ከአምላክ ቃል ተማር
በአምላክ ስም መጠቀም ያለብን ለምንድን ነው?
ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶቹን መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።
1. አምላክ ለራሱ ስም ያወጣው ለምንድን ነው?
ማናችንም ብንሆን እንደ “ሰው፣” “አቶ፣” “ወይዘሮ/ወይዘሪት፣” አሊያም “ሴት፣” ባሉት የወል ስሞች ሳይሆን በግል ስማችን ብንጠራ እንደምንመርጥ የተረጋገጠ ነው። ስምህ የራስህ ማንነት ያለህ ግለሰብ መሆንህን ለይቶ ያሳውቃል። አምላክ “ኤልሻዳይ፣” “ሁሉን ቻይ አምላክ፣” “ፈጣሪ” እና “ሉዓላዊ ጌታ፣” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ይጠራል። (ዘፍጥረት 17:1፤ ኢዮብ 8:3፤ መክብብ 12:1፤ የሐዋርያት ሥራ 4:24) ያም ሆኖ አምላክ ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና ለመመሥረት እንድንችል ሲል ለራሱ ያወጣውን ስም ነግሮናል። በአማርኛ የአምላክ የግል ስም ይሖዋ (ያህዌ) ነው።—ዘፀአት 6:3ን አንብብ።
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአምላክን ስም እንደ “እግዚአብሔር፣” “አምላክ” እና “ጌታ” በሚሉት መጠሪያዎች ተክተውታል፤ ይሁንና በጥንቶቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይህ ስም 7,000 ጊዜ ገደማ ይገኝ ነበር። አምላክ ስሙ እንዲታወቅ እንደሚፈልግ ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል።—ኢሳይያስ 12:4ን አንብብ።
2. የአምላክን ስም ማወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የአምላክን ስም ማወቅ ሲባል የስሙን አጠራር ማወቅ ማለት ብቻ አይደለም። በዚህ ስም የተወከለውን አምላክ ማወቅ፣ ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረትን ያመለክታል። ይሖዋ የሚለው ስም “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው። ይህም አምላክ ዓላማውን ለመፈጸም መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሆን ዋስትና ይሰጣል። ስለሆነም የአምላክን ስም ማወቅ፣ እሱ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንደሚፈጽም ማመንን ይጨምራል። (መዝሙር 9:10) የአምላክን ስም የሚያውቁ እና በስሙ የሚጠቀሙ ሰዎች በይሖዋ የሚታመኑ ከመሆኑም ሌላ በሕይወታቸው ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የሚሰጡት ለእሱ ነው። እንዲህ ላሉት ሰዎች ይሖዋ አምላክ ከለላ ይሆንላቸዋል።—መዝሙር 91:14ን አንብብ።
3. አምላክ ስሙ እንዲታወቅ የሚፈልገው ለምንድን ነው?
አምላክ፣ ሰዎች ስሙን እንዲያውቁ የሚፈልገው ይህን ማድረጋቸው ስለሚጠቅማቸው ነው። ስሙን ማወቃቸው የአምላክ ወዳጆች እንዲሆኑና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ታዲያ ይሖዋ ስሙን እንድናሳውቅ የሚጠብቅብን መሆኑ ምን ያስደንቃል?—ዮሐንስ 17:3ን እና ሮም 10:13, 14ን አንብብ።
ኢየሱስ፣ ስለ አምላክ መንገዶች፣ ስለ ሕጎቹና ስለ ተስፋዎቹ በማስተማር የአምላክን ስም አሳውቋል። በዛሬው ጊዜም የኢየሱስ ተከታዮች የአምላክን ስም በመላው ምድር በማሳወቅ እሱ የጀመረውን ሥራ ማከናወናቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ አምላክ የመረጣቸው “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች” በአንድነት ሆነው ይህን ሥራ ይሠራሉ።—የሐዋርያት ሥራ 15:14ን እና ዮሐንስ 17:26ን አንብብ።
4. አምላክ ስሙን የሚያስከብረው እንዴት ነው?
ይሖዋ፣ ስሙ እንዲከበር የሚፈልገው ነቀፋ ስለተሰነዘረበት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች ሕይወት ያላቸው ነገሮችን የፈጠረው አምላክ እንዳልሆነና እሱን መታዘዝ እንደማያስፈልገን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ስለ እኛ እንደማያስብ እንዲያውም በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው እሱ እንደሆነ ይገልጻሉ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች የአምላክን ስም ያጎድፋሉ። ይሁንና በዚህ ድርጊታቸው ለዘላለም አይቀጥሉም። አምላክ ስሙን በሚያጎድፉ ሰዎች ላይ እርምጃ ይወስዳል።—መዝሙር 83:17, 18ን አንብብ።
ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ካጠፋ በኋላ በመላው ምድር ሰላምና ደኅንነት እንዲሰፍን በማድረግ ስሙን ያስከብራል። (ዳንኤል 2:44) በቅርቡ ሁሉም ሰው ይሖዋ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ እንዲያውቅ ይደረጋል።—ሕዝቅኤል 36:23ን እና ማቴዎስ 6:9ን አንብብ።
ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የአምላክን ቃል በማጥናትና እሱን ከሚወዱ ሰዎች ጋር በመሰብሰብ ወደ አምላክ ቅረብ። ይሖዋ ስሙን በሚያስከብርበት ጊዜ ታማኝ አገልጋዮቹን ያስታውሳቸዋል።—ሚልክያስ 3:16
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ተመልከት።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ስም ጥንታዊ በሆነ የዕብራይስጥ ቅጂ ላይ