በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጸሎትን የሚሰማው አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

ጸሎትን የሚሰማው አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

ጸሎትን የሚሰማው አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ሰዎች ቢጸልዩም እንኳ አምላክ መኖሩን ይጠራጠራሉ። ለምን? ምናልባት በዓለም ላይ ያለውን ይህ ነው የማይባል ሥቃይና መከራ ስለሚያዩ ሊሆን ይችላል። አንተስ አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ያሳስብሃል?

አምላክ ሰዎችን የፈጠረው በዛሬው ጊዜ እንደምናየው ፍጽምና የጎደላቸው ሆነው እንዲሁም ሥቃይና መከራ እየደረሰባቸው እንዲኖሩ ነው? ሆን ብሎ ሰዎች እየተሠቃዩ እንዲኖሩ የሚያደርግን አምላክ ማክበር ያስቸግራል። እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የአንድን አዲስ መኪና አሠራር እያደነቅህ ዙሪያውን ስትመለከት በአንድ በኩል ትንሽ ጉዳት ደርሶበት ብታይ አምራቹ ሆን ብሎ በዚህ መንገድ ሠርቶታል ብለህ ታስባለህ? እንዲህ እንደማታስብ የተረጋገጠ ነው! አምራቹ መኪናውን እንከን አልባ ወይም “ፍጹም” አድርጎ እንደሠራውና የሆነ ሰው ወይም የሆነ ነገር ጉዳት አድርሶበት እንደሚሆን ማሰብህ አይቀርም።

በተመሳሳይም በተፈጥሮ ላይ የሚታየውን አስደናቂ ሥርዓትና ንድፍ እናደንቅ ይሆናል፤ በሌላ በኩል ግን የሰው ልጆችን ሕይወት የሚያመሳቅለውን ሥርዓት አልበኝነትና ሙስና እንመለከታለን። ታዲያ ምን ዓይነት መደምደሚያ ላይ ልንደርስ ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት የፈጠራቸው ፍጹም አድርጎ ነው፤ እንከን ያላቸው ወይም ፍጽምና የጎደላቸው ሊሆኑ የቻሉት በራሳቸው ጥፋት ነው። (ዘዳግም 32:4, 5) ደስ የሚለው ነገር፣ አምላክ ይህን እንከን ለማስተካከል ይኸውም ታዛዥ የሆኑትን የሰው ዘሮች ወደ ፍጽምና ለመመለስ ቃል ገብቷል። ታዲያ እርምጃ ሳይወስድ ይህን ያህል ረጅም ጊዜ የቆየው ለምንድን ነው?

ይህን ያህል ጊዜ የቆየው ለምንድን ነው?

የዚህ ጥያቄ መልስ፣ የሰውን ዘር ሊገዛው የሚገባው ማን እንደሆነ ከተነሳው ጥያቄ ጋር ግንኙነት አለው። ይሖዋ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ በጭራሽ ዓላማው አልነበረም። የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች በእሱ አገዛዝ ሥር እንዲሆኑ ነበር። የሰው ልጅ “[አካሄዱን] በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል” መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይናገራል። (ኤርምያስ 10:23) የሚያሳዝነው ነገር፣ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በአምላክ አገዛዝ ላይ ለማመፅ መረጡ። በዚህ መንገድ የአምላክን ሕግ መጣሳቸው ኃጢአተኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው። (1 ዮሐንስ 3:4) በዚህም የተነሳ ፍጽምናቸውን ያጡ ሲሆን ራሳቸውም ሆነ ዘሮቻቸው እንከን እንዲኖራቸው አድርገዋል።

በብዙ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሰዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ይሖዋ ፈቅዶላቸዋል፤ በዚህ ጊዜ ያስመዘገቡት ታሪክ ግን እንዲህ ያለው ችሎታ እንደሌላቸው አሳይቷል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሁሉም ሰብዓዊ መስተዳድሮች ሥቃይና መከራ ያስከትላሉ። ማናቸውም ቢሆኑ ጦርነትን፣ ወንጀልን፣ የፍትሕ መዛባትን ወይም በሽታን ማስወገድ አልቻሉም።

አምላክ ይህን እንከን የሚያስተካክለው እንዴት ነው?

አምላክ በቅርቡ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚፈቀድላቸው፣ ለሰዎችም ሆነ ለአምላክ ፍቅር ለማሳየት የሚመርጡ ግለሰቦች ብቻ ናቸው።​—ዘዳግም 30:15, 16, 19, 20

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ በፍጥነት እየቀረበ ባለው “የፍርድ ቀን” አምላክ ሥቃይንና መከራን ብቻ ሳይሆን ለዚህ መንስኤ የሚሆኑትን በሙሉ እንደሚያጠፋ ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 3:7) ከዚያም አምላክ የሾመው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ታዛዥ የሆኑትን የሰው ልጆች ይገዛል። (ዳንኤል 7:13, 14) የኢየሱስ አገዛዝ ምን ያከናውናል? መጽሐፍ ቅዱስ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” ይላል።​—መዝሙር 37:11

ኢየሱስ በሰማይ ሆኖ ምድርን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ሰዎች “የሕይወት ምንጭ” በሆነው በይሖዋ ላይ በማመፃቸው ምክንያት ያጋጠማቸውን እንከን ያስተካክላል፤ ይህም በሽታን፣ እርጅናንና ሞትን ማስወገድን ይጨምራል። (መዝሙር 36:9) ኢየሱስ የእሱን ፍቅራዊ አገዛዝ የሚቀበሉ ሰዎችን በሙሉ ይፈውሳቸዋል። እሱ በሚገዛበት ጊዜ የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች እውን ይሆናሉ፦

▪ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም፤ በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ኀጢአትም ይቅር ይባላል።”​—ኢሳይያስ 33:24

▪ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”​—ራእይ 21:4

አምላክ ሥቃይንና መከራን በሙሉ ለማስወገድ የገባውን ተስፋ በቅርቡ እንደሚፈጽም ማወቁ አያጽናናም? አምላክ ለጊዜው መከራ እንዲደርስ ቢፈቅድም ጸሎታችንን እንደሚሰማ ግን ልንጠራጠር አይገባም።

አምላክ አለ። ለእሱ የምታቀርበውን ጸሎት ሌላው ቀርቶ ሥቃይና መከራ ሲደርስብህ የምታሰማውን ምሬት እንኳ ይሰማል። ከዚህም ሌላ ያሉብህ ጥርጣሬዎችና መከራዎች ሙሉ በሙሉ ተወግደው በደስታ የምትኖርበትን ጊዜ ለማየት ይጓጓል።