ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
የመተማመን ስሜትን እንደገና ማጎልበት
ስቲቭ *፦ “ጆዲ ምንዝር ትፈጽማለች ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም። ከዚያ በኋላ በእሷ ላይ የነበረኝ እምነት ጨርሶ ጠፋ። ጆዲን ይቅር ማለት ምን ያህል ከብዶኝ እንደነበር በቃላት መግለጽ ያስቸግረኛል።”
ጆዲ፦ “ስቲቭ እኔን ማመን የከበደው ለምን እንደሆነ ይገባኛል። በጥፋቴ ምን ያህል እንደተጸጸትኩ እንዲያውቅልኝ ለማድረግ ብዙ ዓመታት ፈጅቶብኛል።”
መጽሐፍ ቅዱስ የትዳር ጓደኛቸው ምንዝር የፈጸመባቸው ሰዎች ለመፋታት ወይም አብረው ለመኖር ሊወስኑ እንደሚችሉ ይናገራል። * (ማቴዎስ 19:9) ከላይ የተጠቀሰው ስቲቭ ከሚስቱ ጋር ላለመፋታት ወሰነ። እሱም ሆነ ጆዲ ትዳራቸውን ለመታደግ ቆርጠው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ይህን ማድረግ እንዲሁ አብረው መኖራቸውን ከመቀጠል ያለፈ ነገር እንደሚጠይቅ ተገነዘቡ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ከላይ ከሰጡት አስተያየት መረዳት እንደሚቻለው ጆዲ በትዳሯ ላይ የፈጸመችው ምንዝር በመካከላቸው የነበረው መተማመን ጨርሶ እንዲጠፋ አድርጎ ነበር። በትዳር ውስጥ ደስታ ለማግኘት ደግሞ መተማመን ወሳኝ ነገር ነው፤ በመሆኑም እነዚህ ባለትዳሮች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አስፈልጓቸዋል።
እንደ ምንዝር ያለ ከባድ ችግር በትዳራችሁ ውስጥ አጋጥሟችሁ ትዳራችሁን ለመታደግ እየጣራችሁ ከሆነ ተፈታታኝ ሁኔታ እንደሚያጋጥማችሁ ግልጽ ነው። በተለይ ጉዳዩ ከታወቀ በኋላ ያሉት ወራት አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ቢሆንም አይዟችሁ፤ ሊሳካላችሁ ይችላል! ታዲያ በመካከላችሁ የነበረውን የመተማመን ስሜት እንደገና ማጎልበት የምትችሉት እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ሐሳብ ይህን ለማድረግ ሊረዳችሁ ይችላል። ቀጥሎ የተዘረዘሩትን አራት ሐሳቦች ተመልከቱ።
1 በሐቀኝነት ተነጋገሩ።
ሐዋርያው ጳውሎስ “አሁን ውሸትን ስላስወገዳችሁ . . . እውነትን ተነጋገሩ” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 4:25) መዋሸት፣ ከፊል እውነት መናገር ሌላው ቀርቶ ስለ ጉዳዩ ምንም አለመናገር እንኳ መተማመን እንዳይኖር ጠንቅ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በግልጽና በሐቀኝነት መነጋገር ያስፈልጋችኋል።
መጀመሪያ ላይ ስለተፈጸመው ጉዳይ አንስቶ መወያየት ሊከብዳችሁ ይችላል። ውሎ አድሮ ግን ስለሆነው ነገር በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋችኋል። በውይይቱ ላይ ስለ እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ማንሳት አትፈልጉ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ጉዳዩን ጨርሶ አለማንሳቱም የጥበብ እርምጃ አይደለም። ከላይ የተጠቀሰችው ጆዲ እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ስለ ጉዳዩ ማውራት በጣም ይከብደኝና ያስጠላኝ ነበር። እጅግ የሚጸጽተኝ ነገር በመሆኑ ከናካቴው ልረሳው እፈልግ ነበር።” ይሁንና በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ ውይይት አለማድረጋቸው ችግር አስከትሎባቸዋል። እንዴት? ስቲቭ እንዲህ ይላል፦ “ጆዲ ስለፈጸመችው ድርጊት ለማውራት ባለመፈለጓ ያደረብኝን ጥርጣሬ ማስወገድ አልቻልኩም ነበር።” ጆዲም ያን ጊዜ መለስ ብላ በማስታወስ “በጉዳዩ ላይ ከባለቤቴ ጋር አለመነጋገሬ ግንኙነታችን እንዳይስተካከል እንቅፋት ፈጥሮ ነበር” ብላለች።
ስለተፈጸመው የእምነት ማጉደል ድርጊት ማውራት ስሜትን እንደሚያቆስል ምንም ጥርጥር የለውም። ዴቢ፣ ባሏ ፖል ከጸሐፊው ጋር ምንዝር መፈጸሙን ስታውቅ ምን እንደተሰማት እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “እንዴት? ለምን? ስለ ምን አውርተው ይሆን? እንደሚሉት ያሉ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ። ሳምንታት እያለፉ ሲሄዱ ያለማቋረጥ ስለ ሁኔታው አስብ እንዲሁም በአእምሮዬ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች ይመላለሱ ስለነበር በጣም ስሜታዊ ሆኜ ነበር።” ፖል እንዲህ ይላል፦ “አንዳንድ ጊዜ እኔና ዴቢ የምናደርገው ውይይት ወደ ጦፈ ጭቅጭቅ ይለወጥ ነበር። ሆኖም ሁልጊዜ ይቅርታ እንጠያየቅ ነበር። በሐቀኝነት እንዲህ ያለ ውይይት ማድረጋችን ይበልጥ አቀራርቦናል።”
ታዲያ ውይይታችሁ ውጥረት የነገሠበት እንዳይሆን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ተቀዳሚ ዓላማችሁ የትዳር ጓደኛችሁን መቅጣት ሳይሆን ከአሳዛኙ ድርጊት ትምህርት አግኝታችሁ ትዳራችሁን ማጠናከር እንደሆነ አስታውሱ። ለምሳሌ ቸል ሱ እና ሚስቱ ሚ የንግ፣ ቸል ሱ ምንዝር ለመፈጸም ያበቃው ምን ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት ግንኙነታቸውን እንደገና መገምገም ጀመሩ። ቸል ሱ እንዲህ ብሏል፦ “በግል ጉዳዮቼ በጣም ተጠምጄ እንደነበር ተገነዘብኩ። በተጨማሪም ሌሎችን ለማስደሰትና እንዳደርግ የሚፈልጉትን ነገር ለማሟላት ከልክ በላይ እጨነቅ ነበር። አብዛኛውን ጊዜዬንና ትኩረቴን የምሰጠው ለሌሎች ነበር። በዚህም የተነሳ ከባለቤቴ ጋር የማሳልፈው ጊዜ በጣም አነስተኛ ነበር።” ቸል ሱ እና ሚ የንግ ይህን ማስተዋላቸው አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ያነሳሳቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ ትዳራቸውን ለማጠናከር አስችሏቸዋል።
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ታማኝ ሳትሆን የቀረኸው አንተ ከሆንክ ሰበብ ከመደርደር ወይም ጥፋትህን በትዳር ጓደኛህ ላይ ከማላከክ መቆጠብ ይኖርብሃል። ጥፋተኛ መሆንህንና የትዳር ጓደኛህን በጣም እንደጎዳሃት አምነህ ተቀበል። ተበዳይ ከሆንክ ደግሞ በትዳር ጓደኛህ ላይ ከመጮህ ወይም ስድብና ዘለፋ ከመሰንዘር ተቆጠብ። እንዲህ ማድረግህ የትዳር ጓደኛህ ከአንተ ጋር በግልጽ መነጋገሯን እንድትቀጥል ሊያበረታታት ይችላል።—ኤፌሶን 4:32
2 የጋራ ጥረት አድርጉ።
መጽሐፍ ቅዱስ “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል” በማለት ይናገራል። ለምን? ምክንያቱም “ለሥራቸው መልካም ውጤት [ያገኛሉ] . . . አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል።” (መክብብ 4:9, 10) በመካከላችሁ የነበረውን የመተማመን ስሜት እንደገና ለመመለስ ጥረት በምታደርጉበት ጊዜ ይህን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋችሁ ይበልጥ አስፈላጊ ነው።
አንተና የትዳር ጓደኛህ ግንኙነታችሁን የመረዘውን አለመተማመን በጋራ ሆናችሁ ማስወገድ ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ ትዳራችሁን ለመታደግ ሁለታችሁም ቆርጣችሁ መነሳት አለባችሁ። ችግሩን በተናጠል ለመጋፈጥ ብትሞክሩ ራሳችሁን ለተጨማሪ ችግር ልታጋልጡ ትችላላችሁ። አንዳችሁ የሌላው አጋር እንደሆናችሁ አድርጋችሁ ማሰብ ያስፈልጋችኋል።
ስቲቭና ጆዲ ይህን ተገንዝበዋል። ጆዲ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ስቲቭ ጊዜ ቢወስድብንም ግንኙነታችንን ለማጠናከር በጋራ ጥረት አደረግን። ስቲቭን በዚህ መንገድ በድጋሚ ላለማሳዘን ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር። ስቲቭም፣ በጣም የተጎዳ ቢሆንም ትዳራችን እንዳይፈርስ ለማድረግ ቆርጦ ነበር። በየቀኑ ለእሱ ያለኝን ታማኝነት ማሳየት የምችልባቸውን መንገዶች እፈልግ ነበር፤ እሱም ሁልጊዜ ፍቅሩን ይገልጽልኝ ነበር። ለዚህም ምንጊዜም አመስጋኝ ነኝ።”
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በትዳራችሁ ውስጥ የጠፋውን መተማመን እንደገና ለመመለስ እርስ በርስ ተደጋግፋችሁ ለመሥራት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።
3 መጥፎ ልማዶችን አስወግዳችሁ ጥሩ ልማዶችን አዳብሩ።
ኢየሱስ አድማጮቹን ስለ ምንዝር ካስጠነቀቃቸው በኋላ “ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው” በማለት መክሯል። (ማቴዎስ 5:27-29) ምንዝር የፈጸምከው አንተ ከሆንክ ለትዳራችሁ መሳካት ሲባል አውጥተህ ልትጥላቸው በሌላ አባባል ልታስወግዳቸው የሚገቡ ልማዶች ወይም ዝንባሌዎች ይኖሩ ይሆን?
አብሯችሁ ካመነዘረው ግለሰብ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ እንዳለባችሁ ግልጽ ነው። * (ምሳሌ 6:32፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ፖል ከጸሐፊው ጋር ላለመገናኘት ሲል የሥራ ሰዓቱንና የስልክ ቁጥሩን ቀየረ። ያም ሆኖ ከሴትየዋ ጋር ጨርሶ እንዳይገናኝ ማድረግ አልቻለም። ፖል፣ ሚስቱ እንደገና እንድትተማመንበት ለማድረግ ቆርጦ ስለነበር ሥራውን ለቀቀ። በተጨማሪም የራሱን ሞባይል መያዝ ያቆመ ሲሆን ከሚስቱ ጋር በአንድ ስልክ መጠቀም ጀመረ። እነዚህን እርምጃዎች መውሰዱ ሊያስቸግረው ቢችልም እንዲህ ማድረጉ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል? ሚስቱ ዴቢ እንዲህ ትላለች፦ “ስድስት ዓመት ቢያልፍም እስካሁንም ድረስ ሴትየዋ እንደገና ልታገኘው ትሞክር ይሆናል ብዬ አልፎ አልፎ እጨነቃለሁ። ይሁን እንጂ አሁን ፖል ለፈተናው እንደማይሸነፍ እተማመንበታለሁ።”
በዳይ አንተ ከሆንክ በባሕሪህ ላይ ለውጥ ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሌሎችን የማሽኮርመም ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት ስለመመሥረት የማውጠንጠን ልማድ ይኖርህ ይሆናል። ይህ ከሆነ ‘አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፈህ መጣል’ ይኖርብሃል። የቀድሞ ልማዶችህን አስወግደህ የትዳር ጓደኛህ በአንተ ይበልጥ እንድትተማመን የሚያደርጉ አዳዲስ ባሕርያትን አዳብር። (ቆላስይስ 3:9, 10) ምናልባት በአስተዳደግህ የተነሳ ፍቅርህን መግለጽ ይከብድህ ይሆን? መጀመሪያ ላይ ሊያሳፍርህ ቢችልም እንኳ ለትዳር ጓደኛህ ደጋግመህ ፍቅርህን ከመግለጽ ወደኋላ አትበል። ስቲቭ እንዲህ ይላል፦ “ጆዲ ብዙ ጊዜ በእጇ ዳበስ ወይም ያዝ በማድረግ ፍቅሯን የምትገልጽልኝ ሲሆን አዘውትራም ‘እወድሃለሁ’ ትለኛለች።”
ለተወሰነ ጊዜ ያህል ለትዳር ጓደኛህ በየቀኑ ስለ ውሎህ አንድም ሳታስቀር መናገርህ ጠቃሚ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሚ የንግ እንዲህ በማለት ትናገራለች፦ “ቸል ሱ ከእኔ የሚደብቀው ምንም ነገር እንደሌለ ለማሳየት ሲል ያን ያህል አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮችን እንኳ ሳያስቀር ስለ ውሎው በዝርዝር ይነግረኝ ነበር።”
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ እንደገና ለመተማመን እንድትችሉ የሚረዷችሁ እርምጃዎች ምን እንደሆኑ ተነጋገሩ። እነዚህን ነገሮች በዝርዝር መዝግባችሁ ተግባራዊ አድርጓቸው። በተጨማሪም አብራችሁ ልታከናውኗቸው የምትችሏቸውን አንዳንድ እንቅስቃሴዎች በፕሮግራማችሁ ውስጥ አካትቱ።
4 እንደ ቀድሟችሁ ለመሆን ጊዜ እንደሚወስድ አትዘንጉ።
ሁሉም ነገር እንደ ቀድሞው ሆኗል ብላችሁ ለመደምደም አትቸኩሉ። ምሳሌ 21:5 “ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል” በማለት ያስጠነቅቃል። እንደ ድሮው ለመተማመን ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን ምናልባትም ዓመታት ሊወስድ ይችላል።
ክህደት የተፈጸመብህ አንተ ከሆንክ የትዳር ጓደኛህን ሙሉ በሙሉ ይቅር ለማለትና ጉዳዩን ለመተው የተወሰነ ጊዜ እንደሚያስፈልግህ እሙን ነው። ሚ የንግ እንደሚከተለው በማለት ታስታውሳለች፦ “አንዲት ሚስት ታማኝነቱን ያጎደለውን ባሏን ይቅር ማለት ሲከብዳት ይገርመኝ ነበር። የተበደለችው ሚስት ረዘም ላለ ጊዜ ብስጭቷ የማይበርድላት ለምን እንደሆነ አይገባኝም ነበር። ባሌ እምነቱን ባጎደለ ጊዜ ግን ይቅር ማለት ለምን እንደሚከብድ ገባኝ።” ይቅር ማለትም ሆነ መተማመን በሂደት የሚመጡ ነገሮች ናቸው።
ያም ቢሆን መክብብ 3:1-3 እንደሚለው “ለመገንባትም ጊዜ አለው።” መጀመሪያ ላይ ስሜትህን ለትዳር ጓደኛህ ሳትገልጽ ለራስህ አምቀህ መያዝ የተሻለ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ እንዲህ ማድረግህ በትዳር ጓደኛህ ላይ እንደገና መተማመን እንድትችል አይረዳህም። ግንኙነታችሁን እንደገና “ለመገንባት” እና በመካከላችሁ መተማመን እንዲኖር ለማድረግ የትዳር ጓደኛህን ይቅር ማለት እንዲሁም ስሜትህንና ሐሳብህን ሁሉ ግልጥልጥ አድርገህ ለእሷ በመናገር ይቅርታ ማድረግህን በተግባር ማሳየት ይኖርብሃል። የትዳር ጓደኛህም የሚያስደስቷትንና የሚያሳስቧትን ነገሮች እንድታካፍልህ አበረታታት።
ምሬት እንዲያድርባችሁ በሚያደርጉ ነገሮች ላይ አታውጠንጥኑ። የሚሰማችሁን ምሬት ለማስወገድ ጥረት አድርጉ። (ኤፌሶን 4:32) በዚህ ረገድ አምላክ ራሱ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉ ሊረዳችሁ ይችላል። አምላክ በጥንቷ እስራኤል የነበሩት አምላኪዎቹ ጀርባቸውን በሰጡት ጊዜ በጣም አዝኖ ነበር። ይሖዋ አምላክ ራሱን እንደተከዳ የትዳር ጓደኛ አድርጎ ገልጾ ነበር። (ኤርምያስ 3:8, 9፤ 9:2) ያም ቢሆን “ለዘላለም አልቈጣም” በማለት ተናግሯል። (ኤርምያስ 3:12) ሕዝቡ ከልባቸው ንስሐ ገብተው ወደ እሱ በተመለሱ ጊዜ ይሖዋ ይቅር ብሏቸዋል።
በመካከላችሁ ባለው ግንኙነት ረገድ አስፈላጊው ለውጥ ሁሉ እንደተደረገ ሁለታችሁም በምታምኑበት ጊዜ እያደር የመተማመን ስሜታችሁ እየጎለበተ ይሄዳል። ከዚያ በኋላ ትዳራችሁን ለማዳን ከመረባረብ አልፋችሁ በጋራ የምትደርሱባቸው ሌሎች ግቦች ላይ ማተኮር ትችላላችሁ። እንደዚያም ሆኖ ያደረጋችሁትን መሻሻል በየተወሰነ ጊዜ መለስ ብላችሁ መገምገም ይኖርባችኋል። ሁኔታው ተስተካክሏል ብላችሁ በማሰብ አትዘናጉ። የሚያጋጥሟችሁን ትናንሽ እንቅፋቶች ተቋቁማችሁ ለማለፍ ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ሆናችሁ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረጋችሁ አሳዩ።—ገላትያ 6:9
እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ትዳራችሁን ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ አዲስና ይበልጥ ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት አድርጉ።
ይሳካላችኋል
እንደሚሳካላችሁ በምትጠራጠሩበት ጊዜ፣ የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው አምላክ እንደሆነ አስታውሱ። (ማቴዎስ 19:4-6) ስለዚህ በእሱ እርዳታ ትዳራችሁ እንዲሰምር ማድረግ ትችላላችሁ። ከላይ የተጠቀሱት ባልና ሚስቶች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ትዳራቸውን ማዳን ችለዋል።
በስቲቭና በጆዲ ትዳር ውስጥ ችግር ከተከሰተ 20 ዓመታት አልፈዋል። ስቲቭ ትዳራቸውን ለመታደግ ያደረጉትን ጥረት እንደሚከተለው በማለት ጠቅለል አድርጎ ይገልጸዋል፦ “ጉልህ መሻሻል ያደረግነው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመርን በኋላ ነበር። በዋጋ ሊተመን የማይችል እርዳታ አግኝተናል። በዚህም የተነሳ እነዚያን አስቸጋሪ ጊዜያት ማለፍ ችለናል።” ጆዲ እንዲህ ትላለች፦ “ያንን አስከፊ ጊዜ በጽናት መወጣት በመቻላችን እጅግ እንደተባረክን ይሰማኛል። መጽሐፍ ቅዱስን አብረን በማጥናታችንና ከፍተኛ ጥረት በማድረጋችን አሁን ግሩም ትዳር ሊኖረን ችሏል።”
^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።
^ አን.5 በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሐሳብ ለማግኘት የመስከረም 1999 ንቁ! ገጽ 6ን እና የነሐሴ 8, 1995 (እንግሊዝኛ) ንቁ! ገጽ 10 እና 11ን ተመልከት።
^ አን.17 ለተወሰነ ጊዜ ከግለሰቡ ጋር ጨርሶ አለመገናኘት የማይቻል ከሆነ (ለምሳሌ በሥራ ቦታ) የምትገናኙበትን አጋጣሚ ለመገደብ ጥረት ማድረግ ይኖርባችኋል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ከግለሰቡ ጋር የምትገናኙት ሌሎች ሰዎች ባሉበት እንዲሆን አድርጉ፤ እንዲሁም ጉዳዩን ለትዳር ጓደኛችሁ አሳውቁ።
ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦
-
የትዳር ጓደኛዬ ታማኝነቷን ብታጎድልም ትዳሬን ላለማፍረስ እንድወስን ያደረጉኝ ምክንያቶች ምን ነበሩ?
-
የትዳር ጓደኛዬ ምን ጥሩ ባሕርያት አሏት?
-
ከትዳር ጓደኛዬ ጋር እጠናና በነበረበት ወቅት ትናንሽ በሆኑ መንገዶችም ጭምር ፍቅሬን እገልጽ የነበረው እንዴት ነበር? አሁንስ እንደዚያ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?