የአዋልድ ወንጌሎች—ስለ ኢየሱስ የተሰወሩ እውነቶችን ይዘዋል?
የአዋልድ ወንጌሎች—ስለ ኢየሱስ የተሰወሩ እውነቶችን ይዘዋል?
“ይህ ትልቅ ግኝት ነው። በጣም ብዙ ሰዎችን ማስቆጣቱ አይቀርም።” “ስለ ጥንቱ ክርስትና ያለንን ግንዛቤ ይለውጠዋል።” እነዚህን አስገራሚ አስተያየቶች የሰጡት ለ16 ምዕተ ዓመታት ያህል ጠፍቶ እንደነበረ የሚታሰበው “የይሁዳ ወንጌል” (ከላይ ያለው) በመገኘቱ የተደሰቱ ምሁራን ናቸው።
እንደነዚህ ያሉት የአፖክሪፋ ወይም የአዋልድ ወንጌሎች አሁን አሁን የሰዎችን ትኩረት እየሳቡ ነው። አንዳንድ ሰዎች እነዚህ ጽሑፎች ለረጅም ዓመታት ተሰውረው የኖሩ የኢየሱስ ትምህርቶችንና በሕይወቱ ውስጥ የተፈጸሙ ታላላቅ ክንውኖችን እንደሚገልጡ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የአዋልድ ወንጌሎች ምንድን ናቸው? ስለ ኢየሱስ እና ስለ ክርስትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልናገኛቸው የማንችላቸውን እውነቶች ሊያስተምሩን ይችላሉ?
ትክክለኛ ወንጌሎችና የአዋልድ ወንጌሎች
ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ከ41 እስከ 98 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ ‘የኢየሱስ ክርስቶስን ታሪክ’ ጽፈዋል። (ማቴዎስ 1:1) እነዚህ ዘገባዎች አንዳንድ ጊዜ ወንጌሎች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን የቃሉ ትርጉም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጽ “ምሥራች” ማለት ነው።—ማርቆስ 1:1
ስለ ኢየሱስ የሚገልጹ ትውፊቶችና ሌሎች ጽሑፎች ሊኖሩ ቢችሉም በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፉና የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል እንደሆኑ ተደርገው የተቆጠሩት እነዚህ አራት ወንጌሎች ብቻ ናቸው፤ እነዚህ ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወትና ትምህርት “እርግጠኛ” የሆነ ዘገባ ይዘዋል። (ሉቃስ 1:1-4፤ የሐዋርያት ሥራ 1:1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እነዚህ አራት ወንጌሎች በሁሉም ጥንታዊ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል። በአምላክ መንፈስ መሪነት ከተጻፉት መጻሕፍት መካከል መሆናቸውን እንድንጠራጠር የሚያደርገን ምንም ምክንያት የለም።
ከጊዜ በኋላ ግን ሌሎች ጽሑፎችም ብቅ ያሉ ሲሆን እነሱም ወንጌሎች ተብለው መጠራት ጀመሩ። እነዚህ ሌሎች ወንጌሎች አፖክሪፋ * ወይም አዋልድ ተብለው ተሰየሙ።
በሁለተኛው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ላይ የልዮኑ ኢራንየስ እንደጻፈው ክርስትናን የካዱ ሰዎች፣ “ሞኞችን ለማደናገር ራሳቸው የፈጠሯቸውን” ወንጌሎች ጨምሮ “ለቁጥር የሚያታክቱ የሐሰትና የአዋልድ ጽሑፎች” አዘጋጅተው ነበር። በመሆኑም የአዋልድ ወንጌሎችን ማንበብ ቀርቶ ይዞ መገኘት እንኳ አደገኛ እንደሆነ ይታሰብ ነበር።
ይሁን እንጂ በመካከለኛው ዘመን የኖሩ መነኮሳትና ገልባጮች እነዚህ የጽሑፍ ሥራዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ አድርገዋል። በ19ኛው መቶ ዘመን እነዚህ መጻሕፍት የበለጠ ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን ምሁራን ሂስ የሰጡባቸውን የአዋልድ ጽሑፎች ጨምሮ ብዙ ወንጌሎች ተገኙ። በዛሬው ጊዜ እነዚህ ጽሑፎች በብዛት በሚሠራባቸው ዘመናዊ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል።
የአዋልድ ወንጌሎች—ስለ ኢየሱስ የሚገልጹ ከእውነታው የራቁ ዘገባዎች
አብዛኛውን ጊዜ የአዋልድ ወንጌሎች የሚያተኩሩት በትክክለኛዎቹ ወንጌሎች ውስጥ ብዙም ባልተጻፈላቸው ወይም ከነጭራሹ ባልተጠቀሱ ሰዎች ላይ ነው። አሊያም ደግሞ ኢየሱስ ሕፃን ሳለ የተፈጸሙ እንደሆኑ ስለሚነገርላቸው ክንውኖች ይዘግባሉ። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦
▪ “የማርያም ልደት” ተብሎም የሚጠራው “የመጀመሪያው የያዕቆብ ወንጌል” ስለ ማርያም ልደትና ስለ ልጅነት ሕይወቷ እንዲሁም ዮሴፍን ስለ ማግባቷ ይገልጻል። ይህ ጽሑፍ ሃይማኖታዊ ልብ ወለድ ወይም አፈ ታሪክ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹ በእርግጥም የተገባ ነው። ማርያም ምንጊዜም ድንግል እንደነበረች የሚያስተምር ሲሆን የተጻፈበት ዓላማ ለእሷ ትልቅ ክብር መስጠት እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል።—ማቴዎስ 1:24, 25፤ 13:55, 56
▪ “የቶማስ ወንጌል” በኢየሱስ የልጅነት ሕይወት (ከ5 እስከ 12 ዓመት) ላይ የሚያተኩር ሲሆን ኢየሱስ ለማመን የሚያዳግቱ ተአምራትን እንደፈጸመ ያወሳል። (ዮሐንስ 2:11ን ተመልከት።) በዚህ ጽሑፍ ላይ ኢየሱስ ተንኮለኛ፣ ግልፍተኛና ቂመኛ ልጅ እንደነበረ ብሎም ተአምር የመፈጸም ችሎታውን አስተማሪዎችን፣ ጎረቤቶችንና ሌሎች ልጆችን ለመበቀል ይጠቀምበት እንደነበር ተዘግቧል፤ ኢየሱስ አንዳንዶችን እንዳሳወረና ሽባ እንዳደረገ አልፎ ተርፎም እንደገደለ መጽሐፉ ይተርካል።
▪ “የጴጥሮስ ወንጌል” እና የመሳሰሉት አንዳንድ የአዋልድ ወንጌሎች በኢየሱስ የፍርድ ሂደት እንዲሁም በሞቱና በትንሣኤው ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው። እንደ “ግብረ ጲላጦስ” (“የኒቆዲሞስ ወንጌል” ላይ የሚገኝ ነው) ያሉት ሌሎቹ ወንጌሎች ደግሞ ከእነዚህ ክንውኖች ጋር ግንኙነት ስለነበራቸው ሰዎች ይተርካሉ። በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱት ክንውኖችም ሆኑ ሰዎች በምናብ የተፈጠሩ እንጂ እውነተኛ ስላልሆኑ በመጻሕፍቱ ላይ እምነት መጣል አይቻልም። “የጴጥሮስ ወንጌል” ጳንጥዮስ ጲላጦስን ከጥፋተኝነት ነፃ ለማድረግ የታሰቡ ነጥቦችን የሚያቀርብ ሲሆን የኢየሱስን ትንሣኤ ደግሞ ፈጽሞ እውነት በማይመስል መንገድ ይተርከዋል።
የአዋልድ ወንጌሎችና ክህደት
ታኅሣሥ 1945፣ ገበሬዎች በላይኛው ግብጽ በሚገኘው በናግ ሃማዲ አጠገብ 52 ጽሑፎችን የያዙ 13 የፓፒረስ ጥንታዊ ቅጂዎችን በአጋጣሚ አገኙ። በአራተኛው ምዕተ ዓመት እንደተዘጋጁ የሚታሰቡት እነዚህ ሰነዶች ግኖስቲሲዝም ተብሎ በሚጠራው ሃይማኖትንና ፍልስፍናን ያጣመረ እንቅስቃሴ አባላት እንደተጻፉ ይታመናል። አረማዊ እምነትን፣ የግሪክ ፍልስፍናን፣ የአይሁድ እምነትንና ክርስትናን የሚቀላቅለው እንዲሁም ከመለኮታዊ አካል ጋር በቀጥታ ግንኙነት ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት ላይ ያተኮረው ይህ እንቅስቃሴ በአንዳንድ ክርስቲያን ነን ባዮች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21
በናግ ሃማዲ አቅራቢያ በተገኙት ጥንታዊ ቅጂዎች ውስጥ ያሉት “የቶማስ ወንጌል፣” “የፊልጶስ ወንጌል” እና “የእውነት ወንጌል” የተለያዩ ግኖስቲካዊ አስተሳሰቦችን ኢየሱስ እንደተናገራቸው አድርገው ይገልጻሉ። በቅርብ የተገኘው “የይሁዳ ወንጌል” የተባለው ጽሑፍም ከግኖስቲክ ወንጌሎች አንዱ እንደሆነ ይቆጠራል። ይህ ጽሑፍ ኢየሱስን በትክክል የተረዳው ብቸኛው ሐዋርያ የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደሆነ በመግለጽ ይሁዳን ጥሩ ሰው እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል። በዚህ ወንጌል ላይ ጥናት ያካሄዱ አንድ ባለሞያ እንደተናገሩት በወንጌሉ ላይ ኢየሱስ የተገለጸው “ለዓለም ኃጢአት የሞተ አዳኝ ሳይሆን ጥበብንና እውቀትን የገለጸ መምህር” እንደሆነ ተደርጎ ነው። በሌላ በኩል ግን በአምላክ መንፈስ የተጻፉት ወንጌሎች ኢየሱስ ለዓለም ኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ እንደሞተ ይገልጻሉ። (ማቴዎስ 20:28፤ 26:28፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የግኖስቲክ ወንጌሎች ዓላማ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት ማጠናከር ሳይሆን ማዳከም ነው።—የሐዋርያት ሥራ 20:30
ትክክለኛዎቹ ወንጌሎች ያላቸው ብልጫ
የአዋልድ ወንጌሎችን ጠለቅ ብሎ በመመርመር እውነተኛ ገጽታቸውን ማወቅ ይቻላል። ከትክክለኛዎቹ ወንጌሎች ጋር ስናነጻጽራቸው በአምላክ መንፈስ መሪነት እንዳልተጻፉ በግልጽ ማየት እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 1:13) ኢየሱስንና ሐዋርያቱን ጨርሶ በማያውቁ ሰዎች የተጻፉ በመሆናቸው ስለ ኢየሱስም ሆነ ስለ ክርስትና የሚገልጹት አንድም የተሰወረ እውነት የለም። እንዲያውም በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሠረቱና ከእውነታው የራቁ የፈጠራ ታሪኮችን የያዙ በመሆናቸው ስለ ኢየሱስም ሆነ ስለ ትምህርቶቹ ለማወቅ ሊረዱን አይችሉም።—1 ጢሞቴዎስ 4:1, 2
በሌላ በኩል ግን ማቴዎስና ዮሐንስ ከኢየሱስ 12 ሐዋርያት መካከል ናቸው፤ ማርቆስ ከጴጥሮስ ጋር ይቀራረብ የነበረ ሲሆን ሉቃስ ደግሞ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ተጉዟል። ወንጌሎቻቸውን የጻፉት በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መሪነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:14-17) በመሆኑም አራቱ ወንጌሎች “ኢየሱስ፣ እሱ በእርግጥ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ” መሆኑን ለማመን የሚያስፈልጉትን መረጃዎች በሙሉ ይዘዋል።—ዮሐንስ 20:31
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 “አፖክሪፋ” የሚለው ቃል የመጣው “መሰወር” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል ነው። ቃሉ በመጀመሪያ ያመለክት የነበረው ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ላቀፈ አንድ ቡድን አባላት ብቻ የተዘጋጀ ጽሑፍን ሲሆን የዚህ ቡድን አባል ላልሆኑ ሰዎች ጽሑፉ የተሰወረ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይህ ቃል፣ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፉ ተቀባይነት ባገኙት የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ ጽሑፎችን ያመለክት ጀመር።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Kenneth Garrett/National Geographic Stock