በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ አምላክ ቅረብ

“እባክህ ወደ ቤትህ መልሰን”

“እባክህ ወደ ቤትህ መልሰን”

በአንድ ወቅት ይሖዋን ታገለግል ነበር? ወደ ይሖዋ ለመመለስ ብታስብም ‘እንደገና ይቀበለኝ ይሆን’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦሃል? ከሆነ ይህንን እና ቀጣዩን ርዕስ በትኩረት እንድታነብብ እንጋብዝሃለን። እነዚህ ርዕሶች አንተን ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው።

“ይሖዋ፣ ወደ ቤቱ እንዲመልሰኝና የበደልኩትን ይቅር እንዲለኝ በጸሎት እለምነው ነበር።” ይህን የተናገረችው በእውነት ቤት ብታድግም ይሖዋን ማገልገል አቁማ የነበረች አንዲት ሴት ናት። ይህች ሴት በጣም እንደምታሳዝንህ ጥርጥር የለውም። ‘አምላክ በአንድ ወቅት ያገለግሉት ስለነበሩ ሰዎች ምን ይሰማዋል? እነዚህን ሰዎች ያስታውሳቸዋል? ወደ ቤቱ እንዲመለሱስ ይፈልጋል?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቀህ ታውቃለህ? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ኤርምያስ ያሰፈረውን ሐሳብ እስቲ እንመርምር። መልሱ ልብህን በጥልቅ እንደሚነካው ጥርጥር የለውም።​—ኤርምያስ 31:18-20ን አንብብ።

ኤርምያስ ይህን ሐሳብ ሲጽፍ የነበረውን ሁኔታ እስቲ እንመልከት። ኤርምያስ ከኖረበት ዘመን ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት ማለትም በ740 ዓ.ዓ. ይሖዋ አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት በአሦራውያን በግዞት እንዲወሰድ ፈቅዶ ነበር። * ይሖዋ፣ ሕዝቡ በዚህ መንገድ እንዲቀጡ የፈቀደው በነቢያቱ በኩል በተደጋጋሚ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት አስጸያፊ ኃጢአቶችን ይፈጽሙ ስለነበር ነው። (2 ነገሥት 17:5-18) ሕዝቡ ከአምላካቸው ጋር መቆራረጣቸውና ከትውልድ አገራቸው ርቀው በግዞት በተወሰዱበት ቦታ የደረሰባቸው መከራ አመለካከታቸውን ቀይሮት ይሆን? ይሖዋስ ጨርሶ ረስቷቸው ይሆን? ወደ ቤቱ ይመልሳቸው ይሆን?

“ተጸጸትሁ”

ሕዝቡ በግዞት ተወስደው ሳሉ ወደ ልቡናቸው በመመለስ ንስሐ ለመግባት ተነሳሱ። ይሖዋም እውነተኛ የንስሐ ዝንባሌ እንዳሳዩ ማስተዋሉ አልቀረም። በቡድን ደረጃ ኤፍሬም ተብለው የተጠሩት በግዞት የተወሰዱት እስራኤላውያን የነበራቸውን አመለካከትና ስሜት ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል።

“የኤፍሬምን የሲቃ እንጕርጕሮ በእርግጥ ሰምቻለሁ” በማለት ይሖዋ ተናግሯል። (ቁጥር 18) እስራኤላውያን ኃጢአታቸው ባስከተለባቸው መጥፎ ውጤት የተነሳ የተሰማቸውን ሐዘን ሲገልጹ ሰምቷቸዋል። “የሲቃ እንጕርጕሮ” የሚለው ሐረግ “መነቅነቅን ወይም ማወዛወዝን” ሊያመለክት እንደሚችል አንድ ምሁር ተናግረዋል። ዓመፀኛ በመሆኑ ምክንያት የደረሰበትን መከራ ሲያስብና በአባቱ ቤት የነበረውን ጥሩ ሕይወት ሲያስታውስ በቁጭት ራሱን እንደሚነቀንቅ ልጅ ሁሉ እስራኤላውያንም በድርጊታቸው ተቆጭተው ነበር። (ሉቃስ 15:11-17) ሕዝቡ ስሜታቸውን የገለጹት እንዴት ነበር?

“እንዳልተገራ ወይፈን ቀጣኸኝ።” (ቁጥር 18) ሕዝቡ ቅጣት ይገባቸው እንደነበር አምነዋል። ደግሞም እንዳልተገራ ወይፈን ሆነው ነበር። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው፣ ይህ አነጻጻሪ ዘይቤ እስራኤላውያን “መጀመሪያውኑ ቀንበሩን አልሸከምም ብሎ ባያምፅ ኖሮ በበሬ መንጃ ዘንግ መወጋት እንደማያስፈልገው ወይፈን” ሆነው እንደነበር ሊያመለክት ይችላል።

“አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና፣ መልሰኝ፤ እኔም እመለሳለሁ።” (ቁጥር 18) እስራኤላውያን ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ አምላክ ጮኸዋል። ከይሖዋ ርቀው በኃጢአት ጎዳና ይመላለሱ ነበር፤ አሁን ግን ወደ እሱ ለመመለስ እንዲረዳቸው እየለመኑት ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “አንተ አምላካችን ነህ። እባክህ ወደ ቤትህ መልሰን” በማለት አስቀምጦታል።​—ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን

“ተጸጸትሁ፤ . . . ዐፈርሁ፤ ቀለልሁም።” (ቁጥር 19) ሕዝቡ ኃጢአት በመሥራታቸው አዝነው ነበር። ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነው ተቀብለዋል። እንዲሁም አፍረውና ተሸማቀው ነበር፤ ሕዝቡ በጸጸት ደረታቸውን የሚመቱ ያህል ነበር።​—ሉቃስ 15:18, 19, 21

እስራኤላውያን ንስሐ እንደገቡ በግልጽ ማየት ይቻላል። በሠሩት ኃጢአት ከልባቸው ተጸጽተዋል፣ ኃጢአታቸውን ለአምላክ ተናዝዘዋል፤ እንዲሁም ከመጥፎ አካሄዳቸው ተመልሰዋል። እስራኤላውያን ንስሐ መግባታቸው የይሖዋን ልብ ያራራው ይሆን? ወደ ቤቱ እንዲመለሱስ ይፈቅድላቸው ይሆን?

“በታላቅ ርኅራኄም እራራለታለሁ”

ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር ልዩ ዝምድና ነበረው። “እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፣ ኤፍሬም በኵር ልጄ ነው” በማለት ተናግሯል። (ኤርምያስ 31:9) አንድ አፍቃሪ አባት፣ ልጁ ከልቡ ተጸጽቶ ቢመለስ እሱን ለመቀበል እምቢ ሊል ይችላል? ይሖዋም ለሕዝቡ ያለውን አባታዊ ፍቅር እንዴት እንደገለጸ ልብ በል።

“ኤፍሬም የምወደው፣ ደስም የምሰኝበት ልጄ አይደለምን? ብዙ ጊዜ ተቃውሜው ብናገርም፣ መልሼ ስለ እርሱ አስባለሁ።” (ቁጥር 20) ይህ ምንኛ ልብ የሚነካ አነጋገር ነው! ጥብቅ ሆኖም አፍቃሪ እንደሆነ አባት፣ አምላክ ከኃጢአታቸው እንዲመለሱ ልጆቹን በተደጋጋሚ በማስጠንቀቅ እነሱን ‘ተቃውሞ’ ለመናገር ተገድዶ ነበር። ልጆቹ እሱን ለመስማት አሻፈረን በማለታቸው በግዞት እንዲወሰዱ ሲፈቅድም ከቤቱ እንዲወጡ ያደረገ ያህል ነበር። ሆኖም አምላክ በዚህ መልኩ ቢቀጣቸውም ሕዝቡን አልረሳቸውም። ይህን ፈጽሞ ሊያደርግ አይችልም። አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹን አይረሳም። ታዲያ ይሖዋ ልጆቹ ከልባቸው ንስሐ እንደገቡ ሲመለከት ምን ተሰማው?

“አንጀቴ ይላወሳል፤ * በታላቅ ርኅራኄም እራራለታለሁ።” (ቁጥር 20) ይሖዋ ልጆቹ እንዲመለሱ በጣም ይናፍቅ ነበር። እውነተኛ የንስሐ ዝንባሌ ማሳየታቸው ልቡን ነክቶታል፤ እንዲሁም ወደ እሱ የሚመለሱበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው የአባካኙ ልጅ አባት፣ ይሖዋም ስለ ልጆቹ ሲያስብ ‘አንጀቱ የሚላወስ’ ከመሆኑም ሌላ እነሱን ለመቀበል ይጓጓል።​—ሉቃስ 15:20

‘ይሖዋ ወደ ቤቱ መለሰኝ!’

በ⁠ኤርምያስ 31:18-20 ላይ የሚገኙት ቃላት ይሖዋ የሚያሳየውን ከልብ የመነጨ ርኅራኄና ምሕረት በጥልቀት እንድናስተውል ረድተውናል። አምላክ በአንድ ወቅት ያገለግሉት የነበሩ ሰዎችን አይረሳም። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ወደ እሱ ለመመለስ ቢፈልጉስ? አምላክ “ይቅር ባይ” ነው። (መዝሙር 86:5) ከልብ ተጸጽተው ወደ እሱ የሚመለሱ ሰዎችን ፈጽሞ ችላ አይልም። (መዝሙር 51:17) እንዲያውም እነዚህ ሰዎች ወደ ቤቱ ሲመለሱ በደስታ ይቀበላቸዋል።​—ሉቃስ 15:22-24

በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችው ሴት ወደ ይሖዋ ለመመለስ ስለፈለገች በአካባቢዋ ወደሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ሄደች። እርግጥ ነው፣ መጀመሪያ ላይ ወደ አእምሮዋ የሚመጡትን አፍራሽ ስሜቶች መቋቋም ነበረባት። ወደ ይሖዋ ቤት መመለስ የማይገባት ሰው እንደሆነች ይሰማት ነበር። ሆኖም የጉባኤው ሽማግሌዎች ያበረታቷት ከመሆኑም ሌላ እንደገና በመንፈሳዊ እንድትጠነክር ረዷት። ይህች ሴት “ይሖዋ ወደ ቤቱ ስለመለሰኝ በጣም ደስተኛ ነኝ!” በማለት በአድናቆት ተናግራለች።

በአንድ ወቅት ይሖዋን ታገለግል ከነበረና አሁን ወደ እሱ ተመልሰህ ልታገለግለው የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ እንድትሄድ እናበረታታሃለን። ይሖዋ “እባክህ ወደ ቤትህ መልሰን” በማለት ለሚለምኑት ንስሐ የገቡ ሰዎች ርኅራኄ እና ምሕረት እንደሚያሳያቸው አስታውስ።

በሚያዝያ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ኤርምያስ 17 እስከ 31

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ይህ ከመሆኑ ከጥቂት መቶ ዓመታት በፊት ይኸውም በ997 ዓ.ዓ. የእስራኤል ሕዝብ ተከፍሎ በሁለት መንግሥታት መተዳደር ጀምሮ ነበር። በስተደቡብ የሚገኘውና ሁለቱን ነገድ ያቀፈው መስተዳድር የይሁዳ መንግሥት ይባላል። በስተሰሜን የሚገኘውና አሥሩን ነገድ ያቀፈው መስተዳድር ደግሞ የእስራኤል መንግሥት ይባላል፤ ይህ መንግሥት ኤፍሬም በሚባለው በዋነኛው ነገድ ስምም ይጠራል።

^ አን.16 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መመሪያ ጽሑፍ ስለ አንጀት መላወስ የሚገልጸውን ሐሳብ በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “አይሁዳውያን ስሜታቸውን ለመግለጽ ውስጣዊ የአካላቸውን ክፍሎች ይጠቅሳሉ።”