በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ፈጽሞ የማይቻል!” ምን ማለት ነው?

“ፈጽሞ የማይቻል!” ምን ማለት ነው?

“ፈጽሞ የማይቻል!” ምን ማለት ነው?

ታይታኒክ የተባለችው በጣም ግዙፍና በወቅቱ ከነበሩት መርከቦች ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘላት የቅንጦት መርከብ በ1912 ከወደብ ተንቀሳቀሰች። ይህች መርከብ የተራቀቀ ንድፍ ያላት ከመሆኑም ሌላ በሚገባ ታስቦበት የተሠራች በመሆኗ “ፈጽሞ አትሰምጥም” ተብሎላት ነበር። የተፈጠረውን ሁኔታ ግን በታሪክ የምናውቀው ነው። ታይታኒክ የመጀመሪያ ጉዞዋን ስታደርግ በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ከበረዶ ዐለት ጋር ተጋጭታ ሰመጠች፤ በዚህም ምክንያት 1,500 የሚያህሉ ተሳፋሪዎች ሕይወታቸውን አጡ። ፈጽሞ እንደማትሰምጥ የተነገረላት መርከብ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ ጥልቁ ውቅያኖስ ወረደች።

አንድ ነገር “ፈጽሞ የማይቻል” እንደሆነ እንድናስብ የሚያደርጉን የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ። ለምሳሌ አንድን ነገር መቋቋም፣ ማከናወን ወይም መረዳት ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ለመግለጽ ስንፈልግ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል እንደሆነ እንናገር ይሆናል። በዛሬው ጊዜ የምናያቸው አብዛኞቹ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በአንድ ወቅት ፈጽሞ የማይቻሉ እንደሆኑ ይታሰቡ ነበር፤ ምክንያቱም በወቅቱ የሰው ልጅ እነዚህን ነገሮች ሊሠራቸው ቀርቶ ሊያልማቸው እንኳ አይችልም ነበር። ጨረቃን መርገጥ፣ ወደ ማርስ ተሽከርካሪ መላክና ከምድር ሆኖ እንቅስቃሴውን መቆጣጠር፣ የሰው ልጅን የጂን አወቃቀር መረዳት፣ በሌላ ከተማ ወይም የዓለም ክፍል እየተፈጸመ ያለን ሁኔታ ባለንበት ሆነን በዜና መመልከት እና የመሳሰሉት የዛሬ 50 ዓመት ፈጽሞ እንደማይቻሉ ይታሰቡ የነበሩ ዛሬ ግን ያን ያህል የማያስደንቁ ነገሮች ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሮናልድ ሬገን በተለያዩ የሳይንስ መስኮች ወሳኝ ቦታ ላላቸው ሰዎች ንግግር ሲሰጡ ጉዳዩን እንዲህ በማለት ጠቅለል አድርገው ገልጸውታል፦ “በቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የምትገኙ እናንት [ምሁራን] ትናንት ፈጽሞ የማይቻሉ የነበሩ ነገሮች ዛሬ በጣም የተለመዱ እንዲሆኑ አድርጋችኋል።”

ፕሮፌሰር ጆን ብሮቤክ በዓለም ላይ ከሚታዩት በርካታ አስደናቂ እመርታዎች አንጻር እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ የሳይንስ ሊቅ፣ አንድ ነገር ፈጽሞ እንደማይሆን አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም። መናገር የሚችለው ነገር ቢኖር ይህ ነገር የሚሆን እንደማይመስል ብቻ ነው። በእርግጥ፣ ‘አሁን ካለን ግንዛቤ አንጻር ይህ ሁኔታ የማይቻል ነው’ ማለት ይችል ይሆናል።” ፕሮፌሰሩ አክለው እንደተናገሩት አንድ ነገር ፈጽሞ የማይቻል ከመሰለን “በባዮሎጂና በፊዚዮሎጂ ከምናውቀው ነገር ውጭ አንድ የኃይል ምንጭ” እንዳለ ማስታወስ ይኖርብናል፤ “በቅዱሳን ጽሑፎቻችን ላይ ይህ የኃይል ምንጭ የአምላክ ኃይል እንደሆነ ተገልጿል።”

በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል

ፕሮፌሰር ብሮቤክ ከላይ ያለውን አስተያየት ከመሰንዘራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው የናዝሬቱ ኢየሱስ “በሰዎች ዘንድ የማይቻል ነገር በአምላክ ዘንድ ይቻላል” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 18:27) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ፣ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ ኃይል ነው። ይህን ኃይል ቴክኖሎጂ ባፈራው በየትኛውም መሣሪያ መለካት አይቻልም። መንፈስ ቅዱስ፣ በራሳችን ኃይል ፈጽሞ ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮችን ለማከናወን ያስችለናል።

ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ፈጽሞ ልንቋቋማቸው እንደማንችል የሚሰሙን ሁኔታዎች ብዙውን ጊዜ ያጋጥሙናል። ለምሳሌ ያህል፣ የምንወደውን ሰው በሞት በምናጣበት አሊያም የቤተሰባችን ሕይወት በውጥረት የተሞላ በሚሆንበት ጊዜ ሁኔታውን መቋቋም እንደማንችል ወይም በተስፋ መቁረጥ አዘቅት ውስጥ እንደወደቅንና መውጫ ቀዳዳ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። በተጨማሪም አቅም እንደሌለን ሊሰማንና በከፍተኛ ጭንቀት ልንዋጥ እንችላለን። ታዲያ በዚህ ወቅት ምን ማድረግ እንችላለን?

ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ የሚታመንና እሱን ለማስደሰት አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ እያደረገ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠው የሚጸልይ ሰው እንደ ተራራ የማይገፉ የሚመስሉ እንቅፋቶችን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ እንደሚያገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ኢየሱስ የተናገረውን የሚያበረታታ ሐሳብ ልብ በል፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና በልቡ ሳይጠራጠር የተናገረው ነገር እንደሚፈጸም ቢያምን ይሆንለታል።” (ማርቆስ 11:23) የአምላክ ቃልና መንፈሱ የሚሰጡት ኃይል በሕይወታችን ውስጥ ተጽዕኖ እንዲያሳድር የምንፈቅድ ከሆነ ልንቋቋመው የማንችለው ሁኔታ የለም።

ለ38 ዓመታት በትዳር አብራው ያሳለፈችውን ባለቤቱን በካንሰር ያጣን አንድ ሰው ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ሰው በጥልቅ ሐዘን ከመዋጡም ሌላ በዚህ ሁኔታ መኖር እንደማይችል ተሰምቶት ነበር። እሷን አጥቶ ከሚኖር ይልቅ ሞትን የተመኘባቸው ጊዜያት ነበሩ። “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ” እንደሚሄድ ሆኖ ይሰማው እንደነበር ተናግሯል። (መዝሙር 23:4) ያን ጊዜ መለስ ብሎ ሲያስብ፣ በእንባ ያቀረባቸው ጸሎቶች እንዲሁም በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቡና የአምላክን መንፈስ አመራር ለማግኘት ከልቡ ጥረት ማድረጉ ፈጽሞ ሊቋቋመው እንደማይችል የተሰማውን ሁኔታ በጽናት ለመወጣት እንዳስቻለው ይሰማዋል።

አንድ ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ በጣም ከባድ ችግሮች አጋጥመዋቸው ነበር። ባልየው በጣም ኃይለኛ ከመሆኑም ሌላ በርካታ መጥፎ ልማዶች ነበሩት። ባለቤቱ በዚህ ሁኔታ በሕይወት መቀጠል ፈጽሞ እንደማትችል ስለተሰማት ራሷን ለመግደል ሙከራ አድርጋ ነበር። በዚህ መሃል ባልየው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። የተማረው ነገር መጥፎ ልማዶቹን እንዲያስወግድና ግልፍተኝነቱን እንዲያሸንፍ ረዳው። የዚህ ሰው ሚስት፣ ባሏ “ፈጽሞ የማይቻሉ” ይመስሉ የነበሩ ለውጦችን ማድረጉ በጣም አስደነቃት።

ዕፅ ይወስድና ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ይመራ የነበረ ሌላ ሰው ደግሞ ይህ ነው የማይባል የከንቱነት ስሜት ይሰማው እንደነበር ገልጿል። “ለራሴ ያለኝ አክብሮት ጨርሶ ጠፍቶ ነበር” በማለት ያስታውሳል። “ጌታ ሆይ፣ አንተ እንዳለህ አውቃለሁ። እባክህ እርዳኝ!” በማለት ወደ አምላክ አጥብቆ ጸለየ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሲያጠና ጸሎቱ እንደተመለሰለት የተሰማው ሲሆን ጥናቱም በሕይወቱ ውስጥ ለማመን የሚያዳግቱ ለውጦችን እንዲያደርግ አነሳሳው። እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ በጥፋተኝነትና በዋጋ ቢስነት ስሜት እዋጣለሁ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መንፈሴ ይደቆሳል። ይሁንና የአምላክ ቃል እንደነዚህ ያሉትን የሚረብሹ ስሜቶች ለመቋቋም እንድችል ረድቶኛል። ሌሊት ላይ እንቅልፍ በማጣበት ጊዜ የተማርኳቸውን ጥቅሶች ድምፄን አውጥቼ እደግማቸዋለሁ። እነዚህ ጥቅሶች አእምሮዬን ከመጥፎ ሐሳቦች ለማጽዳት በጣም ረድተውኛል።” ይህ ሰው በአሁኑ ወቅት ደስተኛ ትዳር አለው። እሱና ባለቤቱ፣ ሰዎች የአምላክ ቃል ባለው ኃይል ላይ እምነት እንዲኖራቸው ለመርዳት በትጋት ይሠራሉ። ይህ ሰው በወጣትነቱ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጦ በነበረበት ወቅት አሁን ያለው ዓይነት ሕይወት ይኖረኛል ብሎ ፈጽሞ አያስብም ነበር።

እነዚህ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የአምላክ ቃል ኃይል አለው፤ ቅዱስ መንፈሱም በሕይወታችን ውስጥ “ፈጽሞ የማይቻሉ” የሚመስሉ ነገሮችን ማከናወን ይችላል። ይሁንና “ይህ እምነት ይጠይቃል!” ትል ይሆናል። አልተሳሳትክም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም” ይላል። (ዕብራውያን 11:6) እስቲ ጉዳዩን በዚህ መንገድ ለማየት ሞክር፦ የባንክ ሥራ አስኪያጅ የሆነ ወይም ሌላ ዓይነት ሥልጣን ያለው ጥሩ ወዳጅ አለህ እንበል፤ ይህ ሰው “ስለ ምንም ነገር አትጨነቅ። ማንኛውም ነገር ሲያስፈልግህ ወደ እኔ ና” ብሎሃል። እንዲህ ያለው ተስፋ እንደሚያጽናናህ ምንም ጥርጥር የለውም። የሚያሳዝነው ግን አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ቃላቸውን መጠበቅ አይችሉም። ምናልባትም ይህ ወዳጅህ በአሳቢነት ተነሳስቶ የገባልህን ቃል መፈጸም እንዳይችል የሚያደርግ ሁኔታ ያጋጥመው ይሆናል። ለምሳሌ ወዳጅህ ቢሞት አንተን ለመርዳት የነበረው ፍላጎትም ሆነ ችሎታ መና ይቀራል። በሌላ በኩል ግን ሰዎች ቃላቸውን እንዳይፈጽሙ የሚያደርጓቸው የትኞቹም ነገሮች የይሖዋን አቅም አይገድቡትም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “የሚሳነው ነገር የለም” የሚል ዋስትና ይሰጠናል።​—ሉቃስ 1:37 አ.መ.ት

“ይህን ታምኛለሽ?”

በ⁠ሉቃስ 1:37 ላይ የሚገኘው ከላይ ያለው ሐሳብ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ሣራ የምትባል የ90 ዓመት አረጋዊት፣ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ሲነገራት ስቃ ነበር፤ ያም ሆኖ እስራኤላውያን የሚባሉ ሕዝቦች ሊኖሩ የቻሉት የተሰጣት ተስፋ ስለተፈጸመላት ነው። በትልቅ ዓሣ የተዋጠ አንድ ሰው በዓሣው ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት ከቆየ በኋላ በሕይወት ተርፎ የራሱን ታሪክ ለመጻፍ በቅቷል፤ ይህ ሰው ዮናስ ይባላል። አውጤኪስ የተባለ አንድ ወጣት ከፎቅ ላይ ወድቆ ሕይወቱ ቢያልፍም ከሞት ተነስቷል፤ ይህን ዘገባ ያሰፈረው ሉቃስ ሐኪም በመሆኑ ራስን በመሳት እና በሞት መካከል ያለውን ልዩነት በደንብ ያውቅ ነበር። እነዚህ ዘገባዎች ተረቶች አይደሉም። እያንዳንዱን ታሪክ በጥልቀት ብንመረምር እውነተኛነቱን ማረጋገጥ እንችላለን።​—ዘፍጥረት 18:10-14፤ 21:1, 2፤ ዮናስ 1:17፤ 2:1, 10፤ የሐዋርያት ሥራ 20:9-12

ኢየሱስ ለወዳጁ ለማርታ የሚከተለውን አስደናቂ ሐሳብ ነግሯት ነበር፦ “በሕይወት ያለና በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ . . . ፈጽሞ አይሞትም።” ኢየሱስ፣ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል የሚመስለውን ይህን ተስፋ ከሰጣት በኋላ “ይህን ታምኛለሽ?” የሚል ራሷን እንድትመረምር የሚያነሳሳ ጥያቄ አቀረበላት። ዛሬም ቢሆን ይህን ጥያቄ ትኩረት ሰጥተን ልናስብበት ይገባል።​—ዮሐንስ 11:26

በምድር ላይ ለዘላለም መኖር​ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው?

ለረጅም ዘመን መኖር ከሕግ ጋር በተያያዘ ስለሚኖረው ተጽዕኖ በሚገልጽ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ጸሐፊዎቹ “አሁን ካለን የበለጠ ረጅም ዕድሜ እንዲያውም ለዘላለም መኖር የምንችልበት ጊዜ ሩቅ ላይሆን ይችላል” የሚል ሐሳብ አስፍረው ነበር። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደገለጸው የምንሞተው ሴሎቻችን እክል ስለገጠማቸው፣ ስላረጁ ወይም በሌላ ሂደት የተነሳ ሳይሆን በሰውነታችን ውስጥ የሚከናወኑት ሂደቶች ባልታወቀ ምክንያት ስለሚበላሹ ወይም መሥራት ስለሚያቆሙ ይመስላል። * ኢንሳይክሎፒዲያው እንደሚለው ከሆነ አንድ ሰው የሚያረጀው ውስብስብ የሆነን ሂደት ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉት ነገሮች ስለሚበላሹ ሊሆን ይችላል።

ከላይ ያሉት ሐሳቦች ትኩረት የሚስቡ ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ለዘላለም መኖር እንችላለን ብለን እንድናምን የሚያደርግ ከሳይንስ ይበልጥ አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ያቀርባል። የሕይወት ምንጭ የሆነው ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ‘ሞትን ለዘላለም እንደሚውጥ’ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 36:9፤ ኢሳይያስ 25:8) ይህን ታምናለህ? ይህን ቃል የገባው ይሖዋ ሲሆን እሱ ደግሞ ሊዋሽ አይችልም።​—ቲቶ 1:2

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 ስለ እርጅናና ስለ ዕድሜያችን ርዝመት፣ ጥልቀት ያለው ሐሳብ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ንቁ! መጽሔት የግንቦት 2006 እትም ላይ የሚገኘውን “ምን ያህል ዕድሜ መኖር ትችላለህ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ትናንት ፈጽሞ የማይቻሉ የነበሩ ነገሮች ዛሬ በጣም የተለመዱ [ሆነዋል]።”​—ሮናልድ ሬገን

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሕይወት ከባድ ሲሆንብህ ወደ ማን ዘወር ማለት ትችላለህ?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

NASA photo