መልሶቹን ማወቅ ያን ያህል አስፈላጊ ነው?
መልሶቹን ማወቅ ያን ያህል አስፈላጊ ነው?
“እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።”—ዮሐንስ 8:32
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ከሚነገሩ ግራ የሚያጋቡ አልፎ ተርፎም የሚያሳስቱ እምነቶች ነፃ የሚያወጣንን እውነት ይዟል። ይሁንና ስለ ኢየሱስ የምናምነው ነገር ያን ያህል ለውጥ ያመጣል? አዎን፣ ለውጥ ያመጣል። ይሖዋ፣ ስለ ኢየሱስ እውነቱን ማወቃችን አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማዋል። ኢየሱስም ተመሳሳይ አመለካከት አለው። እኛም ብንሆን እውነቱን ማወቃችን አስፈላጊ እንደሆነ ሊሰማን ይገባል።
● ይሖዋ፣ እውነቱን ማወቃችን አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማው ለምንድን ነው? በአጭር አነጋገር “አምላክ ፍቅር” ስለሆነ ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ ደስተኞች ሆነን ለዘላለም እንድንኖር ይፈልጋል። “አምላክ ዓለምን [ይኸውም የሰውን ዘር] እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው . . . ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:16) አምላክ ልጁን የላከው ከኃጢአት እንዲቤዠንና ከመጀመሪያ ዓላማው ጋር በሚስማማ ሁኔታ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር የሚያስችለንን መንገድ እንዲከፍትልን ነው። (ዘፍጥረት 1:28) አምላክ ስለ ልጁ እውነቱን ለሚማሩና ከተማሩት እውነት ጋር ተስማምተው ለሚኖሩት ሰዎች የዘላለም ሕይወት ስጦታን ለመስጠት ዝግጁ ነው።—ሮም 6:23
● ኢየሱስ፣ እውነቱን ማወቃችን አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማው ለምንድን ነው? ኢየሱስም የሰው ልጆችን ይወዳል። ሕይወቱን በፈቃደኝነት ለእኛ አሳልፎ በመስጠት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ዮሐንስ 15:13) ኢየሱስ ይህን ሲያደርግ የሰው ልጆች መዳን ማግኘት የሚችሉበትን ብቸኛ መንገድ እንደከፈተ ያውቃል። (ዮሐንስ 14:6) ታዲያ ኢየሱስ፣ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ከቤዛዊ መሥዋዕቱ እንዲጠቀሙ የሚፈልግ መሆኑ ምን ያስገርማል? በመላው ዓለም ያሉ ሕዝቦችን ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ እንዲያስተምሩ እውነተኛ ተከታዮቹን የላካቸው ለዚህ ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
● እኛስ እውነቱን ማወቃችን አስፈላጊ እንደሆነ ሊሰማን የሚገባው ለምንድን ነው? እንደ ጤንነት እና ቤተሰብ ስላሉ ትልቅ ቦታ የምትሰጣቸው ነገሮች እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ። አንተም ሆንክ የምትወዳቸው ሰዎች ጥሩ ጤንነት እና የተሻለ ሕይወት እንዲኖራችሁ ትፈልጋለህ? ይሖዋ፣ አንተም ሆንክ የምትወዳቸው ሰዎች ሥቃይና መከራ በሌለበት አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጹም ጤንነት ብሎም የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምትችሉበትን አጋጣሚ በኢየሱስ አማካኝነት ከፍቶላችኋል። (መዝሙር 37:11, 29፤ ራእይ 21:3, 4) እንዲህ በመሰለ ዓለም ውስጥ መኖር አያጓጓህም? ከሆነ፣ ልትወስደው የሚገባ እርምጃ አለ።
“እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” የሚለውን ከላይ ያለውን ጥቅስ እስቲ መለስ ብለህ ተመልከተው። ስለ ኢየሱስና በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና የሚገልጸው እውነት ከሁሉም ከከፋው ባርነት፣ ይኸውም ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ሊያወጣን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን ነፃነት ለማግኘት ‘እውነቱን ማወቅ’ ያስፈልግሃል። ታዲያ ስለዚህ እውነት እንዲሁም ይህ እውነት አንተንም ሆነ የምትወዳቸውን ሰዎች እንዴት እንደሚጠቅማችሁ የበለጠ ለማወቅ ለምን አትጥርም? የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።