:10, 19) ይህ ጥቅስ ሴቶች ሲፈትሉ በሁለት እንጨቶች ይኸውም በዘንግና በእንዝርት ይጠቀሙ እንደነበር ይገልጻል።

የምትፈትለው ሴት፣ ቃጫ ወይም የበግ ፀጉር የተጠመጠመበትን ዘንግ በአንድ እጇ ትይዛለች። በሌላ እጇ ጥቂት ቃጫዎች ወይም ፀጉሮች መዘዝ አድርጋ እየፈተለች ታከርረዋለች፤ ከዚያም በእንዝርት ጫፍ ላይ ከተተከለ መንጠቆ ጋር ታያይዘዋለች። በእንዝርቱ መሃል አካባቢ እንዝርቱ እንዲሽከረከር የሚያደርግ ክብ ነገር ይሰካል። ሴትየዋ እንዝርቱን ቁልቁል አንጠልጥላ ስታሽከረክረው ፈትሉ እየከረረ የምትፈልገውን ያህል ውፍረት ያለው ክር ይሆናል። ቀጥላም የተፈተለውን ክር በእንዝርቱ ዘንግ ላይ ታጠነጥነዋለች፤ በዘንጉ ላይ የተጠመጠመው ቃጫ ወይም ፀጉር በሙሉ ተፈትሎ አንድ ረጅም ክር እስኪሆን ድረስ ይኸው ሂደት ይቀጥላል። በመጨረሻም ክሩ ለመቅለም ወይም ለመሸመን ዝግጁ ይሆናል።

[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]

ማቅለም

የተፈተለው ሱፍ ወይም በፍታ ከታጠበ በኋላ የተለያየ ቀለም ይነከራል፤ የተሸመነውም ጨርቅ ቢሆን ቀለም ሊነከር ይችላል። ክሩ ወይም ጨርቁ ደማቅ ቀለም እንዲኖረው ከተፈለገ በተደጋጋሚ ይነከራል። ቀለም ውድ በመሆኑ ጨርቁ ከማቅለሚያው ጉድጓድ ውስጥ ከወጣ በኋላ ይጨመቃል፤ ከዚያም የተጨመቀው ቀለም ሌላ ጨርቅ ለማቅለም ይውላል። ቀጥሎም ቀለም የተነከረው ድር ወይም ጨርቅ እንዲደርቅ ይሰጣል።

በጥንት ዘመን ሰው ሠራሽ ቀለም ማግኘት ስለማይቻል ሰዎች ከእንስሳትና ከዕፅዋት ተዋጽኦዎች ብዙ ዓይነት ያላቸው ብሎም የማይለቁ ቀለሞችን ይሠሩ ነበር። ለምሳሌ፣ ቢጫ ቀለም ለመሥራት የአልሞንድ ቅጠሎችንና የተፈጨ የሮማን ልጣጭ የሚጠቀሙ ሲሆን ከሮማን ዛፍ ቅርፊት ደግሞ ጥቁር ቀለም ይሠሩ ነበር። ቀይ ቀለም የሚሠሩት ማደር ከሚባለው ተክል ሥሮች ወይም ከርሚስ ከሚባለው ነፍሳት ነበር። ሰማያዊ ቀለም ኢንዲጎ ከሚባለው አበባ ይዘጋጅ ነበር። ሚውሬክስ ከሚባሉት የተለያዩ የባሕር ቀንድ አውጣዎች የሚገኘውን ቀለም በመቀላቀል ሐምራዊ፣ ሰማያዊና ደማቅ ቀይ ቀለሞችን መሥራት ይቻል ነበር።

አንድን ልብስ ለማቅለም ምን ያህል የባሕር ቀንድ አውጣዎች ያስፈልጉ ነበር? ከእያንዳንዱ የባሕር ቀንድ አውጣ የሚገኘው የቀለም መጠን በጣም ትንሽ በመሆኑ አንድ ጥናት እንዳመለከተው አንድ ልብስ ወይም ካባ ደማቅ ሐምራዊ ቀለም እንዲኖረው ለማድረግ እስከ 10,000 የሚደርሱ ቀንድ አውጣዎች ያስፈልጉ ነበር፤ ከዚህ አንጻር በአንዳንድ ቋንቋዎች ይህ ቀለም “ንጉሣዊ ሐምራዊ” የሚል ስያሜ የተሰጠው መሆኑ ተገቢ ነው። በባቢሎኑ ንጉሥ በናቦኒደስ ዘመነ መንግሥት ሐምራዊ ቀለም ያለው ሱፍ ዋጋ ሌሎች ቀለሞች ከተነከረ ሱፍ በ40 እጥፍ ይወደድ እንደነበር ይነገራል። የጥንቷ ጢሮስ ይህን ውድ ቀለም በማቅረብ የታወቀች ስለነበረች ሐምራዊ ቀለም “የጢሮስ ሐምራዊ” ተብሎ ይጠራ ነበር።

[ሥዕሎች]

የባሕር ቀንድ አውጣ ዛጎል

በቴል ዶር፣ እስራኤል የተገኘ በ2ኛው ወይም በ3ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተሠራ ሐምራዊ ቀለም መንከሪያ ጉድጓድ

[የሥዕል ምንጭ]

The Tel Dor Project

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]

ሽመና

ሰዎች የተፈተሉ ክሮችን ሸምነው ለልብስ ወይም ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል ጨርቅ ለማዘጋጀት የሸማኔ ዕቃ ይጠቀማሉ። በቁም መሸመኛው ላይ ወደ ታች የሚንጠለጠሉት ክሮች ድር የሚባሉ ሲሆን በጎን በኩል የሚመጡት ደግሞ ማግ ይባላሉ። ሸማኔው ማጎቹንና ድሮቹን በማጠላለፍ ወይም በማሰበጣጠር ጨርቅ ይሠራል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩት የሸማኔ ዕቃዎች መሬት ላይ የሚዘረጉ አሊያም የሚቆሙ ነበሩ። በአንዳንዶቹ የቁም መሸመኛዎች በሚሸመንበት ጊዜ በድሮቹ ጫፍ ላይ ክብደት ያለው ነገር ይደረግ ነበር። በጥንት ዘመን ሰዎች የሚጠቀሙባቸው በድሮች ላይ የሚንጠለጠሉ ክብደት ያላቸው ነገሮች በእስራኤል ምድር በበርካታ ቦታዎች ተገኝተዋል።

ሽመና በአብዛኛው እያንዳንዱ ሰው በቤቱ የሚያከናውነው ሥራ ነበር፤ በአንዳንድ መንደሮች ግን ነዋሪዎቹ በሙሉ በዚህ ሥራ ይሰማሩ ነበር። ለምሳሌ በ⁠1 ዜና መዋዕል 4:21 ላይ “የበፍታ ጨርቅ ሠሪ የሆኑት ጐሣዎች” የሚል ሐሳብ እናገኛለን፤ ይህ አገላለጽ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችን ቡድን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው።

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰማያዊ ፈትል፣ ቀይና ሐምራዊ ቀለም የተነከረ ሱፍ።​—ዘፀአት 26:1