እውነተኛ ታሪክ እንጂ አፈታሪክ አይደለም
እውነተኛ ታሪክ እንጂ አፈታሪክ አይደለም
“ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ [መረመርኩ።]”—ሉቃስ 1:3
መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? አስገራሚ የሆኑ ታሪኮችን የሚያወሱ ተረቶችና አፈታሪኮች ጉዳዩ የተፈጸመበትን ትክክለኛ ቦታና ቀን እንዲሁም በወቅቱ የነበሩ በታሪክ ውስጥ የታወቁ ሰዎችን አይጠቅሱም። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አኳያ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ በመሆኑ ዘገባው “በሙሉ እውነት” እንደሆነ አንባቢዎች እርግጠኛ መሆን ይችላሉ።—መዝሙር 119:160
ምሳሌ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የባቢሎን ንጉሥ የሆነው “ናቡከደነፆር [የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን] ዮአኪንን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው” ይላል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የባቢሎን ንጉሥ የሆነው “ዮርማሮዴቅ [ኤዊልሜሮዳክ] በባቢሎን በነገሠ በዓመቱ ዮአኪንን ከእስራቱ ፈታው።” ዘገባው አክሎም “ንጉሡም ለዮአኪን እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ የዕለት ቀለቡን ይሰጠው ነበር” ይላል።—2 ነገሥት 24:11, 15፤ 25:27-30
የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ምን አግኝተዋል? የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በጥንቷ ባቢሎን ፍርስራሾች ውስጥ በዳግማዊ ናቡከደነፆር ዘመን የተዘጋጁ ከአስተዳደር ጋር የተያያዙ ሰነዶችን አግኝተዋል። እነዚህ ሰነዶች በባቢሎን ለሚኖሩ ሠራተኞችና ምርኮኞች ስለሚሰጣቸው ድርሻ የሚገልጹ ዝርዝሮችን ይዘዋል። በዝርዝሩ ውስጥ “የያሁድ (የይሁዳ) ምድር ንጉሥ” የሆነው “ያውኪን [ዮአኪን]” እና ቤተሰቡ ተካትተዋል። ናቡከደነፆርን የተካው ኤዊልሜሮዳክ የሚባል ሰው መኖሩን በተመለከተስ የተገኘ መረጃ አለ? በሱሳ ከተማ አቅራቢያ በተገኘ የአበባ ማስቀመጫ ላይ “የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነፆር ልጅ የሆነው የባቢሎን ንጉሥ የአሚል ማርዱክ [የኤዊልሜሮዳክ] ቤተ መንግሥት” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾ ተገኝቷል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ዝርዝር ጉዳዮችን የሚጠቅሱና ትክክለኛ የሆኑ ታሪካዊ መረጃዎችን የያዘ ሌላ ጥንታዊ የሃይማኖት መጽሐፍ አለ? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ጊዜንና ቦታን የሚጠቅሱት ዘገባዎች ከየትኞቹም ጥንታዊ ጽሑፎች የበለጠ ትክክለኛና እምነት የሚጣልባቸው ናቸው።”—ኤ ሳይንቲፊክ ኢንቨስቲጌሽን ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት፣ በሮበርት ዊልሰን
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን ዮአኪንን የሚጠቅስ የባቢሎናውያን ሰነድ
[ምንጭ]
© bpk, Berlin/Vorderasiatisches Museum, SMB/Olaf M. Tessmer/Art Resource, NY