በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በቃሌ ኑሩ’

‘በቃሌ ኑሩ’

‘በቃሌ ኑሩ’

“በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።”​—ዮሐንስ 8:31, 32

ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ “ቃሌ” ያለው እሱ ያስተማረውን ትምህርት ሲሆን ይህ ትምህርት የመነጨውም ከእሱ በላይ ሥልጣን ካለው አካል ነው። ኢየሱስ “ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ የላከኝ አብ ራሱ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 12:49) ኢየሱስ በሰማይ ወዳለው አባቱ ይኸውም ወደ ይሖዋ አምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። ላስተማረው ትምህርት ድጋፍ እንዲሆነውም የአምላክን ቃል በተደጋጋሚ ይጠቅስ ነበር። (ዮሐንስ 17:17፤ ማቴዎስ 4:4, 7, 10) በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚባሉት፣ ‘በቃሉ የሚኖሩ’ ይኸውም የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን “እውነት” እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱ እንዲሁም ከሚያምኑባቸው ነገሮችና ከተግባራቸው ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መጨረሻው ባለሥልጣን አድርገው የሚቀበሉ ሰዎች ናቸው።

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ብቃት አሟልተዋል? በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የጻፈው ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ልክ እንደ ኢየሱስ ለአምላክ ቃል አክብሮት ነበረው። ጳውሎስ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም . . . ይጠቅማል” ብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸውን እንዲያስተምሩ የተሾሙ ወንዶችም ‘የታመነውን ቃል አጥብቀው መያዝ’ ነበረባቸው። (ቲቶ 1:7, 9) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ” የሚል ምክር ተሰጥቷቸው ነበር።​—ቆላስይስ 2:8

በዛሬው ጊዜ ብቃቱን የሚያሟሉት እነማን ናቸው? ቫቲካን በ1965 በተቀበለችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማስተማሪያ ጽሑፍ (እንግሊዝኛ) ላይ የተጠቀሰው መለኮታዊ ራእይን የሚመለከት የቫቲካን ድንጋጌ (እንግሊዝኛ) እንደሚለው የቤተ ክርስቲያኗ አቋም የሚከተለው ነው፦ “[የካቶሊክ] ቤተ ክርስቲያን ስለተገለጠላት ስለ እያንዳንዱ ነገር ማስረጃ አድርጋ የምታቀርበው ቅዱስ ጽሑፉን ብቻ አይደለም። በመሆኑም ቅዱሳን ወጎችንም ሆነ ቅዱሳን መጻሕፍትን እኩል በሆነ መልኩ እምነት ልንጥልባቸውና ልዩ አክብሮት ልንሰጣቸው ይገባል።” ማክሊንስ በተሰኘ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ መጣጥፍ በቶሮንቶ፣ ካናዳ የምትገኝ አንዲት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሚከተለውን ጥያቄ እንዳቀረበች ጠቅሶ ነበር፦ “ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በተጻፈ ‘የለውጥ’ ድምፅ መመራት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? የራሳችን የሆኑ ድንቅ ሐሳቦች አሉን፤ ይሁንና ለእነዚህ ሐሳቦች ከኢየሱስና ከቅዱስ ጽሑፉ ድጋፍ ማግኘት ስለሚጠበቅብን ሁልጊዜ ኃይላቸው ይዳከምብናል።”

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ስለ የይሖዋ ምሥክሮች ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ብቸኛው የእምነታቸው መሠረትና የሥነ ምግባር መመሪያቸው አድርገው ይመለከቱታል።” በቅርቡ በካናዳ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለአንድ ሰው ራሷን ስታስተዋውቅ ግለሰቡ አቋረጣትና ወደ መጽሐፍ ቅዱሷ እያመለከተ “ማንነትሽን በምልክትሽ አውቄያለሁ” አላት።