የመጀመሪያው አመለካከትህ ትክክል ሊሆን ይችላል?
የመጀመሪያው አመለካከትህ ትክክል ሊሆን ይችላል?
አንድ ሐኪም ቤቱ ሆኖ ቴሌቪዥን እየተመለከተ ነው፤ የሚተላለፈው ፕሮግራም ከፍተኛ የአየርላንድ መንግሥት ባለሥልጣን የሆኑ ግለሰብ የተካፈሉበት ውይይት ነበር። ሐኪሙ፣ ባለሥልጣኑን በደንብ ሲመለከታቸው ዕጢ እንዳለባቸው የሚጠቁም ነገር ፊታቸው ላይ አስተዋለ። በመሆኑም ወዲያውኑ ምርመራ እንዲያደርጉ መከራቸው።
የተደረገው ምርመራ ሐኪሙ የተናገረው ነገር ትክክል እንደሆነ አረጋገጠ። ሐኪሙ፣ አንድን ግለሰብ በማየት ብቻ ያለበትን የጤና እክል በትክክል የመለየት ችሎታ ነበረው። አንዳንዶችም ግለሰቦችን በማየት ብቻ ባሕርያቸውን፣ ስብዕናቸውን እንዲሁም እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች መሆን አለመሆናቸውን ማወቅ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል።
ባለፉት ዘመናት ሁሉ ተመራማሪዎች የአንድን ሰው መልክና ቁመና በመመልከት ስለ ግለሰቡ ባሕርይ ማወቅ የሚቻልበትን ሳይንሳዊ ዘዴ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይህንን ዘዴ ፊዚዮግኖሚ ብለው የሚጠሩት ሲሆን ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ይህን ቃል “መልክን ወይም የሰውነትን አቋምና ቅርጽ በማየት የግለሰቦችን ባሕርይ ማወቅ እንደሚቻል የሚገልጽ ሳይንሳዊ መሠረት የሌለው ጽንሰ ሐሳብ” በማለት ይፈታዋል። በ19ኛው መቶ ዘመንም እንዲህ ያለውን ጽንሰ ሐሳብ የደገፉ ምሁራን ነበሩ፤ ከእነዚህም መካከል የቻርለስ ዳርዊን የአክስት ልጅ እንደነበረው ፍራንሲስ ጋልተን ያሉ ስለ ሰው ዘር ባሕል የሚያጠኑ የአንትሮፖሎጂ ምሁራን እና እንደ ጣሊያናዊው ቼዛሬ ሎምብሮሶ ያሉ ስለ ወንጀል የሚያጠኑ ተመራማሪዎች ይገኙበታል። ይሁንና እነዚህ ንድፈ ሐሳቦችና ዘዴዎች በአብዛኛው እየተረሱ መጥተዋል።
ዛሬም ቢሆን ብዙ ሰዎች የአንድን ሰው መልክና ቁመና በመመልከት ብቻ ስለ ማንነቱ ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደሚቻል ያምናሉ። ይሁንና ሰዎችን መጀመሪያ ስናያቸው ስለ እነሱ የሚኖረን አመለካከት ትክክል ሊሆን ይችላል?
መልክን በማየት ሰዎችን መፈረጅ
አንድን ሰው መጀመሪያ ስናየው የሚኖረን አመለካከት የተሳሳተ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። ይሖዋ አምላክ፣ ከእሴይ ቤተሰብ ውስጥ አንዱን የወደፊቱ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባ ነቢዩ ሳሙኤልን አዝዞት ነበር። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ሳሙኤል ኤልያብን አይቶ፣ ‘በእርግጥ እግዚአብሔር የቀባው ሰው እነሆ፤ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞአል’ ብሎ አሰበ። እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ ‘መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል’ አለው።” የተቀሩት የእሴይ ስድስት ልጆች ተራ በተራ ሲቀርቡም ይሖዋ እነሱንም እንዳልመረጣቸው ተናገረ። በመጨረሻ ነቢዩም ሆነ እሴይ ካሰቡት በተቃራኒ አምላክ፣ የወደፊቱ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ስምንተኛውን ልጅ ማለትም ዳዊትን እንደሆነ ገለጸ፤ ዳዊት ትንሽ ልጅ ስለነበር ከቁብ ቆጥሮ የጠራው አልነበረም።—1 ሳሙኤል 16:6-12
በዛሬው ጊዜም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በጀርመን ስለ ወንጀል የሚያጠኑ አንድ ፕሮፌሰር 500 የሕግ ተማሪዎች የተካፈሉበት አንድ ሙከራ ከጥቂት ዓመታት በፊት አካሂደው ነበር። ሙከራውን ለማካሄድ ተማሪዎቹ የማያውቋቸው 12 “እንግዶች” ተጋበዙ። ከእነሱም መካከል የአካባቢው የፖሊስ አዛዥና አቃቤ ሕግ፣ የዩኒቨርሲቲው ገንዘብ ያዥና የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ባለሥልጣን፣ አንዳንድ ጠበቆችና የፍርድ ቤት ባለሥልጣኖች እንዲሁም እስራት የተፈረደባቸው ሦስት ወንጀለኞች ይገኙ ነበር። ተማሪዎቹ በእንግዶቹ መልክና በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያቸው ላይ ብቻ ተመርኩዘው የእያንዳንዱ እንግዳ ሙያ ምን እንደሆነ እንዲሁም ከእንግዶቹ መካከል እስራት የተፈረደባቸው እነማን እንደሆኑና የሠሩት ወንጀል ምን እንደሆነ ማወቅ ይችሉ እንደሆነ ተጠየቁ።
ውጤቱ ምን ሆነ? ከተማሪዎቹ መካከል 75 በመቶ
ገደማ የሚያህሉት ሦስቱን ወንጀለኞች መለየት ችለዋል። ይሁን እንጂ በአማካይ 60 በመቶ የሚያህሉት ተማሪዎች የወንጀል ሪከርድ የሌላቸውን ዘጠኝ እንግዶችም በወንጀለኝነት ፈርጀዋቸዋል። ከ7 ተማሪዎች መካከል አንዱ አቃቤ ሕጉ ዕፅ አዘዋዋሪ እንደሆነ ያሰበ ሲሆን ከ3 ተማሪዎች አንዱ የፖሊስ አዛዡ ሌባ እንደሆነ ተሰምቶታል! ከዚህ እንደምናየው መልክንና ቁመናን በማየት ሰዎችን ከፈረጅን በጣም ልንሳሳት እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?መልክ ሊያሳስት ይችላል
ከአንድ ሰው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስንገናኝ ከዚህ ቀደም ባጋጠመን ነገር ላይ ተመርኩዘን ግለሰቡን ከአንድ ወገን የመፈረጅ አዝማሚያ አለን። እንዲሁም ቀደም ሲል ከምናውቀው ወይም ከሰማነው ነገር ተነስተን ግለሰቡ ላይ መፍረድ ይቀናናል። ከግለሰቡ መልክና ቁመና በተጨማሪ ዜግነቱን፣ ዘሩን፣ ማኅበራዊ ደረጃውን ወይም ሃይማኖቱን በማየት ልንገመግመው እንችላለን።
አንድን ግለሰብ መጀመሪያ ስናየው የሚኖረን አመለካከት ትክክል ከሆነ ራሳችንን ልናደንቅ እንዲሁም ሰዎችን በማየት ማንነታቸውን ማወቅ እንደምንችል ይበልጥ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ ስለ ግለሰቡ የነበረን አመለካከት ፈጽሞ የተሳሳተ እንደሆነ ስንገነዘብ ምን እናደርጋለን? ራሳችንን በሐቀኝነት የምንገመግም ከሆነ ቀደም ሲል የነበረንን መሠረት የሌለው አመለካከት ትተን እውነታውን እንቀበላለን። አለዚያ ግን የሰዎችን ማንነት የማወቅ የላቀ ችሎታ እንዳለን ስለምናስብና በዚህ ችሎታ ስለምንኮራ ሌሎችን ልንጎዳ አልፎ ተርፎም በጣም ልንበድላቸው እንችላለን።
መልክን በማየት የሚፈርድ ሰው፣ ሌሎችን ብቻ ሳይሆን ራሱንም ጭምር ይጎዳል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙ አይሁዳውያን ኢየሱስ ተስፋ የተደረገው መሲሕ ሊሆን እንደሚችል ለማሰብም እንኳ ፈቃደኞች አልነበሩም። ለምን? ስለ ኢየሱስ የነበራቸው አመለካከት የተመረኮዘው በሚያዩት ነገር ላይ ብቻ ስለነበር የአንድ አናጢ ልጅ እንደሆነ ከማሰብ ያለፈ ቦታ ሊሰጡት አልቻሉም። ኢየሱስ በተናገራቸው ጥበብ ያዘሉ ቃላትና በተአምራዊ ሥራዎቹ ቢገረሙም ስለ እሱ የነበራቸውን መሠረተ ቢስ አመለካከት መለወጥ አልፈለጉም። በዚህ አመለካከታቸው የተነሳ ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ ሌሎች ሰዎች ያደረገ ሲሆን “ነቢይ በገዛ አገሩና በገዛ ቤቱ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ሁሉ ይከበራል” ብሏቸዋል።—ማቴዎስ 13:54-58
እነዚያ አይሁዶች መሲሑን ለበርካታ ዘመናት ሲጠብቅ የቆየው ብሔር አባላት ነበሩ። ስለ ኢየሱስ መጀመሪያ በነበራቸው አመለካከት ምክንያት መሲሑን አለመቀበላቸው በመንፈሳዊ ከባድ ኪሳራ አስከትሎባቸዋል። (ማቴዎስ 23:37-39) አይሁዳውያን ስለ ኢየሱስ ተከታዮችም ጭፍን አመለካከት ነበራቸው። የተማረው የማኅበረሰቡ ክፍልና ከፍ ተደርጎ የሚታየው የአይሁድ እምነት መሪዎች የኢየሱስን ተከታዮች ይንቋቸው ስለነበር ብዙ ሰዎች ዝቅተኛ ኑሮ ካላቸው ከእነዚህ ዓሣ አጥማጆች ቁም ነገር ይገኛል ብለው ማሰብ ከብዷቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የአምላክ ልጅ ተከታዮች የመሆን ውድ መብት አጥተዋል።—ዮሐንስ 1:10-12
አንዳንዶች አመለካከታቸውን ለውጠዋል
በኢየሱስ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ትሑት ሰዎች እሱ ያደረጋቸውን ነገሮች ሲያዩ አመለካከታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኞች ሆነዋል። (ዮሐንስ 7:45-52) ከእነዚህ መካከል አንዳንድ የኢየሱስ ቤተሰብ አባላትም ይገኙበታል፤ እነዚህ ሰዎች የቤተሰባቸው አባል የሆነ ሰው መሲሕ ሊሆን እንደሚችል መጀመሪያ ላይ አላሰቡም ነበር። (ዮሐንስ 7:5) የሚያስደስተው ግን ከጊዜ በኋላ አመለካከታቸውን ለውጠው በእሱ አምነዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:14፤ 1 ቆሮንቶስ 9:5፤ ገላትያ 1:19) በተመሳሳይም ከዓመታት በኋላ በሮም የነበሩ አንዳንድ የአይሁድ ማኅበረሰብ ተወካዮች በክርስትና ጠላቶች የተነዛውን አሉባልታ ከማመን ይልቅ ትክክለኛውን ነገር ከሐዋርያው ጳውሎስ አንደበት ለመስማት ፈቃደኞች ሆነዋል። አንዳንዶቹ ጳውሎስን ካዳመጡት በኋላ አማኞች ሆኑ።—የሐዋርያት ሥራ 28:22-24
በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች ስለ የይሖዋ ምሥክሮች አሉታዊ አመለካከት አላቸው። ለምን? በአብዛኛው፣ እውነታውን ስለመረመሩ ወይም የይሖዋ ምሥክሮች የሚያምኑትና የሚያደርጉት ነገር ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ እንደሌለው ስላረጋገጡ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ብዙዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛውን ሃይማኖት ይዘዋል ብሎ ማመን ስለሚከብዳቸው ነው። ይህ ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ብዙዎች ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከነበራቸው አመለካከት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ሳታስተውል አትቀርም።
የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል በሚጥሩ ሰዎች ላይ ጎጂ እና የሚያቃልል ትችት መሰንዘሩ የሚያስገርም አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹን “በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል” በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር። ያም ቢሆን “እስከ መጨረሻው የጸና . . . ይድናል” በማለት አበረታቷቸዋል።—ማቴዎስ 10:22
በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ትእዛዝ በመከተል የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰዎች ለማድረስ ጠንክረው እየሠሩ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) መልእክቱን ለመስማት አሻፈረን የሚሉ ሁሉ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ያመልጣቸዋል። (ዮሐንስ 17:3) አንተስ? ስለ ሰዎች መጀመሪያ ያደረብህ ስሜት ወይም የነበረህ መሠረተ ቢስ አመለካከት ለሌሎች ያለህን ግምት እንዲቀርጹት ትፈቅዳለህ? ወይስ ቀና አስተሳሰብ ይዘህ ሐቁን ለመመርመር ፈቃደኛ ትሆናለህ? መልክ አሳሳች ሊሆንና የመጀመሪያ አመለካከትህ ከእውነታው ሊርቅ እንደሚችል አስታውስ፤ ይሁን እንጂ አስተሳሰብህ ሳይዛባ ሐቁን ብትመረምር ያልጠበቅኸውን አስደሳች ውጤት ልታገኝ ትችላለህ።—የሐዋርያት ሥራ 17:10-12
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ አይሁዶች ስለ ኢየሱስ መጀመሪያ የነበራቸው አመለካከት መሲሕ መሆኑን እንዳይቀበሉ አድርጓቸዋል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ የይሖዋ ምሥክሮች ያለህ አመለካከት የተመሠረተው ስለ እነሱ በሰማኸው ነገር ላይ ነው ወይስ በእውነታው ላይ?