በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሩሲያ የተላከ ደብዳቤ

በወርቃማዎቹ የአልታይ ተራሮች ውድ ሀብት መፈለግ

በወርቃማዎቹ የአልታይ ተራሮች ውድ ሀብት መፈለግ

ቀኑ በጣም ደስ ይላል፤ ያለነው በሳይቤርያ ደቡብ ምዕራብ ጫፍ ላይ በምትገኘውና ቀልብ የሚስብ ውበት ባላት የአልታይ ሪፑብሊክ ነው። በመስኮት ወደ ውጭ ስንመለከት ጥቅጥቅ ያለ ደን ይታየናል፤ ከበስተጀርባው ደግሞ ከርቀት ሰማያዊ ሆነው የሚታዩና አናታቸው በበረዶ የተሸፈነ ግዙፍ ተራሮች አሉ። ወጣ ገባ በሆነውና በአልታይ ውስጥ ርቆ በሚገኘው በዚህ ተራራማ አካባቢ አልታይኮች የሚባሉ የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው የእስያ ሕዝቦች ይገኛሉ። እነዚህ ሕዝቦች መኖሪያቸውን በአልታይ ተራሮች አድርገዋል፤ የተራሮቹ ስም የመጣው በቱርኪክ ሞንጎሊያ ቋንቋ “ወርቃማ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል ነው።

እኔና ባለቤቴ የሩሲያን የምልክት ቋንቋ ተምረን መስማት የተሳናቸው የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙባቸውን ጉባኤዎችና አነስተኛ ቡድኖች መጎብኘት ከጀመርን የተወሰኑ ዓመታት አልፈዋል። በዚህች አገር ውስጥ 170 ገደማ የሚሆኑ ብሔሮችና ጎሳዎች የሚገኙ ሲሆን የሁሉም የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ሩሲያኛ ነው። በመካከላችን ያሉት መስማት የተሳናቸው ሰዎች ደግሞ ሌላ ዓይነት ቋንቋ ይኸውም የሩሲያን የምልክት ቋንቋ ይጠቀማሉ። መስማት የተሳናቸው ሰዎች የጠበቀ ማኅበራዊ ትስስር አላቸው፤ ካገኘናቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከእኛ ጋር ስለ ሕይወታቸው መጫወት ያስደስታቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ አቀባበል አድርገውልናል። በአልታይም ይህን ሁኔታ በግልጽ ማየት ይቻላል።

ጎርኖ አልታይስክ በተባለችው ከተማ ውስጥ እያለን 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ መስማት የተሳናቸው ጥቂት ሰዎች እንደሚኖሩ ሰማን። በዚያ አካባቢ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች መኖራቸውን ብናውቅም አንዳቸውም ቢሆኑ የምልክት ቋንቋ አይችሉም። የእነዚህ መስማት የተሳናቸው የአልታይ ሰዎች ሁኔታ ስላሳሰበን ወደ እነሱ ለመሄድ ወሰንን። ዩርዪ እና ታትያና የተባሉት መስማት የተሳናቸው ባልና ሚስትም ወደዚያ ለመሄድ መጓጓታችንን ሲያዩ አብረውን ለመጓዝ ተነሳሱ። ለጉዟችን ዝግጅት ስናደርግ፣ በዲቪዲ የሚገኙ በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችንና የዲቪዲ ማጫወቻ በመኪናችን ጫንን። በተጨማሪም ትልቅ ፔርሙዝ፣ በአጃ ዳቦና በቋሊማ የተሠሩ ሳንድዊቾች እንዲሁም ትኩስ ፒሮሽኪ (ጎመንና ድንች የተከተተበት እንደ ሳንቡሳ ያለ የሩሲያውያን ጣፋጭ ምግብ) ያዝን። በመጨረሻም፣ በምንሄድበት አካባቢ በተባይ ምክንያት የሚመጣ የአንጎል በሽታ (ኢንሴፈላይተስ) የተለመደ በመሆኑ፣ በሰውነታችን ላይ እንዲሁም በልብሶቻችንና በጫማዎቻችን ላይ ተባይ መከላከያ ነፋን።

ከዚያም ውብ የሆኑትን ተራሮች እየተመለከትን ጠመዝማዛውን መንገድ ተያያዝነው። በአበቦች መልካም መዓዛ የተሞላው አየር መንፈስን ያድሳል! በጉዞ ላይ ሳለን ግጦሽ ላይ ያለ የሳይቤርያ ርኤም መንጋ ስንመለከት በጣም ደስ አለን። በአልታይ የሚገኙት እጅብ ያሉ ቤቶች ከእንጨት የተሠሩ ሲሆኑ ንጹሕ የቆርቆሮ ጣሪያ አላቸው። አብዛኞቹ ቤቶች አጠገብ ብዙውን ጊዜ ስድስት ማዕዘን ሆነው ሾጣጣ ጣሪያ ያላቸው የእንጨት ጎጆዎች ይገኛሉ፤ እነዚህ ቤቶች አይል ይባላሉ። አንዳንዶቹ አይሎች በዛፍ ቅርፊት የተሸፈኑ ጎጆ ቤቶች ይመስላሉ። በአልታይ የሚኖሩ አብዛኞቹ ቤተሰቦች ከግንቦት እስከ መስከረም ባሉት ወራት በአይሎቹ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን በቀሪዎቹ ወራት ደግሞ ወደ ዋናው ቤት ይመለሳሉ።

በአካባቢው የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሞቅ ያለ አቀባበል ካደረጉልን በኋላ መስማት የተሳናቸው አንድ የአልታይ ባልና ሚስት ወደሚኖሩበት ቤት ወሰዱን። እነዚህ ባልና ሚስት እኛን ሲያዩ ደስ አላቸው፤ ከየት እንደመጣንና ወደዚያ የሄድንበትን ምክንያትም ጠየቁን። ኮምፒውተር ስላላቸው ልክ ዲቪዲ ስናወጣ ካልከፈትነው ብለው ወተወቱን። ዲቪዲው እንደተከፈተ ውይይታችን ተቋረጠ፤ እዚያ መኖራችንን የረሱት እስኪመስል ድረስ ዓይናቸው በኮምፒውተሩ ላይ ተተከለ። ባልና ሚስቱ፣ ዲቪዲው ላይ ያዩአቸውን ምልክቶች አልፎ አልፎ ለራሳቸው በመድገም በአድናቆት ስሜት ራሳቸውን ይነቀንቃሉ። እንደምንም ብለን ዲቪዲውን ለጥቂት ጊዜ ካስቆምነው በኋላ ምድር ውብ ገነት እንደምትሆን ወደሚያሳየው መጀመሪያ አካባቢ ወዳለው ምስል ተመለስን። ከዚያም ፊልሙን ቆም አድርገን ወደፊት አምላክ ለሰው ዘር ስለሚያደርገው ነገር እንዲሁም በፊልሙ ላይ በሚታዩት ሁኔታዎች ውስጥ የሚኖሩት ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ተወያየን። ባልና ሚስቱ የነበራቸው ፍላጎት በጣም አበረታታን፤ በውይይታችን መደምደሚያ ላይ ደግሞ በሌላ መንደር ውስጥ ስለሚኖሩና የተወሰኑ ሰዓታት ተጉዘን ልናገኛቸው ስለምንችል መስማት የተሳናቸው ባልና ሚስት ነገሩን።

ከዚያም ጉዟችንን በመቀጠል ተራራውን ሰንጥቆ የሚያልፈውን አስደናቂ የሆነ ጠመዝማዛ መንገድ ይዘን ወደ አንዲት ትንሽ መንደር አቀናን። በዚያም አንድ ቤተሰብ አገኘን፤ እነዚህ ሰዎች፣ ያልተጠበቀ እንግዳ ብንሆንባቸውም በደስታ ተቀበሉን። የቤተሰቡ አባላት ይኸውም ባልና ሚስቱ እንዲሁም ትንሽ ልጃቸውና የሚስትየው እናት መስማት የተሳናቸው ነበሩ። ወደ አይሉ ስንገባ ደስ የሚል የእንጨትና የአሬራ ሽታ አወደን። አይሉ ሾጣጣ በሆነው አናቱ ላይ ብርሃን ለማስገባት የሚረዳ ቀዳዳ አለው። በአንድ ጥግ ኖራ የተቀባ የሸክላ ምድጃ የሚገኝ ሲሆን ግድግዳው ደግሞ ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ስጋጃ ለብሷል። ባልና ሚስቱ የተጠበሱ ትናንሽ ዶናቶችን እና በእስያ ስኒዎች ሻይ አቀረቡልን፤ ይህ ምግብ በአልታይ የተለመደ ነው። እኛም ‘የአምላክ ወዳጅ መሆን ይቻል እንደሆነ አስባችሁ ታውቃላችሁ?’ ብለን ጠየቅናቸው። ለጥያቄው መልስ ለመስጠት ቆም ብለው እያሰቡ ሳለ የሚስትየው እናት፣ ትንሽ ልጅ እያለች በተራሮቹ ላይ ወደሚገኝ ቦታ ምግብ በመውሰድ ለአማልክቱ መሥዋዕት አቅርባ እንደምታውቅ አጫወተችን። “እንደዚያ የሚደረገው ለምን እንደሆነ አላውቅም” ካለችን በኋላ ፈገግ ብላ “ይህ ባሕላችን ነበር” በማለት ተናገረች።

ስለዚህ ጉዳይ የሚናገር ዲቪዲ ስናሳያቸው ፊታቸው በደስታ በራ። ውይይቱን ለመቀጠል ጓጉተው ነበር፤ ይሁንና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እርግጥ ነው፣ በሞባይል አማካኝነት የጽሑፍ መልእክቶችን መለዋወጥ፣ መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር ለመገናኘት የሚረዳ ግሩም ዘዴ ነው፤ ይሁንና በአካባቢው አንድም የሞባይል ስልክ አንቴና ባለመኖሩ እንዲህ ማድረግ አንችልም። በመሆኑም ደብዳቤ ለመጻፍ ቃል ገባንላቸው።

ከእነሱ ጋር ተሰነባብተን ወደ ጎርኖ አልታይስክ ለመጓዝ ረጅሙን መንገድ ስንያያዘው ጀምበሯ ማቆልቆል ጀምራ ነበር፤ ቢደክመንም በጉዟችን በጣም ተደስተናል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ስለዚህ ቤተሰብ ስንጠይቃቸው ባልየው በየአሥራ አምስት ቀኑ ወደ ከተማ እየተጓዘ የምልክት ቋንቋ ከምትችል አንዲት እህት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያጠና እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ እንደሚገኝ ነገሩን። ጥረታችን ለፍሬ በመብቃቱ ምን ያህል እንደተደሰትን ልትገምቱ ትችላላችሁ!

ቅን ልብ ያላቸውን መስማት የተሳናቸው ሰዎች ለመፈለግ ያደረግነው ጥረት በተራሮቹ ውስጥ የተቀበረ ውድ ሀብት ከመፈለግ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ፍለጋው በርካታ ሰዓታት ቢፈጅም በድንገት አንድ ዕንቁ ስናገኝ ጥረታችን እንደተባረከ ሆኖ ይሰማናል። የአልታይ ተራሮች በእነዚያ አስቸጋሪ ኮረብቶች ያገኘናቸውን ልበ ቅን ሰዎች ስለሚያስታውሱን ምንጊዜም ቢሆን ለእኛ ወርቃማ ናቸው።