በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት​—ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው?

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት​—ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው?

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት​—ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ያስደስታቸዋል። አንተስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተያያዘ ግራ የሚያጋባህ ነገር አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር መወያየት ያስደስታቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ሊዲያ የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት እየሄደች ስትሰብክ ሣራ የምትባል ሴት እንዳገኘች አድርገን እናስብ።

የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ አያምኑም የሚባለው እውነት ነው?

ሣራ፦ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ቄስ የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ እንደማያምኑ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እውነት በኢየሱስ አታምኑም?

ሊዲያ፦ በኢየሱስማ እናምናለን። እንዲያውም ለመዳን በኢየሱስ ማመን እንደሚያስፈልግ እንቀበላለን።

ሣራ፦ እኔም የማምነው እንደዚህ ነው።

ሊዲያ፦ እንግዲያው የሚያስማማን ነገር አለ ማለት ነው። ሆኖም ‘የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ የሚያምኑ ከሆነ በኢየሱስ አያምኑም የሚባለው ታዲያ ለምንድን ነው?’ ብለሽ ትጠይቂ ይሆናል።

ሣራ፦ አዎ፣ የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ እፈልጋለሁ።

ሊዲያ፦ ጉዳዩን ጠቅለል አድርጎ ለመግለጽ፣ በኢየሱስ ላይ ጠንካራ እምነት አለን፤ ይህ ሲባል ግን ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን ሁሉ እናምናለን ማለት አይደለም።

ሣራ፦ ምን ማለትሽ ነው?

ሊዲያ፦ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ጥሩ ነገር ሠርቶ ያለፈ ሰው ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እኛ ግን በዚህ ሐሳብ አንስማማም።

ሣራ፦ እኔም ብሆን አልስማማም።

ሊዲያ፦ እንግዲያው ሌላም የሚያስማማን ነጥብ አገኘን ማለት ነው። ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት፦ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ኢየሱስ ከአብ ጋር ስላለው ዝምድና እሱ ራሱ ካስተማረው ነገር ጋር የሚጋጩ ትምህርቶችን አይቀበሉም።

ሣራ፦ ምን ማለትሽ እንደሆነ አልገባኝም።

ሊዲያ፦ ብዙ ሃይማኖቶች ኢየሱስና አባቱ እኩል እንደሆኑ ያስተምራሉ። አንቺም የተማርሽው እንደዚህ ነው?

ሣራ፦ አዎ፣ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ቄስ እግዚአብሔርና ኢየሱስ እኩል እንደሆኑ አስተምረውናል።

ሊዲያ፦ ግን ስለ ኢየሱስ እውነቱን ማወቅ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ እሱ ስለ ራሱ የተናገረውን ነገር መመርመር አይመስልሽም?

ሣራ፦ ይመስለኛል።

ኢየሱስ ምን ብሏል?

ሊዲያ፦ ይህን ጉዳይ ለመረዳት የሚያስችለን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እስቲ እንመልከት። ዮሐንስ 6:38⁠ን ሳነብልሽ ተከታተይኝ። ኢየሱስ “ከሰማይ የመጣሁት የእኔን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው” ብሏል። ኢየሱስ እግዚአብሔር ከሆነ እንዲህ ሊል የሚችል ይመስልሻል?

ሣራ፦ እምም . . . ምን ማለትሽ እንደሆነ አልገባኝም።

ሊዲያ፦ ኢየሱስ ከሰማይ የመጣው የራሱን ፈቃድ ለማድረግ እንዳልሆነ መናገሩን አስተዋልሽ?

ሣራ፦ አዎ፣ የመጣው የላከውን ፈቃድ ለመፈጸም እንደሆነ ተናግሯል።

ሊዲያ፦ ታዲያ ኢየሱስ እግዚአብሔር ከሆነ እሱን ከሰማይ የላከው ማን ነው? ደግሞስ ኢየሱስ ለላኪው ፈቃድ ተገዢ የሆነው ለምንድን ነው?

ሣራ፦ አሃ፣ ምን ማለት እንደፈለግሽ አሁን ገባኝ። ቢሆንም አንድ ጥቅስ ብቻ ኢየሱስ እግዚአብሔር እንዳልሆነ ማስረጃ የሚሆን አይመስለኝም።

ሊዲያ፦ እስቲ በሌላ ወቅት ደግሞ ምን እንዳለ እንመልከት። ቀጥሎ ባለው ምዕራፍ ላይም ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል። ዮሐንስ 7:16⁠ን ታነቢዋለሽ?

ሣራ፦ እሺ፣ “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ‘የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው።’”

ሊዲያ፦ አመሰግናለሁ። በዚህ ጥቅስ መሠረት ኢየሱስ ያስተማረው የራሱን ሐሳብ ነበር?

ሣራ፦ አይ፣ ያስተማረው ትምህርት ከላከው የመጣ እንደሆነ ተናግሯል።

ሊዲያ፦ ልክ ነሽ። እዚህም ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፦ ‘ኢየሱስን የላከው ማን ነው? ያስተማረውን እውነት የተቀበለውስ ከማን ነው?’ ኢየሱስን የላከው አካል ከእሱ የሚበልጥ አይመስልሽም? ደግሞም ላኪ ከተላኪው እንደሚበልጥ የታወቀ ነው።

ሣራ፦ በጣም የሚገርም ሐሳብ ነው። ይህን ጥቅስ ከዚህ በፊት አንብቤው አላውቅም።

ሊዲያ፦ ኢየሱስ በ⁠ዮሐንስ 14:28 ላይ የተናገረውንም እስቲ እንመልከት፤ “እሄዳለሁ ወደ እናንተም ተመልሼ እመጣለሁ እንዳልኳችሁ ሰምታችኋል። የምትወዱኝ ቢሆን ኖሮ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ ምክንያቱም አብ ከእኔ ይበልጣል።” በዚህ ጥቅስ መሠረት፣ ኢየሱስ አባቱን እንዴት አድርጎ የሚመለከተው ይመስልሻል?

ሣራ፦ እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ አብ ከእሱ እንደሚበልጥ ተናግሯል። ስለዚህ ኢየሱስ፣ እግዚአብሔርን የበላዩ እንደሆነ አድርጎ የሚመለከተው ይመስለኛል።

ሊዲያ፦ ትክክል ነሽ። ሌላ ምሳሌ ለመጨመር ያህል፣ በ⁠ማቴዎስ 28:18 ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ምን እንዳላቸው ልብ በይ፤ ጥቅሱ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ይላል። እዚህ ላይ ኢየሱስ ከበፊቱም “ሥልጣን ሁሉ” እንደነበረው ተናግሯል?

ሣራ፦ አይ፣ ሥልጣን እንደተሰጠው ነው የተናገረው።

ሊዲያ፦ ታዲያ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ከሆነ እንዴት ተጨማሪ ሥልጣን ሊቀበል ይችላል? ደግሞስ ሥልጣን የሰጠው ማን ነው?

ሣራ፦ እኔ እንጃ! ይሄ ለእኔ አዲስ ሐሳብ ነው።

ኢየሱስ የጸለየው ወደ ማን ነበር?

ሊዲያ፦ አንዳንዶች እንደሚሉት ኢየሱስ፣ በእርግጥ ሁሉን ቻይ አምላክ ከሆነ ሌላም ግራ የሚያጋባ ነገር ይኖራል።

ሣራ፦ ምን?

ሊዲያ፦ ስለ ኢየሱስ ጥምቀት በሚናገረው ጥቅስ ላይ የምናገኘው ሐሳብ ግራ የሚያጋባ ይሆናል። በ⁠ሉቃስ 3:21, 22 ላይ ያለውን ይህን ዘገባ እስቲ እንመልከት፤ ጥቅሱን ታነቢዋለሽ?

ሣራ፦ “ሕዝቡም ሁሉ በሚጠመቁበት ጊዜ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ እየጸለየም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም አካላዊ ቅርጽ ይዞ በርግብ መልክ በእሱ ላይ ወረደ፤ ከዚያም ‘አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል’ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።”

ሊዲያ፦ ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ ምን እንዳደረገ አስተዋልሽ?

ሣራ፦ እየጸለየ ነበር።

ሊዲያ፦ ታዲያ ኢየሱስ እግዚአብሔር ከሆነ ወደ ማን ነው የጸለየው?

ሣራ፦ ጥሩ ጥያቄ ነው። ቤተ ክርስቲያን ስሄድ እጠይቃለሁ።

ሊዲያ፦ እዚሁ ጥቅስ ላይ ሌላም ጥያቄ ይነሳል፤ ኢየሱስ ከውኃው ሲወጣ ከሰማይ ሆኖ የተናገረ አካል ነበረ። ይህ አካል ምን ብሎ እንደተናገረ ልብ ብለሻል?

ሣራ፦ አዎ፣ ኢየሱስ ልጁ እንደሆነ፣ እንደሚወደውና በእሱ ደስ እንደሚሰኝ ተናግሯል።

ሊዲያ፦ ልክ ነሽ። ይሁንና ኢየሱስ እግዚአብሔር ከሆነ ከሰማይ ሆኖ የተናገረው ማን ነው?

ሣራ፦ በዚህ መልኩ አስቤው አላውቅም።

“አባት” እና “ልጅ” የተባሉት ለምንድን ነው?

ሊዲያ፦ ሌላም ሊታሰብበት የሚገባ ነገር አለ፦ ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር ሲናገር በሰማይ ያለ አባቱ መሆኑን ገልጿል። ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ከሰማይ የመጣው ድምፅም ኢየሱስ፣ ‘ልጁ’ እንደሆነ ተናግሯል። እንዲያውም ኢየሱስ ስለ ራሱ ሲናገር የአምላክ ልጅ እንደሆነ ገልጿል። እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅሽ፦ በቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን ዝምድና እንደ ምሳሌ ተጠቅመሽ ሁለት ሰዎች እኩል መሆናቸውን ልታስተምሪኝ ብትፈልጊ አባትና ልጅ እንደሆኑ ትናገሪያለሽ?

ሣራ፦ አይ፣ ምናልባት ሁለት ወንድማማቾችን ምሳሌ አድርጌ እጠቀም ይሆናል።

ሊዲያ፦ ልክ ነሽ፣ ምናልባትም አንድ ዓይነት የሆኑ መንትያዎችን በምሳሌነት ትጠቅሺ ይሆናል። ኢየሱስ ግን እግዚአብሔር አባቱ እንደሆነና እሱ ደግሞ ልጅ እንደሆነ ተናግሯል። ታዲያ ኢየሱስ ለማስተላለፍ የፈለገው ነጥብ ምን ይመስልሻል?

ሣራ፦ ልትይ የፈለግሽው አሁን ገብቶኛል። ‘ኢየሱስ፣ አንደኛው አካል ከሌላው በዕድሜና በሥልጣን እንደሚበልጥ መግለጹ ነው’ እያልሽኝ ነው አይደል?

ሊዲያ፦ አዎ! እስቲ አስቢው፦ ሁለት ግለሰቦች እኩል መሆናቸውን በምሳሌ ለማስረዳት ወንድማማቾችን ወይም መንትያዎችን ተጠቅመሻል። ታዲያ ታላቅ አስተማሪ የነበረው ኢየሱስ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል ቢሆን ኖሮ ይህን ለማስረዳት ተመሳሳይ ምሳሌ አይጠቀምም ነበር? እንዲያውም ከዚህ የተሻለ ምሳሌ ማቅረብ የሚችል አይመስልሽም?

ሣራ፦ አዎ፣ ይመስለኛል!

ሊዲያ፦ ኢየሱስ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ዝምድና ለመግለጽ የተጠቀመው “አባት” እና “ልጅ” በሚሉት ቃላት ነው።

ሣራ፦ የሚገርም ነጥብ ነው።

የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች ምን ብለዋል?

ሊዲያ፦ ከመለያየታችን በፊት ጥቂት ደቂቃዎች ካሉሽ ከዚህ ርዕስ ጋር በተያያዘ አንድ ሌላ ነጥብ ብጠቅስልሽ ደስ ይለኛል።

ሣራ፦ ይቻላል።

ሊዲያ፦ ኢየሱስ በእርግጥ ሁሉን ቻይ አምላክ ከሆነ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህንን በግልጽ የሚናገሩ አይመስልሽም?

ሣራ፦ ይመስለኛል።

ሊዲያ፦ ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብለው እንዳስተማሩ የሚናገር ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። እንዲያውም ከመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች አንዱ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን እንመልከት። በ⁠ፊልጵስዩስ 2:9 ላይ ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ አምላክ ምን እንዳደረገለት ጳውሎስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ [ለኢየሱስ] የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው።” በዚህ ጥቅስ መሠረት አምላክ ለኢየሱስ ምን አደረገለት?

ሣራ፦ አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አድርጎታል።

ሊዲያ፦ አዎ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከአምላክ ጋር እኩል ከነበረና ከሞት ከተነሳ በኋላ አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ ካደረገው ኢየሱስ ከአምላክ ሊበልጥ ነው ማለት ነው? ከእግዚአብሔር የሚበልጥ አካል ያለ ይመስልሻል?

ሣራ፦ አይ፣ እንደዚያማ ሊሆን አይችልም።

ሊዲያ፦ ትክክል ነሽ። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ማስረጃ አንጻር፣ ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሆነ የሚገልጸው ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ይመስልሻል?

ሣራ፦ እምም . . . እንደዚያ ለማለት ይከብዳል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ነው።

ሊዲያ፦ ልክ ነሽ። ይህ ሲባል ግን ሣራ፣ እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስን አናከብረውም ማለት አይደለም፤ እንዲያውም ትልቅ ቦታ እንሰጠዋለን። ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ በመሆን መሞቱ ታማኝ የሆኑ የሰው ዘሮች በሙሉ መዳን የሚያገኙበት መንገድ እንደከፈተ እናምናለን።

ሣራ፦ እኔም ይህን አምናለሁ።

ሊዲያ፦ ከሆነ ‘ኢየሱስ ስለ እኛ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ላደረገልን ነገር አድናቆታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?’ * የሚል ጥያቄ ይፈጠርብሽ ይሆናል።

ሣራ፦ አዎ፣ ይህ ጉዳይ እኔንም ያሳስበኛል።

ሊዲያ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ሌላ ጊዜ መጥቼ ብንወያይ ደስ ይለኛል። በሚቀጥለው ሳምንት በዚሁ ሰዓት ቤትሽ ብመጣ ይመችሻል?

ሣራ፦ አዎ፣ እኖራለሁ።

ሊዲያ፦ በጣም ጥሩ፤ እንግዲያው ሳምንት እንገናኝ።

[የግርጌ ማስታወሻ]