በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ዓይኔን አበራልኝ

ይሖዋ ዓይኔን አበራልኝ

ይሖዋ ዓይኔን አበራልኝ

ፓትሪስ ኦዬካ እንደተናገረው

ምሽት እየተቃረበ ነበር፤ እንደ ወትሮው በብቸኝነት ተቆራምጄ ሬዲዮ ሳዳምጥ ነው የዋልኩት፤ በዚህ ሁኔታ ሕይወቴን ሙሉ በድቅድቅ ጨለማ ተውጬ ከማሳልፍ ብገላገል እንደሚበጀኝ አሰብኩ። በመሆኑም ቀኑ ከማለቁ በፊት በምሬት የተሞላውን ሕይወቴን ለማጥፋት ወሰንኩ። መርዝ አምጥቼ በውኃ ከበጠበጥኩ በኋላ ፊት ለፊቴ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጥኩት። ሕይወቴን ከማጥፋቴ በፊት ግን ሰውነቴን ተጣጥቤ ጥሩ ልብስ ለመልበስ ፈለግሁ። ይሁንና ራሴን ለማጥፋት የተነሳሁት ለምን ነበር? ዛሬ በሕይወት ኖሬ ይህን ታሪክ ለመናገር የበቃሁትስ እንዴት ነው?

የካቲት 2, 1958 በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ በሚገኘው በካሳይ ኦሪአንታል ግዛት ተወለድሁ። የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለሁ አባቴ ስለሞተ ያሳደገኝ ታላቅ ወንድሜ ነው።

ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ በጎማ ተክል እርሻ ውስጥ ሥራ አገኘሁ። በ1989 አንድ ቀን ጠዋት ላይ ቢሮዬ ሆኜ ሪፖርት እያጠናቀርኩ ሳለ በድንገት ሁሉ ነገር ጨለመብኝ። መጀመሪያ ላይ መብራት የጠፋ መስሎኝ ነበር፤ ሆኖም የጀነሬተሩ ድምፅ ይሰማኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጊዜው ገና ቀን ነበር! ምንም ነገር ሌላው ቀርቶ ፊት ለፊቴ ያሉትን ወረቀቶች እንኳ ማየት እንደተሳነኝ ስገነዘብ ድንጋጤ ወረረኝ!

ወዲያውኑ በእኔ ሥር ካሉት ሠራተኞች አንዱን ጠራሁና ወደ ክሊኒኩ እንዲወስደኝ ጠየቅሁት። እዚያ ያለው ሐኪምም ወደ ከተማ ሄጄ የበለጠ ልምድ ያለው ሐኪም ቢያየኝ የተሻለ እንደሆነ ነገረኝ። ሐኪሙ ሬቲናዎቼ እንደተቀደዱና ችግሩ ከባድ እንደሆነ ስለተገነዘበ ወደ ዋና ከተማው ወደ ኪንሻሳ ላከኝ።

ሕይወት በኪንሻሳ

በኪንሻሳ ብዙ የዓይን ሐኪሞች ጋ ብሄድም አንዳቸውም ሊረዱኝ አልቻሉም። በሆስፒታል ውስጥ ለ43 ቀናት ከቆየሁ በኋላ ሐኪሞቹ የማየት ችሎታዬን ሙሉ በሙሉ እንዳጣሁ ነገሩኝ! ከዚያ በኋላ ቤተሰቦቼ ተአምራዊ ፈውስ ይሰጣሉ ወደሚባሉ የተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች ወሰዱኝ፤ ሆኖም አንዳቸውም ቢሆኑ ሊፈውሱኝ አልቻሉም።

በመጨረሻም የማየት ችሎታዬ እንደሚመለስልኝ የነበረኝ ተስፋ በንኖ ጠፋ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ነገር ጨለመብኝ። የዓይኔን ብርሃን ብቻ ሳይሆን መተዳደሪያዬንም አጣሁ። ይህም እንዳይበቃ ደግሞ ባለቤቴ ቤት ውስጥ ያለንን ነገር ሁሉ ሰብስባ ጥላኝ ሄደች። ከቤት መውጣትና ከሌሎች ጋር መሆን ያሳፍረኝ ጀመር። ከሰዎች ርቄ ቤት ውስጥ ብቻዬን እውል ነበር። ጨርሶ የማልረባ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር።

ሕይወቴን ለማጥፋት ሁለት ጊዜ ሞክሬያለሁ። በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት ለሁለተኛ ጊዜ ያደረግሁትን ሙከራ ነው። በዚህ ወቅት ያተረፈኝ በቤተሰባችን ውስጥ ያለ አንድ ትንሽ ልጅ ነው። ሰውነቴን እየታጠብኩ እያለ ልጁ ሳያውቅ መርዙን መሬት ላይ ደፋው። ደስ የሚለው ነገር ልጁ መርዙን አልጠጣውም። እኔ ግን መርዙ የነበረበትን ኩባያ ሳጣው በጣም ተበሳጨሁ። በኋላ ላይ ኩባያውን የፈለግሁት ለምን እንደሆነና ምን ላደርግ አስቤ እንደነበር ለቤተሰቦቼ ነገርኳቸው።

አምላክም ሆነ ቤተሰቦቼ ራሴን ከማጥፋት ስለጠበቁኝ አመሰግናቸዋለሁ። ሕይወቴን ለማጥፋት የነበረኝ እቅድ ከሽፏል።

እንደገና ደስተኛ መሆን

በ1992 አንድ እሁድ ቀን ቤቴ ቁጭ ብዬ እያጨስኩ ሳለ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች መጡ፤ እነዚህ ሰዎች ከቤት ወደ ቤት እየሰበኩ ነበር። ዓይነ ስውር መሆኔን ስላስተዋሉ በ⁠ኢሳይያስ 35:5 ላይ የሚገኘውን “በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ” የሚለውን ሐሳብ አነበቡልኝ። እነዚህን ቃላት ስሰማ በደስታ ፈነደቅሁ። ከዚህ ቀደም እሄድባቸው የነበሩት ቤተ ክርስቲያኖች ከሚሉት በተቃራኒ የይሖዋ ምሥክሮች ተአምራዊ ፈውስ እንደሚያደርጉልኝ አልተናገሩም። ከዚህ ይልቅ ስለ አምላክ ከተማርኩ እሱ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የማየት ችሎታዬን እንደገና እንደማገኝ አስረዱኝ። (ዮሐንስ 17:3) በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ወዲያውኑ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። ከዚህም ሌላ በአካባቢያችን ባለው የመንግሥት አዳራሽ በሚከናወኑት በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ፤ እንዲሁም በሕይወቴ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን አደረግሁ። ማጨስም አቆምኩ።

ይሁንና ማየት አለመቻሌ መንፈሳዊ እድገት እንዳላደርግ እንቅፋት ሆኖብኝ ነበር። በመሆኑም ለዓይነ ስውራን ወደተዘጋጀ ተቋም በመሄድ በብሬይል ማንበብና መጻፍ ተማርኩ። ይህን በማድረጌ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ለስብከቱ ሥራ በሚሰጠው ሥልጠና መካፈል ችያለሁ። ብዙም ሳይቆይ በምኖርበት አካባቢ መስበክ ጀመርኩ። ይህም በሕይወቴ እንደገና ደስተኛ ለመሆን አስቻለኝ። መንፈሳዊ እድገት ማድረጌን የቀጠልኩ ሲሆን ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩ። ከዚያም ግንቦት 7, 1994 ተጠመቅሁ።

ለይሖዋና ለሰዎች ያለኝ ፍቅር እያደገ ሲመጣ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ። ከታኅሣሥ 1, 1995 ወዲህ የዘወትር አቅኚ በመሆን አብዛኛውን ጊዜዬን በስብከቱ ሥራ እያሳለፍኩ ነው። ከዚህም ሌላ ከየካቲት 2004 ጀምሮ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ የማገልገል ልዩ መብት አግኝቻለሁ። አንዳንድ ጊዜ በአካባቢያችን በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር እንድሰጥ እጋበዛለሁ። እነዚህን ሁሉ በረከቶች በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት የአካል ጉዳት ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ያለንን ምኞት እንዳንፈጽም ሊያግደን እንደማይችል መገንዘብ ችያለሁ።

ይሖዋ “ዓይን” ሰጥቶኛል

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ዓይነ ስውር በመሆኔ ምክንያት ሚስቴ ትታኝ ሄዳለች። ያም ቢሆን ግን ይሖዋ ሌላ በረከት ሰጥቶኛል። ለየት ባለ መንገድም ቢሆን ዓይን ሰጥቶኛል ማለት እችላለሁ። የአካል ጉዳት ቢኖርብኝም እንኳ እኔን ለማግባት ፈቃደኛ የሆነችው አኒ ማቫምቡ እንደ ዓይን ሆናልኛለች። እሷም የሙሉ ጊዜ ሰባኪ በመሆኗ ሁልጊዜ ለስብከት ስወጣ አብራኝ ትሄዳለች። ከዚህም ሌላ ንግግሮቼን ስዘጋጅ ትምህርቱ የተውጣጣባቸውን ጽሑፎች ጮክ ብላ በማንበብ ሐሳቡን በብሬይል መጻፍ እንድችል ትረዳኛለች። ባለቤቴ ለእኔ ልዩ በረከት ናት። አኒ፣ በ⁠ምሳሌ 19:14 ላይ የሚገኘውን “ቤትና ሀብት ከወላጆች ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት” የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት እንድገነዘብ አድርጋኛለች።

ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለእኔና ለአኒ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ በመስጠት ባርኮናል። ወደፊት በገነት ውስጥ ፊታቸውን ለማየት እናፍቃለሁ! ያገኘሁት ሌላ በረከት ደግሞ መኖሪያ የሰጠን ታላቅ ወንድሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀብሎ መጠመቁ ነው! ሁላችንም አንድ ጉባኤ ውስጥ ነን።

አምላክ አትረፍርፎ ስለባረከኝ፣ የአካል ጉዳተኛ ብሆንም እንኳ እሱን የበለጠ ለማገልገል ከልቤ እመኛለሁ። (ሚልክያስ 3:10) የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና መከራን ሁሉ ከምድር ላይ እንዲያስወግድ በየቀኑ እጸልያለሁ። ይሖዋን ካወቅሁ ወዲህ ያለውን ሕይወቴን ሳስብ “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” ብዬ በልበ ሙሉነት መናገር እችላለሁ።​—ምሳሌ 10:22

[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ሳቀርብ፤ ከቤተሰቤና ከወንድሜ ጋር