በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

አምላክ፣ አገልጋዮቹ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ብቻ እንዲያገቡ ያዘዘው ለምንድን ነው?

አምላክ፣ አገልጋዮቹ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ብቻ እንዲያገቡ ያዘዘው ለምንድን ነው?

▪ አምላክ ለእስራኤል ሕዝብ የሰጠው ሕግ በዙሪያቸው ያሉትን ብሔራት በተመለከተ የሚከተለውን መመሪያ ይዞ ነበር፦ “ከእነርሱ ጋር ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ።” (ዘዳግም 7:3, 4) ይህ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው?

አንደኛ፣ ሰይጣን የአምላክ ሕዝቦች የሐሰት አማልክትን እንዲያመልኩ በማድረግ በቡድን ደረጃ ሊበክላቸው እንደሚፈልግ ይሖዋ ያውቃል። በመሆኑም አምላክ፣ የማያምኑ ሰዎች “እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ [ያደርጋሉ]” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ይህ በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። እስራኤላውያን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከጀመሩ የአምላክን ሞገስና ጥበቃ ያጣሉ፤ ይህም በቀላሉ በጠላቶቻቸው እጅ እንዲወድቁ ያደርጋል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ይህ ብሔር ተስፋ የተደረገውን መሲሕ እንዴት ሊያስገኝ ይችላል? በእርግጥም ሰይጣን፣ እስራኤላውያን ከማያምኑ ሰዎች ጋር እንዲጋቡ ለማድረግ የሚሞክርበት በቂ ምክንያት ነበረው።

ጉዳዩ ከእያንዳንዱ እስራኤላዊ አንጻር ሲታይ ደግሞ ይህ ሕግ አምላክ ለሕዝቦቹ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው ይጠቁማል። ይሖዋ፣ የእያንዳንዱ አገልጋዩ ደስታና ደኅንነት የተመካው ከእሱ ጋር ባለው የቅርብ ዝምድና ላይ እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ የማያምን የትዳር ጓደኛ ሊያሳድር ስለሚችለው አደገኛ ተጽዕኖ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት ነበረው? እስቲ የንጉሥ ሰለሞንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የማያምኑ ሚስቶች “ልባችሁን ወደ አማልክታቸው . . . ይመልሱታል” በማለት ይሖዋ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰለሞን ያውቅ ነበር። ሰለሞን ለየት ያለ ጥበብ የነበረው በመሆኑ የአምላክ ምክር እንደማያስፈልገው ወይም ምክሩ ለእሱ እንደማይሠራ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ምክሩን ችላ ብሏል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? “ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት።” ይህ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! ሰለሞን የይሖዋን ሞገስ ያጣ ሲሆን የእሱ ታማኝ አለመሆን ሕዝቡ እንዲከፋፈል ምክንያት ሆነ።​—1 ነገሥት 11:2-4, 9-13

አንዳንዶች፣ ‘ይህን ምክር ተግባራዊ ካላደረጉት መካከል ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉም አይደሉም’ ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላዊው መሐሎን ሞዓባዊቷን ሩትን አግብቷል፤ ይህች ሴት ደግሞ ድንቅ እምነት ያላት የይሖዋ አምላኪ ሆናለች። ይሁንና ሞዓባዊ ሴቶችን ማግባት አደገኛ አካሄድ ነበር። መሐሎን ሞዓባዊት ሴት ማግባቱ ጥሩ ውሳኔ እንደነበረ አልተገለጸም፤ እንዲያውም መሐሎን የሞተው በወጣትነቱ ይኸውም ሩት የይሖዋ አምላኪ ከመሆኗ በፊት ይመስላል። የመሐሎን ወንድም ኬሌዎን ያገባት ዖርፋ የተባለችው ሞዓባዊት ሴት ‘አማልክቷን’ ማምለኳን አልተወችም። በሌላ በኩል ደግሞ ቦዔዝ፣ ሩትን ያገባት የይሖዋ አምላኪ ከሆነች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። ከጊዜ በኋላም አይሁዳውያን ሩትን “ሙሉ በሙሉ ወደ ይሁዲነት እንደተለወጠች ሴት” አድርገው ተመልክተዋታል። የሩት እና የቦዔዝ ጋብቻ ለሁለቱም በረከት አምጥቶላቸዋል።​—ሩት 1:4, 5, 15-17፤ 4:13-17

ታዲያ ይሖዋ አማኝ የሆኑ ሰዎችን ብቻ ማግባትን አስመልክቶ የሰጠው ምክር የማይሠራባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ለመግለጽ እንደ መሐሎንና ሩት ያሉትን ጋብቻዎች እንደ ምሳሌ መጥቀስ ምክንያታዊ ይመስልሃል? አማኝ ያልሆኑ ሰዎችን ስለ ማግባት እንዲህ ዓይነት የመከራከሪያ ነጥቦችን ማንሳት አንድ ሰው በቁማር ብዙ ገንዘብ ስላገኘ ብቻ ቁማር ተቀባይነት ያለው መተዳደሪያ ነው የማለት ያህል አይሆንም?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ያሳስባል። እንዲሁም “ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ [እንዳንጠመድ]” ያስጠነቅቀናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ምክር የሚሰጠው የትዳር ጓደኛ እየፈለጉ ላሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ነው። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ የማያምን ሰው አግብተው የሚኖሩ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሳካ መንገድ መወጣት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚጠቁም ምክር ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 7:12-16, 39፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ምክሮች በሙሉ የጋብቻ መሥራች የሆነው ይሖዋ አምላክ፣ ያገባንም ሆንን ያላገባን አገልጋዮቹ ደስተኞች እንድንሆን እንደሚፈልግ ያሳያሉ።