መቼም የማልረሳው አስደሳች የእረፍት ጊዜ!
ከአየርላንድ የተላከ ደብዳቤ
መቼም የማልረሳው አስደሳች የእረፍት ጊዜ!
“ስለ ፈተናሽ ብቻ ከምትጨነቂ አእምሮሽን ዘና የሚያደርግ ነገር ያስፈልግሻል። አየርላንድ ያለችው የአክስትሽ ልጅ ጋ ለምን አንሄድም? በዚያውም የመንግሥቱን ምሥራች የመስማት አጋጣሚ አግኝተው ለማያውቁ ሰዎች መስበክ እንችላለን።”
ወላጆቼ ይህን ሐሳብ ሲያቀርቡልኝ መጀመሪያ ላይ ብዙም አልጣመኝም ነበር። የፈተናዬ ነገር ያሳሰበኝ ከመሆኑም ሌላ ከእንግሊዝ ወጥቼም ሆነ በአውሮፕላን ሄጄ ስለማላውቅ የጉዞው ነገር አስጨንቆኝ ነበር። የምንኖረው ሞቅ ደመቅ ባለው የለንደን ከተማ በመሆኑ ‘በአየርላንድ ደቡብ ምዕራባዊ ጫፍ ላይ በምትገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ ያለውን የተረጋጋ ሕይወት የምለምደው እንዴት ነው?’ የሚለው ነገር አሳስቦኝ ነበር። የከተማ ሕይወት ለለመደች የ17 ዓመት ወጣት ጉዞው ፈታኝ እንደሚሆን ተሰምቶኝ ነበር።
የሚገርመው ግን የተጨነቅኩት አለምክንያት ነው። አውሮፕላናችን ካረፈበት ቅጽበት ጀምሮ በአየርላንድ ውበት ተማረክሁ። ያም ሆኖ ጉዞ የጀመርነው ጎህ ሳይቀድ በመሆኑ መኪና ውስጥ እንደገባሁ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ። በመሃል ስነቃ ግን ወጣ ገባ ቢሆንም በጣም የሚያምረውን ገጠራማ አካባቢ እመለከት ነበር፤ በአካባቢው የነበሩት መንገዶች ጠባብ ሲሆኑ ዳርና ዳር ላይ የድንጋይ አጥሮች አሏቸው።
በአየርላንድ የመጀመሪያውን ምሽት ያሳለፍነው ስኪበሪን በተባለች ከተማ ሲሆን እዚያም የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ወደ አየርላንድ ከመጣ አንድ ቤተሰብ ጋር አስደሳችና የሚያንጽ መንፈሳዊ ጭውውት አደረግን። ከዚህ ቤተሰብ ጋር የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጨዋታዎችን ስንጫወት አመሸን። አንደኛው ጨዋታ ላይ እያንዳንዳችን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ባለታሪኮች ስም የተጻፈበት ወረቀት ከአንድ ቦርሳ ውስጥ እናወጣና ይህን ግለሰብ ለማወቅ የሚረዱ ነገሮችን በእንቅስቃሴ ብቻ እናሳያለን፤ ሌሎቹ ደግሞ የባለታሪኩን ማንነት ለመገመት ይሞክራሉ።
በቀጣዩ ቀን ከወላጆቼ፣ ከታናሽ ወንድሜ፣ ከአክስቴ ልጅና ከባሏ እንዲሁም ከአንድ ሌላ ቤተሰብ ጋር ሆነን 30 እንኳ የማይሞሉ ሰዎች ወደሚኖሩባት ኤር የተባለች ትንሽ ደሴት በጀልባ ተሳፍረን ሄድን። ኢየሱስስ ምሥራቹ በመላው ምድር እንደሚሰበክ ተናግሮ የለ! እኛም በዚህች ደሴት ላይ ለሚኖሩት እንግዳ ተቀባይና ተግባቢ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ግሩም ሐሳቦችን ስንነግራቸው ዋልን፤ እግረ መንገዳችንንም የዚያን አካባቢ ያልተነካ ድንግል ውበት የማየት አጋጣሚ አግኝተን ነበር።
ጥርት ባለው ሰማይ ላይ ፀሐይዋ ፍንትው ብላ ትታያለች። በአካባቢው በብዛት ከሚገኙት ደማቅ ቢጫ አበቦች የሚወጣው ለስለስ ያለና ደስ የሚል መዓዛ አየሩን አውዶታል። ረግረጋማው መስክ በጸደይ ወቅት በሚፈኩ አበቦች ተሸፍኗል። ከአሸዋማው የባሕር ዳርቻ ብዙም ሳይርቅ በሚገኙት ቋጥኞች ላይ ለማሚት እና ጋኔት የተባሉት የአእዋፍ ዝርያዎች ከጫጩቶቻቸው ጋር ተኮልኩለዋል። ካለንበት ሆነን አሻግረን ስንቃኝ ሰው የማይኖርባቸው በርካታ ትናንሽ ደሴቶች ይታያሉ፤ እነዚህ ደሴቶች በሙሉ ሮሪንግዎተር ቤይ በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ። የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ምንኛ አስደናቂ ናቸው!
ወደ ስኪበሪን ከተመለስን በኋላ በአካባቢው በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ብዙ ጥሩ ጓደኞች አገኘሁ። እንዲሁም ከዚያ በፊት ሞክሬያቸው የማላውቃቸውን ነገሮች
አደረግኩ፤ ከእነዚህም መካከል በጣም የወደድኩት ካያክ በተባለው ታንኳ መጓዝ ነው። የአየርላንድን የባሕር ዳርቻ ካያክ ውስጥ ሆኖ እንደመመልከት የሚያስደስት ነገር ያለ አይመስለኝም! ለራታችን የሚሆን ዓሣ ለማጥመድ ወደ ባሕሩ ብንሄድም አቆስጣዎች ከፊት ከፊታችን እየዋኙ ዓሦቹን ቀድመው ይለቅሟቸው ነበር። በባሕሩ ዳርቻ ራሳችን የፈጠርናቸውን ጨዋታዎች የተጫወትን ሲሆን የአየርላንድን ባሕላዊ ጭፈራም እንኳ ለመጨፈር ሞክሬ ነበር።ስለ ስኪበሪን ከተማም አንዳንድ ነገሮችን ለማወቅ ሞክረናል። በ1840ዎቹ ዓመታት የአየርላንድ የድንች እርሻ በተበላሸበት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል የዚህች ከተማና የአካባቢዋ ነዋሪዎች ይገኙበታል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረጉ ሲሆን 9,000 የሚያህሉት በጅምላ መቃብር ውስጥ ተቀብረዋል። ሆኖም በቅርቡ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ረሃብ ጨርሶ እንደሚወገድና በዚህ ምክንያት የሞቱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ትንሣኤ እንደሚያገኙ ማወቃችን አጽናናን።
የጉባኤው ክልል ሰፊ በመሆኑ የመንግሥቱ መልእክት ያልደረሳቸውን ሰዎች ለማግኘት በአካባቢው ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብረን ሄድን። ጠባቡን መንገድ ተከትለን ቁልቁል ስንወርድ በአንድ ኮረብታ ላይ የተሠሩ ቤቶች ጋ ደረስን፤ ከዚህ ኮረብታ ላይ የአየርላንድን ባሕር አሻግሮ መመልከት ይቻላል። በዚህ አካባቢ ያገኘናቸው ሰዎችም ቢሆኑ እንግዳ ተቀባዮችና ተግባቢዎች ነበሩ። በኤር ደሴት እንዳደረግነው ሁሉ በዚህ አካባቢም ሰዎችን ስናነጋግር እረፍት ላይ እንደሆንን እና እግረ መንገዳችንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘነውን ደስ የሚል መልእክት ለሌሎች እንደምንናገር እንገልጽላቸው ነበር።
እናቴ ያነጋገረቻት አንዲት ሴት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በደስታ ተቀበለቻት። ከጥቂት ቀናት በኋላ ይህቺን ሴት እንደገና ስናገኛት መጽሔቶቹን እንደወደደቻቸው ነገረችን።
“ሌሎች መጽሔቶችን ይዛችሁልኝ ብትመጡና ብታወያዩኝ ደስ ይለኛል” አለችን። እኛም ወደ አገራችን የምንመለስበት ጊዜ እንደደረሰና ሌላ ሰው መጥቶ እንዲያነጋግራት እንደምናደርግ ገለጽንላት።
ሴትየዋም እናቴን “እንግዲያው እንደገና ስትመጪ መጥተሽ ጠይቂኝ፤ የአየርላንድ ሰዎች አንዴ ያወቅነውን ሰው አንረሳም!” አለች።
የመጨረሻውን የእረፍት ቀናችንን ያሳለፍነው በአካባቢው ባለ ጉባኤ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር ሆነን በባሕሩ ዳርቻ ላይ ነበር። ባሕሩ እየገፋ ያመጣቸውን እንጨቶች ካቀጣጠልን በኋላ ኩልል ያለው ባሕር ወደ ዳርቻው ያወጣቸውን መስል የተባሉ የባሕር እንስሳት ለቅመን ጠበስን። የከተማ ልጅ ብሆንም በዚያ ባሳለፍኩት ጊዜ በጣም ተደስቻለሁ!
በአየርላንድ ስላሳለፍኩት ሳምንት ተናገሪ ብባል ‘መቼም የማልረሳው አስደሳች የእረፍት ጊዜ አሳልፌያለሁ’ ማለት እችላለሁ! የአየርላንድ ቆይታዬ አስደሳች ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን የሚያስደስትና ለእሱ ክብር የሚያመጣ ነገር በማከናወኔ እርካታ ተሰምቶኛል። አምላካችንን ይሖዋን ማገልገል በጣም ያስደስተኛል፤ በተለይ ደግሞ እንደ እኔ ዓይነት ስሜት ካላቸው ብሎም በዚህ ሥራ አብረውኝ ከሚካፈሉ ግሩም ጓደኞቼና የቤተሰቤ አባላት ጋር ሆኜ ይህን ማድረግ መቻሌ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎታል። አፍቃሪና መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው በርካታ ጓደኞች ስለሰጠኝና በአየርላንድ ፈጽሞ የማይረሳ አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ ስለቻልኩ ወደ ቤት ስመለስ ይሖዋን አመሰገንኩት።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
An Post, Ireland