በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርስ በርስ የሚስማሙ መጻሕፍት

እርስ በርስ የሚስማሙ መጻሕፍት

“መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ።”​—2 ጴጥሮስ 1:21

መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? በጥንት ዘመን የተዘጋጁ ጽሑፎች የተጻፉት በተመሳሳይ ወቅት ቢሆንም እንኳ ብዙውን ጊዜ እርስ በርስ ይጋጫሉ። በተለያዩ ሰዎች፣ በተለያየ ወቅትና ቦታ የተጻፉ መጻሕፍት ደግሞ እርስ በርስ የመስማማታቸው አጋጣሚ እጅግ ጠባብ ነው። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የሚገኙትን 66 መጻሕፍት ያስጻፋቸው አንድ አካል እንደሆነ ይገልጻል፤ በመሆኑም እነዚህ መጻሕፍት እርስ በርስ የሚስማሙ ከመሆናቸውም ሌላ ስለ አንድ ዓይነት መልእክት ይናገራሉ።​—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ምሳሌ፦ በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረ ሙሴ የተባለ እረኛ፣ የሰው ልጆችን የሚያድን “ዘር” እንደሚመጣ በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ ላይ ጽፎ ነበር። ይህ ዘር ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ የትውልድ ሐረግ እንደሚመጣ ቆየት ብሎ በዚሁ መጽሐፍ ላይ ተተንብዮ ነበር። (ዘፍጥረት 3:15፤ 22:17, 18፤ 26:24፤ 28:14) ከ500 ዓመታት በኋላ ነቢዩ ናታን፣ ዘሩ ከንጉሥ ዳዊት የዘር ሐረግ እንደሚመጣ ገለጸ። (2 ሳሙኤል 7:12) ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ዘሩ ኢየሱስንና የተመረጡ ተከታዮቹን ያቀፈ እንደሚሆን አብራራ። (ሮም 1:1-4፤ ገላትያ 3:16, 29) በመጨረሻም የዚህ ዘር አባላት ስለ ኢየሱስ በምድር ላይ እንደሚመሠክሩ፣ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ እንዲሁም ከእሱ ጋር ለ1,000 ዓመት እንደሚገዙ የሚናገር ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ ላይ ተጻፈ፤ ይህ ትንቢት የተነገረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ነበር። ኢየሱስንና የተመረጡ ተከታዮቹን ያቀፈው ይህ ዘር ዲያብሎስን ያጠፋል፤ እንዲሁም የሰው ልጆችን ያድናል።​—ራእይ 12:17፤ 20:6-10

የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ምን ይላሉ? ልዊ ጎሴን የተባሉ ምሁር 66ቱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሚገባ ከመረመሩ በኋላ “በአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ውስጥ በበርካታ ሰዎች የተጻፈው ይህ መጽሐፍ ያለው የሚያስገርም ስምምነት” በጣም እንዳስደነቃቸው ጽፈዋል፤ አክለውም ‘ጸሐፊዎቹ የአምላክ ልጅ ዓለምን እንዴት እንደሚቤዥ የሚገልጸውን ታሪክ ሙሉ በሙሉ ባይረዱትም ተመሳሳይ ዓላማ ለማሳካት ያለማሰለስ ጥረት አድርገዋል’ ብለዋል።​—ቴአፕኑስቲ​ዘ ፕሌናሪ ኢንስፓይሬሽን ኦቭ ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ከ1,500 በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ 40 በሚያህሉ ሰዎች የተጻፈ አንድ መጽሐፍ እርስ በርሱ ይስማማል ብለህ ትጠብቃለህ? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው ትላለህ?

“ይህ መጽሐፍ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ እርስ በርስ ስምምነት ያለው እንደሆነ ይሰማናል። . . . ከሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ይህን መጽሐፍ ሊወዳደር ቀርቶ ሊጠጋ እንኳ የሚችል ጽሑፍ የለም።”​—ዘ ፕሮብሌም ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት፣ በጄምስ ኦር