በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በጥንት ዘመን የኖሩ ሰዎች ቅጥራንን ለማያያዣነት ይጠቀሙበት የነበረው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ የባቤልን ግንብ ስለገነቡት ሰዎች ሲናገር “በድንጋይ ፈንታ ጡብ፣ ለማያያዣም ቅጥራን ተጠቀሙ” ይላል።​—ዘፍጥረት 11:3

ቅጥራን ከድፍድፍ ዘይት በተፈጥሮ የሚገኝ ፈሳሽ ነው። ይህ ፈሳሽ በሜሶጶጣሚያ ባሉ ብዙ አካባቢዎች በመሬት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ወደ ውጭ ሲወጣ ይረጋል። በጥንት ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ቅጥራን የማጣበቅ ባሕርይ እንዳለው ተገንዝበው ነበር። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ቅጥራን “በእሳት በተተኮሱ ጡቦች ለሚሠሩ ሕንፃዎች ተስማሚ” ነው።

አርኪኦሎጂ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ፣ ሜሶጶጣሚያ ውስጥ ባለችው በጥንቷ ኡር ከተማ በሚገኝ በፒራሚድ ቅርጽ የተሠራ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ አካባቢ በቅርቡ ስለተካሄደ ጉብኝት ያወሳል። የዚህ ርዕስ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል፦ “በደቡባዊ ኢራቅ በስፋት የሚገኘው ድፍድፍ ዘይት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ከዋለባቸው መንገዶች አንዱ ቅጥራንን ለማያያዣነት መጠቀም ነው፤ በእሳት የተተኮሱት ጡቦች የተያያዙት በቅጥራን እንደሆነ አሁንም መመልከት ይቻላል። በዛሬው ጊዜ በአካባቢው ላለው አለመረጋጋትና ዓመፅ ምክንያት የሆነው ይህ የሚያጣብቅ ጥቁር ነገር በአንድ ወቅት ለግንባታ የሚውሉትን ጡቦች ለማያያዝ አገልግሏል። ቅጥራን ለማያያዣነትና ለመንገድ ሥራ ጥቅም ላይ መዋሉ በቀላሉ ሊሰበር የሚችለው የሱሜሪያ ጡብ ውኃ የማያስገባ እንዲሆንና የሚገነቡት ሕንፃዎችም ለበርካታ ሺህ ዓመታት ሳይፈርሱ እንዲቆዩ አስተዋጽኦ አድርጓል።”

በጥንት ዘመን የነበረው “ወረቀት” ምን ዓይነት ነው?

ይህ ጥያቄ የሚነሳው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ዮሐንስ “የምጽፍላችሁ ብዙ ነገር ቢኖረኝም በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልፈልግም” የሚል ሐሳብ በማስፈሩ ነው።​—2 ዮሐንስ 12

በዚህ ጥቅስ ላይ “ወረቀት” ተብሎ የተተረጎመው ሃርቴስ የተባለው የግሪክኛ ቃል፣ “ፓፒረስ” ከተባለው ውኃ ውስጥ የሚበቅል ተክል የተሠራ ወረቀትን ያመለክታል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ከዚህ ተክል አገዳ፣ ወረቀት ይሠራ የነበረው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እስከ 3 ሜትር የሚደርስ ቁመት ያላቸው አገዳዎች ተልጠው በስሱ ይሰነጠቃሉ፤ ከዚያም የተሰነጠቁት አገዳዎች በጣም ተጠጋግተው በቁመታቸው ይደረደራሉ፤ ቀጥሎም ሌሎቹ በስሱ የተሰነጠቁ አገዳዎች በቁመታቸው በተደረደሩት አገዳዎች ላይ በአግድሞሽ ይደረደራሉ፤ በመጨረሻም የተደራረቡት አገዳዎች በእንጨት መዶሻ ከተቀጠቀጡ በኋላ እንዲለሰልሱ ይደረጋል።”

የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች፣ በግብፅ እና በሙት ባሕር አካባቢ በፓፒረስ የተዘጋጁ በርካታ ጥንታዊ ጽሑፎች አግኝተዋል። በኢየሱስ ዘመን እንዲሁም ከዚያ በፊት በፓፒረስ ላይ የተጻፉ አንዳንድ ቅዱሳን መጻሕፍት በእነዚህ አካባቢዎች ተገኝተዋል። ሐዋርያት እንደጻፏቸው ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ደብዳቤዎች መጀመሪያ የተጻፉት በዚህ ዓይነቱ ወረቀት ላይ ሊሆን ይችላል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Spectrumphotofile/​photographersdirect.com

© FLPA/​David Hosking/​age fotostock