የገቢ መቀነስ የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም
የገቢ መቀነስ የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም
ኦቤድ የሁለት ልጆች አባት ነው። በአፍሪካ በሚገኝ አንድ ትልቅ ከተማ ውስጥ ባለ ዘመናዊ ሆቴል፣ ለአሥር ዓመታት ያህል ይሠራ የነበረ ሲሆን በወቅቱ የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ተቸግሮ አያውቅም። አልፎ አልፎ፣ በአገሩ ውስጥ ወዳሉ የዱር አራዊት የሚገኙባቸው ፓርኮች ቤተሰቡን ይዞ ለሽርሽር በመሄድ ጥሩ ጊዜ ያሳልፉ ነበር። ሆኖም የሚሠራበት ሆቴል ደንበኞች ቁጥር በመቀነሱ ከሥራው ሲፈናቀል የቤተሰቡ ሕይወት ተቀየረ።
ስቴፈን በአንድ ትልቅ ባንክ ውስጥ ከ22 ዓመታት በላይ የሠራ ሲሆን ከጊዜ በኋላ እድገት አግኝቶ የባንኩ ሥራ አስኪያጅ ሆነ። ሥራው ከሚያስገኝለት በርካታ ጥቅማ ጥቅሞች መካከል ትልቅ ቤትና መኪና ይገኙበታል፤ እንዲሁም የቤት ሠራተኞች መቅጠርና ልጆቹን ታዋቂ ትምህርት ቤት ማስገባት ችሎ ነበር። ይሁንና ባንኩ ሠራተኞቹን በአዲስ መልክ ማዋቀር ሲጀምር ስቴፈን ከሥራ ተፈናቀለ። “እኔና ቤተሰቤ በጣም ተደናገጥን” ብሏል። አክሎም “በተስፋ መቁረጥ፣ በምሬትና በስጋት ተዋጥኩ” በማለት ተናግሯል።
በዛሬው ጊዜ እንደነዚህ ያሉ ታሪኮችን መስማት የተለመደ ሆኗል። የዓለም ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ መሄዱ አስተማማኝ ገቢ የነበራቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራቸውን እንዲያጡ አድርጓል። ሥራ ማግኘት የቻሉ ብዙዎች ደግሞ አነስተኛ ደሞዝ ያለው ሥራ ለመያዝ ተገድደዋል፤ በዚያ ላይ የሸቀጦች ዋጋ መናር ኑሮን ከባድ አድርጎባቸዋል። የበለጸጉትም ሆነ በማደግ ላይ ያሉት አገራት የኢኮኖሚ ውድቀቱ ያስከተለው ችግር ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።
ጥበበኛ መሆን ያስፈልጋል
የምናገኘው ገቢ ሲቀንስ ወይም ከሥራ ገበታችን ስንፈናቀል አሉታዊ በሆኑ ሐሳቦች ልንዋጥ እንችላለን። ማንኛውም ሰው ቢሆን እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲገጥሙት በተወሰነ መጠን ስጋት እንደሚያድርበት ግልጽ ነው። ሆኖም አንድ ጠቢብ ሰው “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል!” ብሎ ነበር። (ምሳሌ 24:10 NW) የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥመን ከመደናገጥ ይልቅ የአምላክ ቃል የሚሰጠንን ምክር በሥራ በማዋል “ጥበብን እንደ ውድ ሀብት [ማከማቸት]” ይኖርብናል።—ምሳሌ 2:7 NW
መጽሐፍ ቅዱስ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ምክር ለመስጠት የተዘጋጀ መጽሐፍ ባይሆንም በዚህ ረገድ የሚያቀርባቸው ጠቃሚ ምክሮች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ረድተዋቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ጠቃሚ መመሪያዎች እስቲ እንመልከት።
ወጪያችሁን አስሉ። ኢየሱስ በሉቃስ 14:28 ላይ “ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ልብ እንበል። ይህን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ በጀት ማውጣትና በዚያ መሠረት መኖር ያስፈልጋል። ይሁንና ኦቤድ እንደተናገረው ይህን ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ብሏል፦ “ሥራዬን ከማጣቴ በፊት ያን ያህል አስፈላጊ ያልሆኑ ብዙ ነገሮችን እንሸምት ነበር። ያማረንን ነገር ሁሉ የምንገዛበት ገንዘብ አጥተን ስለማናውቅ በጀት ማውጣት አላስፈለገንም።” አስቀድሞ እቅድ ማውጣት፣ ያላችሁ አነስተኛ ገቢ ቤተሰባችሁ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮችን ለመግዛት እንዲውል ያስችላል።
በአኗኗራችሁ ላይ ለውጥ አድርጉ። ቀድሞ ከነበራችሁ ባነሰ ገቢ መኖርን መልመድ ቀላል ባይሆንም እንዲህ ማድረጉ ግን አስፈላጊ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲመጣ አይቶ ከጉዳት ለማምለጥ ጎንበስ ይላል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 22:3 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ስቴፈን እንዲህ ብሏል፦ “የራሳችን ቤት አነስ ያለ ከመሆኑም ሌላ ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም ገንዘብ ለመቆጠብ ስንል በዚያ መኖር ጀመርን። ልጆቻችንንም ጥሩ ትምህርት ወደሚሰጥበት ሆኖም ውድ ወዳልሆነ ትምህርት ቤት አስገባናቸው።”
በአኗኗራችሁ ላይ ያደረጋችሁትን ለውጥ መቀበል ቀላል እንዲሆንላችሁ ቤተሰባችሁ በግልጽ መነጋገር አለበት። ከሥራ ከመፈናቀሉ በፊት በአንድ ባንክ ውስጥ ለዘጠኝ ዓመታት ይሠራ የነበረው ኦስተን እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ የግድ የሚያስፈልጉን ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ቁጭ ብለን ከተወያየን በኋላ በዝርዝር አሰፈርናቸው። ውድ የሆኑ ምግቦችንና እምብዛም የማያስፈልጉንን አዳዲስ ልብሶች ለመግዛት እንዲሁም ከፍተኛ ወጪ በሚጠይቁ መዝናኛዎች ለመካፈል የምናጠፋውን ገንዘብ መቀነስ ነበረብን። እነዚህን ማስተካከያዎች በምናደርግበት ወቅት ቤተሰቤ ስለተባበረኝ አመስጋኝ ነኝ።” እርግጥ ነው፣ ትናንሽ ልጆች እንዲህ ዓይነት ለውጥ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ላይገባቸው ይችላል፤ ሆኖም ወላጆች የተፈጠረውን ሁኔታ ለልጆቻችሁ ልታስረዷቸው ትችላላችሁ።
ሞክራችሁ የማታውቁትን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ሁኑ። የቢሮ ሠራተኛ ከነበርክ የጉልበት ሥራዎችን መሥራት ከባድ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ኦስተን “በአንድ ትልቅ ድርጅት ውስጥ በአስተዳደር ቦታ ላይ ስሠራ ስለቆየሁ ዝቅተኛ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን ለመቀበል ራሴን ማሳመን ከብዶኝ ነበር” ብሏል። በእርግጥ ይህ የሚያስገርም አይደለም፤ መጽሐፍ ቅዱስም በምሳሌ 29:25 ላይ “ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው” ይላል። ሆኖም ሌሎች ምን ይሉኛል ብለህ በመፍራት እንዲህ ያሉ ሥራዎችን አለመቀበልህ ቤተሰብህን ለመመገብ አያስችልህም። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን አሉታዊ አስተሳሰብ ለማሸነፍ ምን ሊረዳህ ይችላል?
ትሑት መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። ኦቤድ በሆቴል ውስጥ የነበረውን ሥራ ካጣ በኋላ አንድ የቀድሞ የሥራ ባልደረባው ጋራዡ ውስጥ አብሮት እንዲሠራ ሐሳብ አቀረበለት። ይህን ሥራ ሲያከናውን ለተሽከርካሪዎች ቀለምና ሌሎች ነገሮችን ለመግዛት አቧራማ በሆኑ መንገዶች ረጅም ርቀት በእግሩ መጓዝ ነበረበት። ኦቤድ እንዲህ ይላል፦ “ሥራውን ባልወደውም የተሻለ አማራጭ አላገኘሁም። ትሕትናን ማዳበሬ በፊት የማገኘውን ገቢ ሩብ እንኳ በማይሆን ደሞዝ ተቀጥሬ ለመሥራት ፈቃደኛ እንድሆን ረድቶኛል፤ በእርግጥ አሁን የማገኘው ገቢ የቤተሰቤን ፍላጎት ለሟሟላት በቂ ነው።” አንተስ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ማዳበርህ ይጠቅምህ ይሆን?
ባላችሁ የምትረኩ ሁኑ። አንድ መዝገበ ቃላት ባለው የሚረካ ሰው “ባገኘው ነገር የሚደሰትና በቃኝን የሚያውቅ” እንደሆነ ይገልጻል። ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ከባድ ችግር ያለበት ሰው ይህ ዓይነቱ አመለካከት ምክንያታዊ እንዳልሆነ ይሰማው ይሆናል። ይሁንና ማጣት ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቀውና ሚስዮናዊ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ እስቲ እንመልከት፦ “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬያለሁ። በትንሽ ነገር እንዴት መኖር እንደሚቻል አውቃለሁ፣ ብዙ አግኝቶ እንዴት መኖር እንደሚቻልም አውቃለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:11, 12
ምናልባት እኛ ያለንበት ሁኔታ የተሻለ ሊሆን ይችላል፤ ያም ሆኖ ሁኔታዎች ተለዋዋጭ በሆኑበት በዚህ ዓለም የከፋ ነገርም ሊያጋጥመን እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለሰጠው ለሚከተለው ምክር ትኩረት መስጠታችን በእጅጉ ይጠቅመናል፦ “በእርግጥ፣ ባለው ነገር ለሚረካ ሰው ለአምላክ ማደር ትልቅ ትርፍ ያስገኛል። ስለዚህ ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።” ጳውሎስ ስንፍናን ባያበረታታም ለኑሮ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዴት ማዳበር እንደምንችል ጠቁሟል።—1 ጢሞቴዎስ 6:6, 8
እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ምንድን ነው?
ያማረንን ሁሉ በመሰብሰብ ንብረት በንብረት ላይ ማከማቸት ወይም የተንደላቀቀ ሕይወት መምራት እውነተኛ ደስታ አያስገኝም። ኢየሱስ ራሱ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ተናግሯል። በእርግጥም ደስታና እርካታ የሚያስገኘው ባለን ነገር ሌሎችን መርዳትና ለሌሎች የብርታት ምንጭ መሆን ነው።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ ጠንቅቆ ያውቃል። በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጠቃሚ ምክር ብዙዎች ሕይወታቸው እንዲሻሻልና አላስፈላጊ ጭንቀቶችን እንዲያስወግዱ ረድቷቸዋል። በእርግጥ፣ እነዚህን ምክሮች መከተል አንድ ሰው ያለበት የኢኮኖሚ ሁኔታ በአንድ ጊዜ እንዲሻሻል አያደርግም። ሆኖም ‘ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋቸውን የሚቀጥሉ’ ሁሉ መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸው እንደሚሟሉላቸው ኢየሱስ ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 6:33