በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

የሥላሴ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለው?

የሥላሴ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለው?

▪ ስለ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት ከተሰጡ በርካታ ፍቺዎች ቢኖሩም አንደኛው እንዲህ ይላል፦ “ሁሉም ዘላለማዊ የሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ሁሉን ማድረግ የሚችሉ፣ አንዳቸው ከአንዳቸው የማይበላለጡ፣ ሁሉም አምላክ የሆኑ ሦስት መለኮታዊ አካላት (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) አሉ። ይሁን እንጂ ሦስቱም አንድ አምላክ ናቸው እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም።” መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ያስተምራል?

ይህን መሠረተ ትምህርት ለመደገፍ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ጥቅስ ማቴዎስ 28:19 ነው። በዚህ ጥቅስ (የ1954 ትርጉም) ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” እውነት ነው፣ በዚህ ጥቅስ ላይ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ ላይ ተጠቅሰዋል። ይሁንና ሦስቱ አንድ ስለመሆናቸው የሚናገር ምንም ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ከላይ ያለውን የተናገረው ሰዎችን እንዲያስተምሩና በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቋቸው ለአይሁዳውያን ተከታዮቹ ተልዕኮ ለመስጠት ነበር። ታዲያ አይሁዳውያን ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን ብለው ያምኑ ነበር?

ለእስራኤል ብሔር በተሰጠውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የሙሴ ሕግ ላይ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” የሚል ትእዛዝ ይገኛል። (ዘዳግም 5:7) እዚህ ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ የተናገሩት አካላት ስንት ናቸው? ዘዳግም 6:4 “እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” በማለት አምላክ፣ አንድም ሦስትም እንዳልሆነ በማያሻማ መንገድ ገልጿል። እስራኤላውያን ይህ ሕግ የተሰጣቸው ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆዩ ነበር፤ በግብፅ ሦስት አማልክትን እንደ አንድ ማምለክ የተለመደ ሲሆን በዚህ መንገድ ከሚመለኩት በርካታ አማልክት መካከል ኦሳይረስ፣ አይስስና ሆረስ (በስተግራ የሚታዩት) ይገኙበታል። እስራኤላውያን ግን አንድ አምላክ ብቻ እንዲያመልኩ ታዝዘዋል። ሕዝቡ ይህንን ትእዛዝ መረዳታቸው ምን ያህል አስፈላጊ ነበር? የአይሁድ ሃይማኖት ረቢ የሆኑት ዶክተር ጆሴፍ ኸርማን ኸርትስ እንዲህ ብለዋል፦ “ስለ አምላክ አንድነት የሚናገረው ይህ ግልጽ መግለጫ በርካታ አማልክትን በሚያመልኩ ሁሉ ላይ ጦርነት የማወጅ ያህል ነበር። . . . የክርስትናው የሥላሴ ትምህርት የአምላክን አንድነት የሚቃወም ስለሆነ [የአይሁዳውያን የእምነት መግለጫ በሆነው] በሺማ ውስጥ አልተካተተም።” *

ኢየሱስ በትውልድ አይሁዳዊ ስለሆነ ይህንን ሕግ እንዲከተል ተምሯል። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ዲያብሎስ በፈተነው ጊዜ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! ‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏልና።” (ማቴዎስ 4:10፤ ዘዳግም 6:13) ከዚህ ዘገባ ቢያንስ ሁለት ነገሮች እንማራለን። አንደኛ ሰይጣን፣ ይሖዋን ሳይሆን ሌላ አካል እንዲያመልክ ኢየሱስን ለማሳመን እየሞከረ ነበር፤ ኢየሱስ የሥላሴ ክፍል ቢሆን ኖሮ ሰይጣን ያቀረበው ይህ ፈተና ምንም ትርጉም አይኖረውም። ሁለተኛ፣ ኢየሱስ “ለእሱም ብቻ” በማለት ሊመለክ የሚገባው አምላክ አንድ ብቻ መሆኑን ግልጽ አድርጓል፤ ኢየሱስ የሥላሴ ክፍል ቢሆን ኖሮ “ለእኛ” ይል ነበር።

ሰዎች ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ሲያገኙና እሱን ለማገልገል ሲፈልጉ “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” ይጠመቃሉ። (ማቴዎስ 28:19) ይህም ሲባል የይሖዋን ሥልጣን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ ያለውን ሚና በሚገባ የተረዱ ከመሆኑም ሌላ አምነውበታል ማለት ነው። (መዝሙር 83:18፤ ማቴዎስ 28:18) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ማለትም በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል ምን እንደሚያከናውን እንደተገነዘቡ ያሳያል።​—ዘፍጥረት 1:2፤ ገላትያ 5:22, 23፤ 2 ጴጥሮስ 1:21

የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ሰዎችን ለዘመናት ግራ ሲያጋባ ቆይቷል። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ለተከታዮቹ እውነቱን በግልጽ ያሳወቃቸው ከመሆኑም ሌላ ‘ብቻውን እውነተኛ አምላክ’ ወደሆነው ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ረድቷቸዋል።​—ዮሐንስ 17:3

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 በ⁠ዘዳግም 6:4 ላይ በተመሠረተው ሺማ በሚባለው ጸሎት ላይ የሚገኘው ስለ አምላክ አንድ መሆን የሚናገረው መግለጫ በአይሁዳውያን ምኩራብ በሚከናወነው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Musée du Louvre, Paris