በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛ ሳይንሳዊ ሐሳቦች

ትክክለኛ ሳይንሳዊ ሐሳቦች

“የምክርና የዕውቀት ቃል የሆኑ፣ መልካም ትምህርቶችን አልጻፍሁልህምን? . . . ተገቢውን መልስ ትሰጥ ዘንድ፣ እውነተኛውና የታመኑ ቃሎችን [አላስተማርኩህምን?]”​—ምሳሌ 22:20, 21

መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ በጥንታዊ መጻሕፍት ላይ የሚገኙት ሐሳቦች አስተማማኝ ያልሆኑና አደገኛ ናቸው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ በጣም የተሳሳቱ መሆናቸው በዘመናዊ ሳይንስ ተረጋግጧል። በዛሬው ጊዜም እንኳ የመማሪያ መጻሕፍትን የሚያዘጋጁ ሰዎች መጻሕፍቱን በቅርቡ ከተገኘ እውቀት ጋር ለማስማማት ሲሉ በየጊዜው ማረም ያስፈልጋቸዋል። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ፈጣሪ ሲሆን ቃሉም “ለዘላለም ጸንቶ [እንደሚኖር]” ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።​—1 ጴጥሮስ 1:25

ምሳሌ፦ የሙሴ ሕግ፣ እስራኤላውያን “ከሰፈር ውጭ” ጉድጓድ ቆፍረው እንዲጸዳዱና በኋላም አፈር እንዲመልሱበት ያዝዝ ነበር። (ዘዳግም 23:12, 13) እስራኤላውያን የእንስሳም ሆነ የሰው በድን ከነኩ በውኃ መታጠብ ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 11:27, 28፤ ዘኍልቍ 19:14-16) የሥጋ ደዌ በሽታ ያለባቸው ሰዎች በሽታቸው ተላላፊ እንዳልሆነ እስኪረጋገጥ ድረስ ተገልለው እንዲቀመጡ ይደረግ ነበር።​—ዘሌዋውያን 13:1-8

ዘመናዊው የሕክምና ሳይንስ ምን ያሳያል? ዛሬም ቢሆን ቆሻሻን በተገቢው መንገድ ማስወገድ፣ እጅን መታጠብና የታመሙ ሰዎች ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ማድረግ በሽታን ለመከላከል የሚረዱ ውጤታማ ዘዴዎች ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ)፣ መጸዳጃ ቤት ወይም ሌላ ቆሻሻ ማስወገጃ መንገድ በሌለበት አካባቢ ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ሲገልጽ “ከማንኛውም የውኃ አካል ቢያንስ 30 ሜትር ርቃችሁ ተጸዳዱ፤ እንዲሁም ዓይነ ምድራችሁን ቅበሩ” ይላል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ደግሞ ማኅበረሰቦች ዓይነ ምድርን በአግባቡ የሚያስወግዱ ከሆነ በተቅማጥ በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸው በ36 በመቶ ይቀንሳል። ሐኪሞች በድን ከነኩ በኋላ እጃቸውን ካልታጠቡ ብዙ ታካሚዎች በበሽታ እንዲጠቁ እንደሚያደርጉ ከተገነዘቡ 200 ዓመት እንኳ አይሞላም። ዛሬም ቢሆን እጅን መታጠብ “በሽታዎች እንዳይዛመቱ ለመከላከል የሚረዳ ከሁሉ የበለጠ ውጤታማ ዘዴ እንደሆነ” ሲዲሲ ይገልጻል። የሥጋ ደዌ ወይም ሌላ ዓይነት በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ማድረግን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ሳውዲ ሜዲካል ጆርናል የተባለው መጽሔት በቅርቡ እንደገለጸው “ወረርሽኝ እንደጀመረ አካባቢ፣ ይበልጥ እንዳይዛመት ለመቆጣጠር የሚረዳው ብቸኛው ውጤታማ መንገድ የታመሙ ግለሰቦች ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ማድረግ ሳይሆን አይቀርም።”

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ማንኛውም ጥንታዊ የሃይማኖት መጽሐፍ ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር ይስማማል ብለህ ትጠብቃለህ? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው ትላለህ?

“ማንም ቢሆን በሙሴ ዘመን ንጽሕናን ስለ መጠበቅ የተሰጡትን መመሪያዎች ሲያነብ መደነቁ አይቀርም።”​—ማንዋል ኦቭ ትሮፒካል ሜዲሲን፣ በዶክተር አልዶ ካስቴላኒ እና ዶክተር አልበርት ቻልመርዝ